የፊንፊኔ ፖሊስ ስለ ዛሬው ውሎ ምን አለ?




ፊንፊኔ #Ethiopia ግንቦት 18/2015(YMN) ዛሬ አርብ (የጁምዓ) ሶላት ከተጠናቀቀ በኋላ በመርካቶ አካባቢ " ረብሻና ግርግር " ተፈጥሮ የሰው ሕይወት አልፏል፤ ህግ በማስከበር ስራ ላይ በተሰማሩ የፖሊስ አባላት ላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት ደርሷል ሲል ገልጿል።

በአንዋር መስጂድ የጁምዓ ሶላት ከተጠናቀቀ በኋላ በሌሎች አካባቢዎች " መስጂዶች ፈርሰዋል " በሚል ምክንያት በመርካቶ ዙሪያ በተፈጠረ " ረብሻና ግርግር " የሁለት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ ህግ በማስከበር መደበኛ ሥራ ላይ በነበሩ የፖሊስ አባላት ላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት ደርሷል ብሏል።

በተለይ በተለምዶ " ጋዝ ተራ " እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ተፈጥሮ በነበረ " ግርግር " ሁለት ግለሰቦች ጉዳት ደርሶባቸው ለህክምና ሆስፒታል ከተላኩ በኋላ ሕይወታቸው አልፏል ሲል ገልጿል።

እንዲሁም አራት ግለሰቦች ጉዳት ደርሶባቸዋል ያለው ፖሊስ ህግን ለማስከበር በተሰማሩ 37 የፖሊስ አመራርና አባላት እንዲሁም 15 የሚሆኑ የተለያዩ የፖሊስ አጋዥ ሀይሎች ከባድና ቀላል ጉዳት ደርሶባቸው ለህክምና ተልከዋል ብሏል።

" ረብሻውን ባስነሱት አካላት " ንብረትነታቸው የአዲስ አበባ ከተማ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በሆኑ ሁለት አውቶቡሶች ላይ ጉዳት ደርሷል ያለው ፖሊስ ፤ " መነሻውን አንዋር መስጂድ ያደረገው ረብሻ በጋዝ ተራ ፣ ቆርቆሮ ተራ ፣ ሰባተኛ አካባቢ ፣ አመዴ እና በተለያዩ አካባቢ ለማዛመት የተሞከረ ቢሆንም በፀጥታ አካሉ ጥረት ረብሻው ሳይስፋፋ መቆጣጠር ተችሏል " ብሏል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ፤ " በአንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎች በአዲስ አበባ ከፍተኛ የሆነ ረብሻ እንደተነሳ ተደርጎ እየተናፈሰ ያለው መረጃ የተጋነነ ነው " ያለ ሲሆን " አጋጥሞ የነበረው ብጥብጥ በቁጥጥር ስር ውሎ አካባቢው ወደ መደበኛው እንቅስቃሴ ገብቷል ፤ ብጥብጡን በመምራትና በማስተባበር እንዲሁም ዋነኛ ተሳትፎ የነበራቸው 114 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር በማዋል በህግ አግባብ ምርመራ እየተደረገባቸው ነው " ሲል ገልጿል።

ፖሊስ " በአዲስ አበባ በህዝበ ሙስሊሙም ሆነ በዕምነት ተቋሙ ላይ የተፈጠረ ችግር ሳይኖር በሌሎች ቦታዎች ላይ መስጂድ ፈርሷል በሚል ምክንያት ህገ-ወጥ ሰልፍ በማድረግ ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል " ያለ ሲሆን " በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ አቅደው በተንቀሳቀሱ ግለሰቦች ላይ የፀጥታ አካላት እየወሰዱት ያለውን እርምጃ አጠናክረው ይቀጥላሉ ፤ የከተማችንን ሠላምና ፀጥታ ለማወክ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ከህገ-ወጥ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ " ሲል አስጠንቅቋል።

@ቲክቫኢትዮጵያ

Post a Comment

0 Comments