እንዲህም ይሆናል ከ75 ዓመታት ቆይታ በኋላ የተገናኙ ወንድማማቾች!

 


ፊንፊኔ #Ethiopia ሰኔ 13/2015(YMN) እንዲህ አይነት ታሪክ ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖራል ተብሎ የሚታሰብ አይመስልም፤ግን ደግሞ ሆኖ ይኸው በተግባር አየነው።

የጉዳዩ ታሪክ እንዲህ ነው አቶ ደለሳ ሞጋሳ እና ወይዘሮ በዶ ኦቦሌ የሚባሉ ሰዎች በምዕራብ ሸዋ ዞን ቶኬ ኩታዬ ወረዳ ጊምቢ ቢላ ተብሎ በሚታወቅ ቀበሌ በ1939 ዓም ትዳር መሰረቱ ትዳሩ አልፀና በሎ ለአንድ ዓመት እንኳ መቆየት ሳይቻል ቀረ አለመግባበት ተፈጠረና መለያየት ግድ ሆነ።

ወይዘሮ በዶ(Badhoo) ጽንስ ይዘው ወደ ቤተሰባቸው ተመልሰው ገቡ፤ከዚህ በኋላ ከራ የሚባል ሰው ወልደው ከሁለት ዓመታት ቆይታ በኋላ ልጃቸውን ለቤተሰብ ትተው ሌላ አካባቢ ትዳር መስርተው ብዙ ልጆችን ማፍራት ቻሉ፤ የወይዘሮ በዶ ልጅ አቶ ከራ የወንድ አያትና ሴት አያታቸውን እንደ አባትና እናት በማወቅ አደጉ።

አቶ ደለሳም የአቶ ከራን እናት ሳይፈልጉ ሌላ ሴት በማግባት የልጆች አባት ከሆኑ በኋላ ቀደም ካለው ትዳራቸው ልጅ መወለድ አለመወለዱን ባለማረጋገጣቸው ዕድሜያቸው 95 ዓመት ሲደርስ በመታመማቸው ለልጃቸው አቶ ቢቲማ ደለሳ አደራ በመስጠት እርሱ እንዲፈልግ መልዕክት በማስተላለፍ አረፉ።

አቶ ቢትማም ከአባታቸው የተሰጣቸውን አደራ ሳይበሉ ታሪክን መርምረው ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ወንድማቸው ወደሚገኝበት ወደ ምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ ወረዳ ደሴ አክሊሉ ወደምትባል ቀበሌ በማምራት ታላቅ ወንድማቸውን አቶ ከራ 75 ዓመት ዕድሜ አስቆጥረው አገኟቸው

አቶ ከራ የልጆች አባት በመሆን ልጆቻቸውን በመዳር ለወግ ማዕረግ አድርሰዋል፤ የ27 ልጆች አያትም ሆነው ደስታቸውን ገልፀዋል፤ታላቅ ወንድም ስለሆኑ እንዲሁም ፈልገው ስለ አጡ በኦሮሞ ባህል መሰረት ጋቢ በማልበስ ቅቤ ቀብተው ታላቅ ወንድማቸው ማድረጋቸውን አቶ ቢቲማ ደለሳ ተናግረዋል።

አቶ ከራ የውልደታቸውን ታሪክ ሳያውቁ ይህ አባትህ ነው ተብለው በሌላ ሰው ስም ሲጠሩ ኖረዋል በአያታቸው ዘንድ በማደግ የልጆች አባት ሆነው አቶ ቢቲማ ሲፈልጓቸው እንኳ ይጠራጠሩ እንደነበር ጠቁመው ወንድሞቻቸው በዚህ ጊዜ ፈልገዋቸው ስለ አገኟቸው ደስታቸውን በመግለጽ መርቀዋል።

ከአንድ እናት የተወለዱት የአቶ ከራ ወንድም አቶ ታደሰ ጉተማ እንዳሉት ወንድማቸው ወንድሞቻቸውን ስለ አገኙ ተደስተዋል፤እሳቸው በተወለዱበት ቦታ ይህ ሚስጢር ተደብቆ ቆየ ሲሉም ተናገረዋል አቶ ታደሰ ጉተማ፤አሁን የ75 ዓመት የእድሜ ባለፀጋ የሆኑት አቶ ከራ በአምቦ ወረዳ ደሴ አክሊሉ በምትባል ቀበሌ ውስጥ ከአመያ ጎሳ ጋር ተቀላቅለው አቀባበል ተደርጎላቸዋል።በዚህ ዓይነት ሁኔታ እናትና አባታቸውን ሳያውቁ የኖሩና ኖረውም ያለፉ ዜጎችን ብዛት ቤት ይቁጠረው።

ምንጭ:የቶኬ ኩታዬ ወረዳ ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት

 

 

 

Post a Comment

0 Comments