በታሪክ አዙሪት የተጠመደ ትውልድ


                                    አቶ ስብሃት ነጋ(አቦይ ስብሃት) የኦነግ ታጣቂዎችን ተቀብለው ምሳ ሲጋብዙ

በኢህአፓ "ዘመን"የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ነበርኩ።የፖለቲካን ትርጉም በቅጡ የማንረዳ ወጣት ተማሪዎች ሳንቀር የኢህአፓ አጨብጫቢ እንድንሆን በግልፅም በስውርም ግፊት ይደረግብን እንደነበር አስታውሳለሁ።በዚህ ምክንያትም የኢህአፓን የቅስቀሳ ልሳን(ዴሞክራሲያ) በስውር መበተን÷መፈክሩንም ጨለማን ተገን አድርገን በቀይ ቀለም በየግድግዳው ላይ መፃፍ÷መዶሻና ማጭድ የተሳለበት ቀይ ጨርቅ በኤሌክትሪክ ምሰሶ ላይ ሳይቀር ማንጠልጠል ...የጀብድ ስራችን ሆነ።ከዚያም አልፎ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር የት/ቤታችንን የሳር ክምር በክብሪት ማቃጠላችንን ዛሬ ሳስበው ያሳዝነኛል።በኛ የጅል ፖለቲካ "ደርግን መጉዳታችን"ነው።በየግድግዳው ከምንፅፋቸው መፈክሮች ዋነኞቹ "ጊዜያዊ ህዝባዊ መንግስት ይቋቋም÷ደርግ ፋሽስት ነው÷ጭቁኑ ህዝብ ያቸንፋል..."የሚሉት አይረሱኝም።ኢህአፓ በሌላ ክንፉ ነፍሰገዳይ ስኳድ ነበረው።በዚህም የከተማ ውስጥ ነፍስ ግድያን አፋፋመ።ንፁሀን ዜጎችና የሠራተኛ ማህበራት መሪዎች ሳይቀሩ"የደርግ ባንዳዎች"እየተባሉ በጠራራ ፀሐይ ይረሸኑ ነበር።የደርጉ ሊቀመንበር መንግስቱ ኃይለማሪያም ሳይቀሩ ዘጠኝ ጊዜ የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸው ተርፈዋል።ይህ አሳዛኝ ሁኔታ "ቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር"የሚል መጠፋፋት ወልዶ የወጣቶችና የምሁራን ደም ፈሰሰ።በመጨረሻም የኢህአፓው ቀንደኛ መሪ ብርሐነመስቀል ረዳ ወደትግራይ ለመሸሽ ሙከራ ሲያደርግ ወረኢሉ ውስጥ በገበሬዎች ከመገደሉ ባለፈ ሌሎቹ አንድ ትውልደ ወጣት አስፈጅተው በባሌም በቦሌም ወደ ስደት ፈረጠጡ።
                                    ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ

የዛሬዎቹ ዘረኞችና ፅንፈኞች ከታሪክ ባለመማር ትውልዱን ወደእርስ በእርስ ፍጅት ለማስገባት አቅላቸውን ስተው እየወተወቱ ነው።በኢህአፓ"ጊዜያዊ ህዝባዊ መንግስት ይቋቋም"መፈክር ምትክ "የሽግግር መንግስት ይቋቋም "እያሉ ነው።በኢህፓ ነፍሰገዳይ ስኳድ አምሳያ ሸኔና ፋኖ የሚል ጨካኝ ነፍሰገዳይ ቡድኖች ንፁሀንን እየገደሉና እየዘረፉ ነው።እጅግ የሚያስቆጨው ነገር ይህን ትውልድ በታሪክ አዙሪት ውስጥ አስገብተው ሊያፋጁት ዕረፍት ያጡት አንዳንዶቹ የኢህአፓው ዘመን ተዋናዮች ናቸው።ትውልድ በማስፈጀት የሚታወቁት አዛውንቶቹ እነሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ በስደት አገር በሰላም እየኖሩ "በአጭር ጊዜ አራት ኪሎ እንገባለን"በሚል ቅዠት በደም እየነገዱ ነው።በእርግጥ ብዙ በዘር ጥላቻና በአመፅ ርሀብ የታመመ መንጋ ስላለ ኪሳቸው በዶላር ሊያብጥ ይችላል።ሰሞኑን አሜሪካ ውስጥ የሰበሰቡት ዶላርም ይህንኑ ያረጋግጣል።የሞራልና የስነምግባር ውዳቂ የዩቲዪብ ነጋዴዎችም በጩኸትና በሀሰት ወሬ ፈጠራ እያገዟቸው ነው።ነፍስ ግድያውንም ጀምረውታል።ይህ ነፍሰገዳይ ቡድን ተጠራርጎ መሸነፉና ኢትዮጵያም ዛሬም እንደልማዷ አሸንፋ መውጣቷ ግን የማይቀር ነው።ለዚህ ታሪክ ምስክር ነው።

(በዓለምነው አበበ)

ከአዘጋጁ!
አዲሱ ትውልድ የቀድሞውን ሁኔታና ታሪክ ማወቅ ይገባዋል፤ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ የቀድሞውን እውነተኛ ታሪክ የሚያውቁ ምሁራንና ዜጎች ለአዲሱ ትውልድ ጽፈው ሲያቀርቡ ብቻ ነው በእርግጥ በማህበራዊ ሚዲያዎች ተጽዕኖ ምክንያት ሰዎች ብዙ ከማንበብ ተገድበዋል የሚል ጥርጣሬ አለ፤ ነገር ግን ሁሉም አያነብም ማለት ተገቢ አይደለም የሚያነቡና ታሪክን የሚመረምሩ ዜጎች ሊኖሩ ይችላሉ
ስለዚህ ከላይ የቀረበውን ጽሑፍ ዓይነት መልዕክት የያዘ ጽሑፍ ለአዲሱ ትውልድ ማቅረብ የምትፈልጉ ወገኖች በአፋን ኦሮሞና በአማርኛ brehuri1@gmail.com ብትልኩልኝ በዚህ ብሎግ ላይ እንዲወጣላችሁና ለብዙዎች እንዲደርስ ማድረግ እችላለሁ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይም አንባቢዎች እንዲያገኙት አደርጋለሁ እናንብብ! እንፃፍ!

Post a Comment

0 Comments