በቆሞ ቀሮች ግትርነት ሕዝብ ተጠቃሚ ሊሆን አይችልም!



ፊንፊኔ #Ethiopia ጥቅምት 18/2016(YMN) እነ መስመር ኃይልና ሕዝቢ ጉልበትና “ሕወሃትና የትግራይ ሕዝብ አንድ ነው” የምትል ባዶ መፈክራቸውን የተው አይመስልም፤ቆሞ ቀሮቹ በትግራይ ሕዝብ ስም ምን ያላደረጉት አለ?ስፍር ቁጥርስ ይኖረው ይሆን?
“ሕወሃትና የትግራይ ሕዝብ አንድ ነው”ሲሉ ኖረው የትግራይ ወጣቶችን በሃሰተኛ ፕሮፓጋንዳቸውና በሸመቱላቸው ሃሺሽ አናውዘው እንዲያልቁ ካደረጉ በኋላ አሁንም የማያርፉ መሆናቸውን የሚያመለክት መረጃ ከወደ ትግራይ መቀሌ ሽታው መሰንፈጥ ጀምሯል
ለምን?ብለን እንጠይቅ! ለእነርሱ ስልጣን ሲባል የትግራይ ክልል ሕዝብ የማይሆነው የለም፤አድርግ ያልነውን ሁሉ ያደርጋል ብለው ያምናሉ፤ምክንያቱም እነርሱ ሲዘምሩ እንደኖሩትና አሁንም እንደሚያምኑት ሕወሃትና የትግራይ ሕዝብ የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸውና
ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በኋላ የተመሰረተው ጊዜያዊ የትግራይ ክልል መንግስት ሳይፈቅድና ሳያውቅ መቀሌ ውስጥ ለብቻቸው ዶልተው የሚሰበሰቡበት ምክንያት ግልጽ ነው፤ቀድሞውንም በአቅመ ቢስነታቸው ምክንያት ምንም ማድረግ ስለማይችሉ ነው እንጂ የክልሉን ጊዜያዊ የሽግግር መንግስት ልባቸው አልተቀበለውም፤እምቢ ብሏቸዋል
እንግዲህ እዚያው አስበው በለመዱትና በኖሩበት የሴራ ሽረባ የጎነጎኑት ነገር አለ ብለን እንድንጠረጥራቸው የሚያደርገን የምናውቀው የኖሩበት ባህሪያቸው ነው፤የአስመሳይነት ባህሪያቸው ይታወቃልና የትግራይ ሕዝብ ግን ሊቀድማቸው ይገባል፤እነዚህ ሽማግሌዎች የሕወሃት ቁንጮዎች በጊዜያዊ የሽግግር መንግስት አስተዳደር ላይ ንቀት እንዳላቸው አሳይተዋል
ለመሆኑ የትግራይ እናቶች የልጆቻቸውን ሞት ከተረዱ ስንት ቀን ተቆጥሯል? ቆሞ ቀር ግትሮቹ ይህን የማሰብ ብቃት እንኳ የላቸውም!ይሉኝታም አልፈጠረባቸውም
በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች በጦርነት እንዲያልቁ ካደረጉ በኋላ አሁንም ቀሪው ሕዝብ እንዲሞትላቸው ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም፤ለእነርሱ ስልጣን ሲባል የትኛውም ጉዳት ቢደርስ ግድ እንደሌላቸውና ልበ ደንዳናነታቸውን አሁንም አሳይተዋል
በውጭ የሚገኘው ዳያስፖራ እንዳልበረደለት እየታየ ነው፤ምናልባት ቁንጮዎቹ ሽማግሌዎች ተስፋ ያደረጉት ይህን ኃይልና የአይዞ ባይ አጋሮቻቸውን ድጋፍ ሊሆን ይችላል
እንግዲህ ልብ ያለው ልብ ይበል! የትግራይ ክልል ሕዝብ ከደረሰበት አሳቃቂ ሁኔታ አደጋ ለመውጣት መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል!አለን አልሞትንም ባዮችን ከአሁኑ ጨከን ብሎ ፊት ካልነሳቸው እነዚህ ይሉኝታ ቢሶች የማያደርጉት ነገር የለም
ለዚህ ደግሞ ያለፉበት ሂደትና ተፈጥሯቸው ያስገድዳቸዋል፤የለውጡን ኃይል በማደናቀፍ የክልሉን የሽግግር ጊዜ መንግስት መዋቅር ሽባ በማድረግ በጣም ወደምትጣፍጣቸው ስልጣን ለመመለስ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፤ምናልባት “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው”በሚለው መሰረት የከሰረውን የአካባቢውን የፖለቲካ ነጋዴና ተላላኪ ሁሉ በመጠቀም መንቀሳቀሳቸው ስለማይቀር የትግራይ ሕዝብ ዳግም ላለመጎዳት አስቀድሞ ፊት ይንሳቸው!
ጊዜያዊ የሽግግር መንግስቱ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ ምን ብለዋል? ቀጥሎ መግለጫቻው ተያይዟል ያንብቡ!
" መንግስት የማያውቀው ፤ የህዝብ ሃብት በማባከን ከቀበሌ እስከ ዞን ስብሰባ መጥራት ምክንያቱ ግልፅ አይደለም " - አቶ ጌታቸው ረዳ
በትግራይ የተጀመረው ህግ የማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕረዚደንት አቶ ጌታቸው ረዳ ገለፁ።
ፕሬዚደንቱ ጥቅምት 16 /2016 ዓ.ም በፅህፈት ቤታቸው በኩል ባወጡት መግለጫ ፤ "የተሰው ታጋዮች መርዶ በተነገረበት ማግስት ያሉ የመንግስት ስራዎች ወደ ጎን በመተው መንግስት የማያውቀው የህዝብ ሃብት በማባከን ከጥቅምት 14/2016 ዓ.ም ጀምሮ ከቀበሌ እስከ ዞን ስብሰባ መጥራት ምክንያቱ ግልፅ አይደለም " ብለዋል።
የሰብሰባው ዋነኛ ተሳታፊ በየደረጃው ያሉ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊዎች ሲሆኑ ፣ መንግስትና ህዝብ የሰጣቸው ሃላፊነት ወደ ጎን በመተው በራሳቸው መንገድ በሄዱ ሃላፊዎች እርምጃ ተወስዷል፤ የተጀመረውም ህግ የማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።
እነዚህ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊዎች ህዝብ በማስተባበር ያጋጠመን ችግር መፍታት ትተው ወደ መቐለ በመምጣት መንግሰት የማያውቀው ስብሰባ ማካሄድ አላማው ግልፅ እንዳልሆነ ፕረዚደንት ጌታቸው ረዳ ጨምረው ገልፀዋል።
ለስብሰባው በተደረገው ጥሪ " በአንዳንዱ አከባቢ ስንቃቸውን ይዘው እንዲመጡ " መነገሩን የገለፁት አቶ ጌታቸው ፤ የመንግስት አሰራር ጥሰው በተገኙ ሃላፊዎች በተወሰደው እርምጃ ምክንያት የአመራር ክፍት እንዳይፈጠር ማስተካከያ እርምርጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።
" አሁን ያጋጠመው ችግር ለማስተካከል ሰራዊቱ ፣ ድርጅቱ ህዝቡ በማንቀሳቀስ ይሰራል " ያሉት ፕረዚደንቱ " ሁሉም ነገር በህግና አሰራር ብቻ መከናወን ይገባል " ብለዋል።
" በየደረጃው የሚገኝ የመንግስት አካል ህዝብና መንግስት የሰጠው ሃላፊነት በአግባቡ በመወጣት ህዝብ የሚጠቅም ስራ መስራት አለበት " ያሉት አቶ ጌታቸው ረዳ " ይህንን ለማደናቀፍ በሚሞክር ማንኛውም አካል ጥንካራ ህግ የማስከበር እርምጃ ይወሰዳል " ማለታቸው የጊዜያዊ አስተዳደሩም ፕረዚደንት ፅህፈት ቤት መግለጫ በመጥቀስ የቲክቫህ ኢትዮጵያ የመቐለ ቤተሰብ ዘግቧል።
ፕሬዚደንት ጌታቸው ረዳ ጥቅምት 15/2016 ዓ.ም ጊዚያዊ አስተዳደሩ በማያውቀው እንቅስቃሴ ተገኝተዋል ያሉዋቸውን 6 የክልሉ ዞኖች የህዝብ ግንኙነት ሃላፊዎች በደብዳቤ ከስራ አሰናብተዋቸዋል።

Post a Comment

0 Comments