ፊንፊኔ #Ethiopia መጋቢት 14,2015(YMN) ሀሰተኛ ሰነድ አቅርበሻል በማለት ከአንድ ግብር ከፋይ ግለሰብ 70ሺ ብር ጉቦ የተቀበለ የገቢዎች ባለሙያን እጅ ከፍንጅ መያዙን እና በወንጀሉ ተባባሪ የሆነ አንድ ባለሙያን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
በቂርቆስ ክ/ከተማ የአነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርጫፍ ጽ/ቤት የአወሳሰን ባለሙያ የሆነው አንድ ሰራተኛ የቅርጫፍ ጽ/ቤቱ ግብር ከፋይ የሆኑ ግለሰብን ካቀረብሽው 10 ደረሰኞች መካከል 8ቱ የተበላሹ በመሆኑ ወደ አጣሪ ኮሚቴ መላኩንና ሁለቱ ደግሞ እጄ ላይ ይገኛሉ በማለት ጉዳዩን ለማዳፈን ግን 100ሺ ብር ጉቦ እንዲሰጠው ይጠይቃል፡፡ የግል ተበዳይ ያቀረቧቸው ሰነዶች ትክክለኛ እንደሆኑ ለማስረዳት ቢሞክሩም ባለሙያው ሳይቀበላቸው ይቀራል፡፡ የአወሳሰን ባለሙያ የሆነው ይህው ግለሰብ በቢሮ ስልክ ደጋግሞ በመደወል የግል ተበዳይን በማስጨነቅ በህግ እንደሚጠየቁ በማስፈራራት 70ሺ ብር ለመቀበል ይስማማል፡፡
የግል ተበዳይ ጉዳዩን ለተቋሙ ኃላፊዎች በማሳወቅ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የደንበል አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ባደረገው ክትትል በቅርጫፍ ፅ/ቤቱ የአወሳሳን ባለሙያ የሆነው ሙያተኛ 22 አካባቢ ከሚገኘው መስቲ ሬስቶራንት አካባቢ ሚዚያዚያ 13 ቀን 2015 ዓ/ም ገንዘቡን ሲቀበል እጅ ከፍንጅ መያዙን እና የዚህ ወንጀል ተባባሪ የሆነው በተቋሙ የጥቆማ አቀባበል ባለሙያ ከፍተኛ ኦፊሰር የሆነው ሰራተኛ ደግሞ በተመሳሳይ ቀን በጉቦ የተገኘውን ገንዘብ ሲቀበል መገናኛ አካባቢ እንደተያዘ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
0 Comments