ፊንፊኔ #Ethiopia ሚያዚያ 22/2015 (YMN) በአማራ ክልል በህቡዕ አደረጃጀት ውስጥ ሲንቀሳቀሱና የሽብር ተግባር ሲፈጽሙ የተገኙ 47 ተጠርጣሪዎችን ከበርካታ የነፍስ ወከፍና የቡድን መሣሪያዎች፣ ቦንቦችና ተቀጣጣይ ፈንጂዎች ጋር በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል
ከፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል የተሰጠው ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
በአማራ ክልል ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን በማፍረስ ክልላዊ ስልጣንን በኃይል ለመያዝ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት በህቡዕ ተደራጅተውና ተቀናጅተው በሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ኃይሎች ላይ የማያዳግም ህጋዊ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ሚያዚያ 20 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል።
በመሆኑም የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል እየወሰደ ባለው እርምጃ በዚህ ህቡዕ አደረጃጀት ውስጥ ሲንቀሳቀሱና የሽብር ተግባር ሲፈጽሙ የተገኙ 47 ተጠርጣሪዎችን ከበርካታ የነፍስ ወከፍና የቡድን መሣሪያዎች፣ ቦንቦችና ተቀጣጣይ ፈንጂዎች እንዲሁም ከሳተላይት መገናኛ መሣሪያዎች እና የተለያዩ መረጃዎችን ከያዙ ላፕቶፖች ጋር በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ አመልክቷል።
ተጠርጣሪዎቹ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችን የግድያ ዒላማ በማድረግ፤ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል በመናድ የክልሉን መንግሥታዊ መዋቅር በመቆጣጠር የፌደራል መንግሥትን ለመጣል በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ተደራጅተው እና ተቀናጅተው በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ እንደተደረሰባቸው አስታውቋል።
ግብረ-ኃይሉ ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ፤ መንግስት የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት እና ለሐሳብ ትግል ሰፊ ዕድል በመስጠቱ እንዲሁም ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ ባደረገው ጥረት ብዙዎች ይሄንን ዕድል መጠቀማቸውን አስታውሷል።
ይሁንና የአማራን ህዝብ የማይወክሉ እነዚህ ጽንፈኛ ኃይሎች የመንግሥትን ሰላማዊ አማራጭ በመግፋት በውጭ ከሚገኙ ግብረ-አባሮቻቸው ጋር በህቡዕ በመገናኘት የፖለቲካ፣ የወታደራዊ፣ የኢንተለጀንስ፣ የሚዲያ እና የፋይናንስ ክንፍ ማቋቋምቸው እንደተደረሰበት መግለጫው አመልክቷል።
የጋራ ግብረ-ኃይሉ መግለጫ እንዳመለከተው፤ የጽንፈኛ ኃይሎችን የፖለቲካ፣ የወታደራዊ፣ የኢንተለጀንስ፣ የፋይናንስ እና የሚዲያ ክንፍ የሚመራው ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ የተባለ ግለሰብ ሲሆን፤ ይህ ክንፍ በተለያዩ የውጭ ሀገራት ከሚገኙ 16 ጽንፈኛ የዲያስፖራ አባላት ጋር ትስስር በመፍጠር በሚያገኛቸው የሎጀስቲክስ እና የፋይናንስ ድጋፎች በአማራ ክልል ከባህርዳር ከተማ ጀምሮ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ታጣቂዎችን የመመልመል፣ የማሰልጠን፣ የማስታጠቅና የማሠማራት ተግባር በማከናወን በክልልና በፌደራል ደረጃ ሽብር እና ግድያ እንዲፈጽሙ ተልዕኮ ሲሰጥ እንደነበር በተደረገ ክትትል እና ምርመራ ተደርሶበታል ብሏል መግለጫው።
ለዚህም በለጠ ሸጋው እና ምሕረት ወዳጆ ወይም በቅጽል ስሙ ምሬ ወዳጆ በተባሉት የጽንፈኛ ኃይሉ ታጣቂ መሪዎች እና ግብረ-አባሮቻቸው ሰሞኑን በትውልድ በቀኤአቸው ግፍና ጭካኔ በተሞለበት አኳሃን የተገደሉት የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ እና የጥቃት ሰለባ የሆኑ የሥራ ባልደረቦቻቸው ማሳያ ናቸው ብሏል የጋራ ግብረ-ኃይሉ መግለጫ።
የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል መግለጫ አክሎም፤ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የሚገኙ እነዚህ ጽንፈኛ ኃይሎች በፈጠሩት ህቡዕ አደረጃጀት እኩይ ዓላማቸውን ለማስፈጸም በአማራና በሌሎች አካባቢዎች በሚገኙ 130 ወረዳዎች የመለመላቸውንና በህቡዕ ያዘጋጇቸውን 450 ግለሰቦች የአማራ ክልል ህዝብ የመረጣቸውንና በተለያዩ የአመራር እርከኖች ላይ ያስቀመጣቸውን በኃይል በማስወገድ በራሳቸው መዋቅር የመተካት ሥራ ሲሰሩ እንደነበር በክትትል እና በምርመራ የተደረሰባቸው መሆኑን አስታውቋል።በተጨማሪም ጽንፈኛ ኃይሎች የክልሉን የፀጥታ ኃይልንም በራሳቸው ታጣቂዎች ለመቀየር ተዘጋጅተው እንደነበር የተገኛው መረጃ ማመላከቱን ገልጿል።
ዶ/ር መሥፍን ኃ/ማርያም፣ ዶ/ር ግሩም ላቀውና ሌሎችም በተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚኖሩ የጽንፈኛ ኃይሉ ተባባሪዎች ከውጭ ሆነው የፖለቲካ ክንፉን እንደሚያስተባብሩ፤ አንተነህ ብርሃን፣ ወርቁ ጓዴና ሌሎችም ከሀገር ውስጥና ከውጭ የሚላከውን ገንዘብ እንዲቀበሉና ለሽብር ተልዕኮ ማስፈፀሚያ እንዲያውሉ የባንክ አካውንት እንደተከፈተላቸው በክትትልና በተደረገው ምርመራ መረጋገጡን የገለፀው የጋራ ግብረ-ኃይሉ መግለጫ፤ ቴዎድሮስ አስፋውን ጨምሮ ሌሎችም በዚሁ የሽብር እንቅስቃሴ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን መግለጫው አስታውቋል።
መግለጫው አያይዞም የእነዚህ ጽንፈኛ ኃይሎችን የሚዲያና ፕሮፓጋንዳ ክንፍ የሚመራው መስከርም አበራ በተባለች ግለሰብ መሆኑን ጠቅሶ፤ በዚህ ህቡዕ አደረጃጀት ውስጥ ከሀገር ውስጥ ዳዊት በጋሻው የተባለ ግለሰብ እንዲሁም ከተለያዩ የውጭ ሀገራት ደግሞ ከኢትዮ 360 እና መረጃ ቲቪ ሀብታሙ አያሌው፣ ምንአላቸው ስማቸው፣ ብሩክ ይባስ እና እየሩሳሌም ተ/ፃዲቅ በተጨማሪም ዘመድኩን በቀለ እና ልደቱ አያሌው ከአንከር ሚዲያ መሳይ መኮንን እንዲሁም ሌሎች ግለሰቦች የዚህ እኩይ ዓላማ አስፈፃሚ አባላት መሆናቸውን በምርመራ መረጋገጡን ገልጿል።
እነዚህ ጽንፈኛ ኃይሎች የሀሰት ወሬዎችን በመፍጠር እና ከፍተኛ የሽብር ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ህዝቡን በብሄር እና በሀይማኖት በመከፋፈልና በማጋጨት የክልል እና የፌደራል መንግሥትን በኃይል ለመጣል እንዲሁም ሀገሪቱ ከጀመረችው የለውጥና የልማት መንገድ ወጥታ ወደ ለየለት ሁከትና ትርምስ እንድትገባ በህቡዕ ተደራጅተው እየሠሩ መሆናቸውን የገለፀው የጋራ ግብረ ኃይሉ፤ በሀገር ውስጥና በውጭ ሆነው በሀሰት ሀገር ለማፍረስ የሚሰሩ እነዚህን ጨምሮ ሌሎችም በህቡዕ አደረጃጀቱ ውስጥ ያሉ ግለሰቦችም ጭምር በሽብርተኝነት ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑን መግለጫው አመልክቷል።
እነዚህ የሽብር ኃይሎች ከሚኖሩባቸው ሀገራት በአለም አቀፍ የፖሊስ ድርጅት (ኢንተርፖል) እንዲሁም እነሱ ከሚኖሩባቸው ሀገራት መንግሥት የፀጥታ እና የደኅንነት ተቋማት ጋር በተመሠረቱ የትብብር ማዕቀፎች አማካኝነት ወደ ሀገር ቤት ተላልፈው እንዲሰጡ በህግም እንዲጠየቁ እየሰራ መሆኑን እና ይህንኑ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።
የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል መግለጫ አክሎም፤ እነዚህ ውጭ ሀገር የሚኖሩ ተፈላጊዎች ከውጭ ሀገር በሚያገኙት እና በሀገር ውስጥ ያላቸውን ሀብት ተጠቅመው ለዚህ እኩይ ተግባር እያዋሉ መሆኑን በምርመራ የተደረሰበት ስለሆነ በሀገር ውስጥ ያላቸውን ሀብት የመለየት እና በህግ የመቆጣጠር ስራ እየተሰራ መሆኑንም ጭምር አስታውቋል።
ሕገ-መንግሥቱንና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለማፍረስ እየተንቀሳቀሱ የነበሩ እነዚህ ጽንፈኛ ኃይሎች የኢትዮጵያን አንድነት ከማይፈልጉ የውጭ ፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር ተቀናጅተው መንግሥትን በኃይል ለማስወገድ ሲሰሩ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው የሚገኝ መሆኑን ያመለከተው የጋራ ግብረኃይሉ መግለጫ፤ ኅብረተሰቡ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚወሰደውን እርምጃ ከትጥቅ ማስፈታት ጋር በማያያዝ ውዥንብር ለመፍጠርና የተሳሳተ መረጃ ለማሰራጨት ከሚጥሩ አካላት ራሱን እንዲጠብቅ በጋራ እንዲታገል ጥሪ አቅርቧል።
በመጨረሻም የተጀመረው ህጋዊ ኦፕሬሽን ከግቡ እንዲደርስ ህብረተሰቡ እያደረገ ላለው ከፍተኛ ተሳትፎ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ምስጋና እያቀረበ፤ በህግ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ጥብቅ ክትትል እየተደረገባቸው ያሉ ተፈላጊዎችን ካሉበት ጠቁሞ እንዲያሲዝ በዚህ አጋጣሚ ጥሪውን እያቀረበ በቀጣይ የምንደርስበትን ውጤት ለህዝብ እየገለፀ እንደሚሄድ ያስታውቃል።
የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል
ሚያዝያ 22 ቀን 2015 ዓ.ም
0 Comments