ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉራጌ ምን ተጠየቁ ምላሻቸውስ?



ፊንፊኔ #Ethiopia መጋቢት 17,2015(YMN) ትናንት በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ከህብረተሰቡ ጋር የተወያዩት ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ከተሳታፊዎች በክልል መደራጀት ጥያቄ፣ የልማት ጥያቄዎች ቀርቦላቸው ምላሽ ሰጥተዋል።

የክልልነት ጉዳይን በተመለከተ አንድ ተሳታፊ አባት "የክልሉ ጉዳይ መቼ፣ እንዴት፣ በምን አይነት ሁኔታ ምላሽ ያገኛል የሚለው ቢቀመጥ" ሲሉ ዶ/ር ዐቢይን ጠይቀዋል። አንድ ሌላ ተሳታፊ (ሴት) የክልልነት ጥያቄው የተጠየቀው "ማንነታችንን፣ ባህላችንን ለማሳደግ ታሳቢ በማድረግ ነው፤ ይሄን ብልፅግና ይመልስልናል ባህላችን፣ ቋንቋችን ያደገበት ሁኔታ የለም ፤ ቋንቋችንን፣ ባህላችንን ለማሳደግ የቱሪዝም ስራዎችን ወደ አካባቢያችን ለመሳብ እንዲሁም የልማት የጠቃሚ እንድንሆን በተለይም የውሃ፣ የመብራት ፣ መንገድ ችግሮችን ክልል ብንሆን መመለስ ይቻል ይሆናል በሚል ታሳቢ በማድረግ ነው የተጠየቀው " ሲሉ ተደምጠዋል። ጠ/ሚኒስትሩ ምን ምላሽ ሰጡ ? የክልልነት ጥያቄው በህግ አግባብ ብቻ ምላሽ ያገኛል ብለዋል። ጥያቄው ከተነሳ ጊዜ አንስቶ ምላሽ ለመስጠት በተሰራበት የህግ አግባብ ዛሬና ነገን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ቢስተናገድ የተሻለ ነው ሲሉ ተናግረዋል። ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ፦ " ክልል የሚባለው ቢመለስ በ6 ወር ደመወዝ ባትከፍሉ ጭቅጭቅ ይቀራል ? አይቀርም፤ ክልል ያለው እኮ ለልማት ብለን ነው እንጂ 10 ሰው ኮብራ እንዲይዝ አይደለም ትላላችሁ አይቀርም። አሁን መክረን ዘክረን የነገውንም ታሳቢ አድርገን መወሰን ይጠቅማል " በሌላ በኩል ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ ከልማት ጥያቄዎች ጋር በተየያያዘ በተለይም የውሃ፣ መንገድ፣ ሆስፒታል፣ ት/ቤት ጥያቄ ቀርቦላቸው መልሰዋል። ዶ/ር ዐቢይ ባለፉት ዓመታት መንግስት በዞኑ ያለውን ችግር ለመፍታት ሲሰራ እንደነበር አስታውሰው አሁንም ያሉ ችግሮችን በእርጋታና ንግግር ይመለሳል ብለዋል። ዶ/ር ዐቢይ "ውሃ እየጠየቅን የቧንቧ መስመር የምንሰብር ከሆነ፣ መንገድ እየጠየቅን ድልድይ የምናፈርስ ከሆነ ወደምንፈልገው ነገር አያደርስም፤ ወደምንፈልገው የሚያደርሰን በተረጋጋ መንገድ ተወያይተን፣ ተመካክረን፣ ጊዜ ወስደን ምላሽ መስጠት ስንችል ነው" ብለዋል።
ፌዴራሉ መንግስት ከክልል ጋር በመመካከር አንገብጋቢ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መፍትሄ ይፈልጋል ያሉት ዶ/ር ዐቢይ " በምንችለው ልክ አጣዳፊ የሆኑ እንደ ውሃ ያለውን ምላሽ ለመስጠት እንሞክራለን " ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ያለፉትንን ዓመታት ከፍተኛ ጫና ውስጥ እንደነበረች ሊዘነጋ አይገባም ያሉት ዶ/ር ዐቢይ በሁሉም ቦታ የልማት ጥያቄዎች አሉ እንደ ሀገር ያለንን አቅም በውጤታማነት ጊዜን በመጠበቅ ከመጠቀም ያለፈ አማራጭ የለም ብለዋል። ከልማት ስራ ጋር በተያያዘ መንገድን ያነሱት ዶ/ር ዐቢይ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉትን የተጀመሩ የመንገድ ስራዎችን ለማስጨረስ የሚያስፈልገው ገንዘብ 1 ትሪሊዮን መድረሱን ገልፀዋል። "የኢትዮጵያ መንግስት የአንድ አመት በጀት እዛ አልደረሰም" ያሉት ዶ/ር ዐቢይ ሙሉ በጀት መንገድ ላይ ቢውል እንኳን አዲስ ሊሰራ ቀርቶ የተጀመረውን አይጨርስም ስለዚህ ጊዜ ያስፈልጋል ብለዋል። ዶ/ር ዐቢይ "ጦርነት ውስጥ ነበርን፣ የዓለም መንግስታት ባይናገሩትም በብዙ መንገድ መደገፍ በሚገባቸው ልክ ሳይደግፉን የያዙን ጊዜ ነበር፣ ድርቅ ያጋጠመን ጊዜ ነበር፣ ብዙ ወጀቦች ያለበት ጊዜ ነው እንደዛም ሆኖ በየቦታው እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተስፋ የሚሰጡ እንጂ ተስፋ የሚያስቆርጡ አይደሉም" ብለዋል።
አክለው "ትንሽ ጊዜ መረጋጋት ከቻልን ነገሮች ወደ ሰላም እየሄዱ ስለሆነ በውስጥ ያለንን አቅም ከውጭም የምናገኛቸውን ድጋፎች ጨምረን በርካታ የልማት ስራዎችን ለመስራት እንሞክራለን" ሲሉ ተናግረዋል

Post a Comment

0 Comments