በአማራ ክልል ሕገመንግስታዊ ስርዓቱን በማፍረስ ክልላዊ ስልጣንን በኃይል ለመቆጣጠር በሚጥሩ ጽንፈኛ ኃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ እየተወሰደ ነው፦ የጸጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል
የጸጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ለአማራ ህዝብ እንታገላለን በሚል በውስጥም በውጭም በመቀናጀት የራሳቸውን ህቡዕ አደረጃጀት የፈጠሩ አካላት ከመሰል ቡድኖች ጋር በመቀናጀት የህዝቡን የቁርጥ ቀን ልጆች መልሰው እየበሉ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ፅንፈኛ ኃይሎች በትናንትናው ዕለትም የአማራ ክልል ብልፅግና ጽ/ቤት ሓላፊ እና የክልሉ የቁርጥ ቀን ልጅ የሆነውን ግርማ የሺጥላን በመግደል አስነዋሪ ድርጊታቸውን አሰመስክረዋል፡፡
ይሄንን እኩይት የጥፋ ሴራ እየፈፀሙ ያሉ ፅንፈኛ ኃይሎች የአማራ ህዝብ የልማትና የሰላም ተጠቃሚ እንዳይሆንና የተረጋጋ ህይወት እንዳይኖረው እንዲሁም በመንግስት የሚወሰኑ ውሳኔዎች እንዳይተገበሩ እንቅፋት ሲፈጥሩ መቆየታቸውን የጋራ ግብረ ኃይሉ መግለጫ አመልክቷል፡፡ በየአካባቢው የተደረጉ የሽምግልና ሂደቶችን በመግፋት እንዲሁም የተቀበሉ በመምሰል በህቡዕ ተደራጅተውና ተቀናጅተው ሕገወጥ ተግባራቸውን መቀጠላቸውን አስታውቋል፡፡ በአማራ ክልል ሕገመንግስታዊ ስርዓቱን በማፍረስም ክልላዊ ስልጣንን በኃይል ለመቆጣጠርም ሲጥሩ መቆየታቸውን ጠቅሷል፡፡ የጸጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይልም ይህን ተከትሎ አስፈላጊና ህጋዊ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ጠቁሟል፡፡
ይሄ ጽንፈኛ ሀይል በአማራ ክልል ሳይገደብ እንደ ሀገርም መንግስትን በኃይል ከስልጣን ለማስወገድ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም ያለው የጋራ ግብረ ኃይሉ መግለጫ፤ ከዚህ የጥፋት መንገዳቸው እንዲመለሱ በተደጋጋሚ የተሰጣቸውን እድል ከመጠቀም ይልቅ አሁንም በሕግወጥ ተግባራቸው መቀጠላቸውን አመልክቷል፡፡ በዚህ ህግወጥ ተግባራቸውም በቁጥጥር ስር ዉለው ጉዳያቸው በህግ እየታየ የሚገኙ በርካታ የቡድኑ አባላት መኖራቸውንም ግበረ ሃይሉ አስታውቋል፡፡ መንግስት በሃገሪቱ ብሎም በክልሉ የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሓላፊነት ያለበት በመሆኑ በሌሎቸም የሕገውጥ ቡድኑና ቡድኑን በገንዘብና በሀሳብ በህቡእ በሚደግፉ አካላትና ግለሰቦች ላይ የማያዳግም እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ የፅንፈኛ ቡድኖቹ ደጋፊዎች በዚህ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጅ ላይ የተፈፀመውን ግድያ ከመኮነን ይልቅ አሳፋሪ በሆነ መልኩ ገዳይ ቡድኖቹን ሲደግፉ ተስተውለዋል ብሏል መግለጫው፡፡
ሃሳብን በሃሳብ ከማሸነፍ ይልቅ ከኢትዮጵያዊ ጨዋነት ባፈነገጠ መልኩ በአሰቃቂ ሁኔታ ግድያ የፈጸሙትን ፅንፈኛ ቡድኖች ህዝቡ በአንድነት በማውገዝ ኢትዮጵያዊ ጨዋነቱን ሊያስመሰክር ይገባልም ብሏል፡፡
በአቶ ግርማ የሺጥላ ላይ የተፈፀመው አሰቃቂ ግድያ የፅንፈኛ ኃይሎቹን ትክክለኛ መልክና ገፅታ ለህዝቡ በይፋ ያጋለጠ ነው ያለው የደኅንነትና የጸጥታ የጋራ ግብረ ኃይል መግለጫ፤ መንግስት ለህዝቡ ሰላምና ደኅንነት መረጋገጥ ግዴታውን ለመወጣት አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ የጀመረ በመሆኑ፤ ህዝቡም ይሄንን ተገንዝቦ የፌደራል እና የክልል የፀጥታ አካላት ተጠያቂነትን ለማስፈን የጀመሩትን እንቅስቃሴ ጥቆማና መረጃ በመስጠት እንዲደግፍ የጋራ ግብረ ሀይሉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
መግለጫው አክሎም፤ የፅንፈኛ ሀይሎቹን አስነዋሪ ተግባር በመሸፋፈን በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገፆች መሰረተ ቢስ ወሬዎችን ከሚያሰራጩ የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች ህብረተሰቡ ራሱን እንዲጠብቅ አሳስቦ፤ ግብረ ሀይሉ እየወሰደ ያለውን እርምጃ በቀጣይ ለህዝቡ የማሳወቅ ስራው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጧል፡፡
0 Comments