አቶ አዲሱ ምን አሉ?




ፊንፊኔ #Ethiopia ሰኔ 14/2015(YMN) የብልጽግና ፓርቲ የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ቂጤሳ  ከሰሞኑ የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ያካሄዱት ውይይት በስኬት መጠናቀቁን አስመልክተው ሰፋ ያለ ጽሑፍ አጋርተዋል አንባቢዎቼ ለአጠቃላይ ግንዛቤ ይረዳችሁ ዘንድ የአቶ አዱሱን ጽሑፍ እንዲህ አቀረብኩላችሁ መልካም ንባብ!

ፓርቲያችን ብልጽግና እንደ ሀገር ያሉበትን ታላላቅ ተልዕኮዎች ሀገር እና ህዝብ በሚጠብቁበት ልክ እና መጠን ከግብ ማድረስ ይቻለው ዘንድ በተለያዩ ደረጃዎች ሲያካሂዳቸው የነበሩትን ውይይቶች በስኬት አጠናቋል፡፡ በማዕከላዊ ኮሚቴ፣ በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እና በከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ደረጃ በተደረጉትና በጥብቅ ዲሲፕሊን፣ በጥልቅ ውይይት፣ በሃሳብ ሙግት እና በዴሞክራስያዊ በሳል ውይይት በተመሩት በእነዚህ መድረኮች ላይም አሁናዊ እና ተሻጋሪ የሆኑ ዓለም አቀፋዊ፣ ኢኮኖሚያዊ- ፖለቲካዊ እና ሌሎች አጀንዳዎች ተንሸራሽረው አበይት የሚባሉት ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ተደርሷል፡፡ ግልጽ አቅጣጫዎችም ተቀምጠዋል፡፡

ከሀገራችን ሰላም እና ጸጥታ ረገድ አሁን ያለው ነባራዊ እውነታ ትላንት ከነበርንበት ጋር ሲነጻጸር ተስፋ ሰጪ እመርታዎች የታዩበት ቢሆንም አሁንም ቢሆን ከሰራናቸው የሰላም ግንባታ ስራዎች ይልቅ በርካታ ቀሪ የቤት ስራዎች እደሚጠብቁን በውይይቱ ተመላክቷል፡፡ በዚህም መሰረት የሃሳብ ልዩነቶች የግጭት መሰረቶች መሆን እንዳይችሉ እና በሰላማዊ መንገድ ሃሳባቸውን ማንሸራሸር ያልቻሉ በጉልበት ሃሳብን ወደመጫን እንዳይሸጋገሩ የፖለቲካ ምህዳሩን ይበልጥ የማስፋት እና መብትን ከግዴታ፣ ነጻነትን ከተጠያቂነት ጋር አቆራኝቶ በመምራት የተጀመረውን የዴሞክራሲ ግንባታ አጠናክሮ በማስቀጠል እንደሚገባ የጋራ አቋም ተይዟል፡፡
በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የተከሰቱ አለመግባባቶችን እና ግጭቶችን ሰላማዊ በሆነ አግባብ እልባት ለመስጠት የተሰሩ ስራዎች በውይይቶቹ ላይ የተነሱ ሲሆን እነዚህን አዎንታዊ ትሩፋቶች ማስፋት እና ለነጋችንም የሰላም ጉዞ ስንቅ ማድረግ እንደሚገባ ተሰምሮበታል፡፡ ከህወሀት፣ ከቤንሻንጉል ጉምዝ ታጣቂዎች፣ ከጋምቤላ ነጻነት ግንባር እና ከሌሎችም ጋር የተደረጉ የሰላም ስምምነቶች እንደ መልካም ተሞክሮ ተወስደው ሌሎች አለመግባባቶችም በዚሁ ረገድ በሰላማዊ መንገድ መፈታት እንዳለባቸው አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ የሰላማዊ ውይይት፣ ንግግር እና ድርድር አስፈላጊነት እና ቀዳሚ ተመራጭነት እንዳለ ሆኖ የሚከፈቱ የሰላም በሮችን በመዝጋት እና የመንግስትን ህግ የማስከበር ሉአላዊ ስልጣን በመዘንጋት ሰላም እና ጸጥታችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ አፍራሽ ሁኔታዎች ሲከሰቱ በማያሻማ ሁኔታ ህግ የማስከበር እርምጃ በመዉሰድ የህዝቡን ሰላም ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑ ተሰምሮበታል፡፡
ከሰላም እና ጸጥታው በሚወዳደር ደረጃ የህዝባችን ዋና ችግር ሆኖ በውይይት መድረኮቹ ላይ የተነሳውና በጥልቀት የታየው ጉዳይ የኑሮ ውድነት ጉዳይ ነው፡፡ እርግጥ አለማችን አሁን ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ በሀገራችን ላለው የኑሮ ውድነት ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ቢሆንም ሀገራዊው አሁናዊ መልክ ከአለማቀፋዊው ተለዋዋጭ ክብ እውነት ጋር ተዳምሮ ችግሩን ውስብስብ አድርጎታል፡፡ እንደ አለም ከአለም ጋር የምንቆምባቸው- የምንሰራቸው እና ለመፍትሄውም እንደ አለም አካል የምንባጅባቸው በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው እንደ ሀገር የሚሰሩ ወሳኝ የቤት ስራዎቻችን ላይም ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
ከነዚህም ውስጥ የኑሮ ውድነቱ በዋናነት ጡንቻውን ያፈረጠመውና መኖር- አለመኖር ከሚል የህልውና ጥያቄ ጋር ህዝባችንን ያፋጠጠው ምግብ ነክ ከሆኑ ምርቶች ረገድ በመሆኑ የሀገር ውስጥ የምግብ ነክ ሸቀጦች የዋጋ ጭማሪ ላይ በትኩረት እንዲሰራ ጽኑ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ በዚህም መሰረት ዋነኛዉ መፍትሄ ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ ልዩ ትኩረት ይደረግበታል፡፡ የሌማት ትሩፋት ይበልጥ መስፋት- የበጋ ስንዴ ስራችን ከእስካሁኑ በላቀ ማስፋፋት- የከተማ ግብርና ስራችንን ባህል የማድረግ ስራን በጥብቅ ድጋፍ እና ክትትል መምራት እንደሚገባ በውይይቶቹ ላይ መግባባት ተደርሷል፡፡
የንግድ ስርዓታችንን በማዘመን በኑሮ ውድነቱ ላይ ቤንዚን የሚያርከፈክፉ እና የህይወት ሸክም ካጎበጣቸው ደሃ ዜጎቻችን ትከሻ ላይ ሆዳቸውን መሙያ አሰስ ገሰስ ትርፍ የሚቃፍፉ ስርአት አልባ ደላሎችን አደብ ማስገዛት እንደሚገባ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ በአምራቹ እና በሸማቹ መሀል ያሉትን ህገወጥ ደላሎች በመቀነስ የኑሮ ውድነቱን ጫና የሚያቃልሉ እርምጃዎችም በቅርቡ መወሰድ ይጀምራሉ፤ የተጀመሩትም ተጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡
የስራ እድል ፈጠራ ጉዳይ በመድረኮቹ የተነሳ እና በስፋትም ውይይት የተደረገበት ዋና ርዕሰ ጉዳይ ነው፡፡ የስራ አጥነትን ችግርን ለመፍታት ኢኮኖሚዉን በተሟላ ሁኔታ ማንቀሳቀስ እንዳለ ሆኖ በራሳቸው ስራ የሚፈጥሩትን የማበረታታት- ለሌሎች የስራ እድል የሚፈጥሩትን በማትጋት እና ፈጣሪነትን የሚያከብር ስርአትም በመዘርጋት ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት መስራት እንደሚገባ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ተወዳዳሪ ክህሎት ብቻ ሳይሆን ተሻጋሪ አመለካከት ያላቸው ስራ ፈጣሪ ወጣቶችን ለመፍጠር ሁሉም ባለድርሻ አካላት የተናበበ እና የተጣጣመ አሰራርን በመዘርጋት ውጤታማ ስራ እንዲሰሩ በውይይቱ ላይ በአጽንኦት ተሰምሮበታል፡፡ ይህንንም እውን ለማድረግ ሁሉም አመራር በአትኩሮት እንዲሰራ ጥብቅ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ የስራ እድል ፈጣራ ስራዎችም ከጊዝያዊ የስራ ፈጠራ ባሻገር ዘላቂ- አዝላቂ- አንቂ እና አመርቂ እንዲሆኑ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
አገልግሎት እና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችም የውይይት መድረኮቹ አጀንዳዎች ነበሩ፡፡ በዋናነት የአገልጋዩ የአገልጋይነት ብያኔ ወይም መረዳት መታረቅ እንዳለበት ተነስቷል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን ጥብቅ የተጠያቂነት ስርአት መፍጠር እንደሚገባ በውይይቱ ተመላክቷል፡፡ በአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ውስጥ መልካሙን አገልጋይ ማመስገን እና ማጀገን እንዳለ ሆኑ ሊያገለግሉ ተመርጠው ሊገለገል የሚጋጋጡትን ሙሰኛ ሌቦች በቁርጠኝነት ለመዋጋት አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
ከመልሶ ግንባታ ጋር ተያይዞ በተነሳው እና በሰፊው በተንሸራሸረው አጀንዳ አንጻርም ብዙ ሃሳቦች ተመላልሰዋል፡፡ በግጭቶች እና በሌሎችም ሰበቦች ከቤት ንብረታቸው- ከቀኤ ሰፈቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀደመ ኑሯቸው የመመለስ ስራ ከእስካሁኑ ጥረት እና ፍጥነት በሚልቅ የተደመረ አስቸኳይነት ባለው የተናበበ ሁነት እንዲሰራ ተወስኗል፡፡ የተፈናቀሉ ወገኖቻችን በአስቸኳይ ወደየስፍራቸው ተመልስው ተማሪው ትምህርቱን- ገበሬው እርሻውን- ነጋዴውም ንግዱን… ወዘተ በመቀጠል ህይወት ወደ መደበኛ ምህዋሯ እንድትመለስ መረባረብ እንደሚገባ ተመልክቷል፡፡በተለያዩ ግጭቶች ውስጥ ሲሳተፉ የነበሩና የተከፈቱ የሰላም በሮችን ተጠቅመው ወደ ሰላማዊ ህይወት የሚመለሱ ዜጎችንም መልሶ የማደራጀት እና መደበኛ ህይወtቸውን እንዲመሩ የማብቃት ስራውም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ አበይት አጀንዳዎች ስኬታማ የሚሆኑበትን ሁሉም የሀገራችን ህዝቦች ከተናጠል ቡድናዊ እዉነታዎች ይልቅ የወል እዉነቶች ላይ የሚግባቡበትን ሁኔታዎች በማመቻቸት እና አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ በማድረግ የተራራቁ የሚቀራረቡባት- የተቀራረቡ የሚናበቡባት- የተናበቡ የሚግባቡት ሀገር እንድትኖረን ለማስቻል ሁሉም አካላት ላሰለሰ ጥረት እንዲያደርጉ ከስምምነት ላይ ተደርሷል- አቅጣጫም ተቀምጧል፡፡
ሁሉም ለዚህ ሁሉ ግባችን ስኬትም የውስጠ ጥራት ማረጋገጥ የውድ ሳይሆን የግድ የሆነ ቁልፍ ተግባር እንደሆነ በአትኩሮት ተመክሮበታል፡፡ በመሆኑም ፓርቲያችን ውስጡን እያጠራ ጉዞውን ይቀጥላል፡፡ ሲቀዘቅዝ በእጅ ሲያቃጥል በማንኪያ አይነት ወላዋይ አቋም ለሀገር እና ለህዝብ ከሚኖረው ትሩፋት ይልቅ የሚያኖረው እንቅፋት ይበዛል፡፡ እንደ ሀገር እና እንደ ህዝብ ያስመዘገብናቸው ድሎች እና ያመጣናቸው ለውጦች በተአምር የተገኙ ትሩፋቶች ሳይሆኑ በጠንካራ ስራና በመራር ትግል ያመጣናቸው የተደመረ ጥረት ውጤቶች ናቸው።
የሀገራችንን የችግር ቋጠሮ ለመፍታት የምናደርገው ጥረት ሁለት ወደ ፊት አንድ ወደ ሗላ እየተንገዳገደ የተቸገርንበት አንዱ ምክንያት የገባነውን ጽኑ ኪዳን በዘነጉ የብልጽግና አመራሮች ድክመትም ጭምር እንደሆነ ይታመናል፡፡ በመሆኑም ሁለት እግር አለን ብለው ሁለት ዛፍ ላይ የሚወጡ - የቤታቸውን ፍሪዳ ንቀው የጎረቤትን ትርፍራፊ የሚቀላውጡ ፣ ለጎረቤት እርግዝና በቤታቸው የሚያምጡ እና የድል ገድ ወዴት እንደዞረች አጢነው ከድል አድራጊ ለመጃመል ማካፈያ ላይ ቆመው ከዚያም ከዚያም የሚማትሩ ሰርጎ ገቦች በፖለቲካ ጉዟቸን ውስጥ ጥለው ያለፉትን ጠባሳ እና የፈጠሩትን ምስቅልቅል በውል በመረዳት ፓርቲያችን በመርህ ላይ በተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ትግል በማድረግ ራሱን ከሰርጎ ገብነት እያጠራ መሄድ እንዳለበት መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

(አዲሱ ረጋ ቂጤሳ)

Post a Comment

0 Comments