ኢትዮጵያን ከብተና ለመታደግ በተለያዩ ግንባሮች በጀግንነት ሀገራዊ ተልዕኳቸውን ሲወጡ ለቆዩ የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ የሠራዊት አባላት እና አመራሮች በቡልቡላ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል የጀግና አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡
በሥነ ስርዓቱ ላይ የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላን ጨምሮ ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰን እና ከፍተኛ ጄኔራል መኮንኖች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የሠራዊት አባላት ተገኝተዋል።
በመርሐ ግብሩ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ባደረጉት ንግግር÷የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ አመራሮችና አባላት ባለፉት ዓመታት ሀገርን ለማዳን ያበረከቱት አስተዋጽኦ፣ የከፈሉት መስዋዕትነት ሀገርን ያዳነ ወገንን ያኮራ ነው ብለዋል፡፡
ለፈፀሙት ታላቅ የጀግንነት ተጋድሎ ምስጋና እንደሚገባቸው አውስተው÷የጀግንነት ታሪካቸውም በሚገባ ተፅፎ ለትውልድ መተላለፍ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የኮማንዶና አየርወለድ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ በበኩላቸው÷የጀግንነት አሻራ ፅፎ ለማለፍም ሆነ ለማሥቀጠል በተቀናጀ አግባብ መብቃት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
በአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ የዓውደ ውጊያ ውሎዎችን የሚያስቃኝ የፎቶ ዐውደ ርዕይና ገላጭ የሆነ ዘጋቢ ፊልም መቅረቡን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
0 Comments