በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያለው የፅንፈኞች እንቅስቃሴ ስጋት ወደማይሆንበት ደረጃ ደርሷል፡- ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ኃይሎች አሁን ላይ ስጋት ወደማይሆኑበት ደረጃ መድረሳቸውን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ከመከላከያ ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በሁለቱ ክልሎች ተከስተው የነበሩ የፀጥታ ችግሮችን የመከላከያ ሰራዊቱ ጥበብ በታከለበት ወታደራዊ እንቅስቃሴ እየቀረፈ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢታማዦር ሹሙ በአማራ ክልል የህዝቡን የመብት ጥያቄ ካባ በማድረግ ፍላጎቱን በኃይል ለማሳካት የተንቀሳቀሰው ኃይል ላይ እየተወሰደ ባለው እርምጅ አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል፡፡
በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሆነው የሀሰት ፕሮፖጋንዳ የሚነዙ ኃይሎች፤ ለሀገርና ለህዝብ ሲል ውድ ህይወቱን እየከፈለ ሰላም የሚያረጋግጠውን ሰራዊት ስነ-ልቦና ያልተረዱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ሰራዊቱ በተሰማራባቸው የግዳጅ ቃጣናዎች ሁሉ ህግ-መንግስታዊ ተልዕኮውን በአስተማማኝ እየተወጣም ነው ብለዋል፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ የፅንፈኞች የሀሰት ፕሮፖጋንዳን የተገነዘበው ህዝባችን ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን በመሆን ለሰላሙ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በሀሰተኞች ሴራ ተታለው ከፅንፈኞች ጋር የተሰለፉ ወጣቶች በሰላማዊ መንገድ ወደህዝቡ እንዲመለሱም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
መከላከያ በ2015 የበጀት ዓመት ተልዕኮውን በሚገባ መፈፀሙን የገለጹት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ ለቀጣዩ በጀት ዓመትም እንደተቋም የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ከምን ጊዜውም በላይ ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡
0 Comments