"የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመመካከር መወሰኑ በራሱ አብሮነቱንና አንድነቱን ከማስቀጠል የመነጨ ጽኑ ፍላጎት ያለው መሆኑን ማሳያ ነው"




ፊንፊኔ #Ethiopia ሰኔ 09/2015(YMN) የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመመካከር መወሰኑ በራሱ አብሮነቱንና አንድነቱን ከማስቀጠል የመነጨ ጽኑ ፍላጎት ያለው መሆኑን ማሳያ ነው ሲሉ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ምሕረቱ ሻንቆ ገለጹ።

ሚኒስትር ዴኤታው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት አስተያየት፣ ለመመካከር ፍላጎት ያለው ቡድን፣ ግለሰብ ወይም ሕዝብ ካለ ቀሪውን ረጅም መንገድ አብረው መጓዝ ይችላሉ።ለአጭር ጊዜ የጋራ ጉዞ ወይንም ለጋራ ቆይታ ሰፊ ምክክር እምብዛም አያስፈልግም።እንደ ሟርተኞች ሟርት ኢትዮጵያ የምትፈርስ አገር ሳትሆን አንድነቷን አስጠብቃ ትዘለቃለች።ለዚህም ነው ሕዝቦቿ በሙሉ ልባቸው ለምክክር እየተዘጋጁ ያሉት።

 ምክክር ከራስ ጀምሮ እስከ አገር ደረጃ የሚዘልቅ፣ የሰው ልጅም ሆነ በሰው ልጆች የሚመሩ ተቋማት በራሳቸው ሙሉ እንዳልሆኑ ግን ደግሞ ሙሉ ለመሆን ተጨማሪ ሰው ወይም ሐሳብ እንደሚያስፈልጋቸው ትልቅ ማሳያ ነው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ በተመሳሳይ መልኩ እንደ አገር ሰፋ ተደርጎ ሲታይም የዛሬዋ ኢትዮጵያ መልክና ቅርጽ የትናንቱ የሕዝቦቿ አስተዋፅዖ ድምር ውጤት በመሆኑ ስለነገዋም በጋራ ማጤን ያስፈልጋል ብለዋል።

እንደ ረዳት ፕሮፌሰር ምሕረቱ ገለጻ፣ የሰመረ የወደፊት የጋራ ጉዞ ለማድረግ ለመመካከር መወሰን እንደ ቀላል የማይታይ ምክንያታዊ ውሳኔ ነው።ምንም እንኳ ያለፉት የመንግሥት ሥርዓቶች የራሳቸው ደካማና ጠንካራ ጎን ቢኖራቸውም ስለ አገር ግን ጽኑ አቋም እንደነበራቸው እርግጠኛ መሆን ይቻላል።ከሕዝብ አንጻር ሲታይም ኢትዮጵያን ለመታደግ ያልተዋደቀ ሕዝብ አልነበረም።ሆኖም ግን መንግሥታቱ በአብሮነት ጉዞ ውስጥ የተፈጠሩ ችግሮች ላይ የመመካከር እድል ባለመስጠታቸው የዛሬ ትውልድ የድምር እዳ ተካፋይ ለመሆን ተገዷል። የምክክር ባሕልን ማዳበር ለአንድ አገር አንድነት፣ አብሮነትና እድገት ትልቅ ድርሻ መኖሩን እንደሚያሳይ ጠቅሰው፤ ከምክክር ውጪ በአገሪቱ የተሞከሩ ሌሎች የኃይል አማራጮች ከንቱ መሆናቸውን ያልተገነዘበ ኢትዮጵያዊ አለ ለማለት አያስደፍርም ብለዋል።ነገር ግን በምክክር የማይፈታ ችግር ስለሌለ ሁሉም ለምክክር መዘጋጀቱ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል።

ምክክር፣ የሐሳብ ፍጭትና ግጭት በመሆኑ ሕይወት ስለማያጠፋና ንብረትም ስለማያወድም የ21ኛው ክፍለ ዘመን ሥልጡን አካሄድ መሆኑ እጅግ ተመራጭ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በመሆኑም አገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን በየደረጃው ያሉ አለመግባባቶች መፈታት እንዳለባቸውና ሁሉም ለምክክር ያለውን ፍላጎት ወደ ተግባር ለመቀየር የድርሻውን መወጣት ይጠበቅበታል ብለዋል።

ዛሬ በብዙ ነገሮች የማይስማማው ሕዝብ፣ ስለ ነገ አብዝቶ መጨነቁ አይቀሬ ነው።በእርግጥም ለብዙ ዘመናት አብሮ የመጣው ሕዝብ ስለነገው መጨነቁ ከአብሮነትና ከዘላቂነት የሚመነጭ ጤናማ ሥጋት ነው፤ በመሆኑም ከዚህ አንጻር የአገሪቱ መጻዒ እድል ያማረና ከሥጋት የጸዳ እንዲሆን ለምክክሩ ስኬታማነት መላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች የታላቅነት ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በዚህ ደረጃ የምክክር መድረክን ማዘጋጀት በኢትዮጵያ የመጀመሪያ በመሆኑ ሊገጥሙት የሚችሉ ችግሮችን ለመታደግ በቁርጠኝነት መሥራት የሁሉም ኃላፊነት መሆኑም አስገንዝበዋል።

Maddi:Dhaabbata Pireesii Itiyoophiyaa

Post a Comment

0 Comments