የዳሬ ሰላም የሰላም ውይይትና ተስፋው



ፊንፊኔ #Ethiopia ሕዳር 05/2016(YMN) በኢትዮጵያ መንግስት ተወካዮችና ራሱን “የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት” ነኝ ብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን መካከል በታንዛኒያ ዳሬ ሰላም ሰሞኑን የተጀመረው የቀጣይ ዙር የሰላም ውይይት በመካሄድ ላይ ነው የሚሉ መረጃዎች በመውጣት ላይ ይገኛሉ

“የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት” ነኝ የሚለው ታጣቂ ቡድን ከትናንት በስቲያ የሰላም ውይይቱ በታንዛኒያ ዳሬ ሰላም በመካሄድ ላይ እንደሆነ  በጽሑፍ ባሰራጨው አጭር መግለጫ ያስታወቀ ሲሆን በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ግን ጉዳዩን በተመለከተ እስከ አሁን የወጣ መረጃ የለም

የኢትዮጵያን መንግስት በመወከል በሰላም ውይይቱ ላይ በመሳተፍ ላይ የሚገኙት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዴዮን ጢሞቲዎስ መሆናቸው ተነግሯል

ቀደም ሲል እዚያው ታንዛኒያ በተካሄደ የአንደኛ ዙር የሰላም ውይይት የታጣቂ ቡድኑ በኢትዮጵያ መንግስት ተቀባይነት የሌለው “የሽግግር መንግስት ይቋቋም” ብሎ በያዘው አቋም ምክንያት ቀሪ ጉዳዮች በቀጣይ ይታያሉ በሚል ስምምነት ቀጠሮ ተይዞ ውይይቱ እንደተጠናቀቀ ይታወቃል

የአንደኛው ዙር የሰላም ውይይት ያለ ውጤት የተጠናቀቀው “የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት” ነኝ የሚለው ታጣቂ ቡድን ተወካዮች ሁሉም ነገር እንደተጠናቀቀ አድርገው በያዙት የተሳሳተ መረጃ ምክንያት እንደሆነ የመጀመሪያው ዙር የሰላም ውይይት ያለ ምንም ውጤት ከተጠናቀቀ ወዲህ የወጡ መረጃዎች ጠቁመዋል

መንግስት “ሸኔ” እያለ የሚጠራውና በተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ የአሸባሪነት ስያሜ የተሰጠው ቡድን ባለፉት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የደፈጣ ጥቃት ሲፈፅም የቆየ መሆኑ ይታወቃል

በቡድኑ ጥቃት ምክንያት ነዋሪዎች  ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን፤  የበርካቶች ሕይወት ማለፉንና ንብረት መውደሙን የሚያመለክቱ መረጃዎች ቀደም ሲል በተለያዩ ወቅቶች ተሰራጭተዋል

በኦሮሞ ሕዝብ ስም የሚንቀሳቀሰው ሸኔ ለውጡን ለመቀልበስ ከሚንቀሳቀሱ ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች ጋር በመቀናጀት እታገልለታለሁ በሚለው የኦሮሞ ሕዝብና ሌሎች ወገኖች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያደርስ የቆየ እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በአሸባሪ ቡድኑ ላይ በተለያዩ ወቅቶች በወሰደው እርምጃ በርካታ የታጣቂ ቡድኑ አባላት መደምሰሳቸውንና በርካቶችም መማረካቸውን በተለያዩ ወቅቶች ባወጣው መረጃ አረጋግጧል

ሰሞኑን ሁለተኛው የሰላም ውይይት በዳሬ ሰላም እየተካሄደ መሆኑ ከተሰማ ወዲህ አንዳንድ ቡድኖችና ግለሰቦች በሰጡት አስተያየት “ከሸኔ ጋር የሰላም ውይይት መካሄድ የለበትም”ሲሉ በመከራከር አቋማቸውን ገልፀዋል

የተለያዩ ምክንያቶችን በመጥቀስ የሰላም ውይይቱን በመቃወም ላይ የሚገኙ  ይሎች ዋነኛ ስጋት በግጭቱ ምክንያት የሚያገኙት ገቢ የሚቋረጥባቸው በመሆኑ እንደሆነ የሰላም ውይይቱ በመልካም ውጤት እንዲጠናቀቅ በሚሹ ወገኖች እየተሰጠ ያለው አስተያየት ጠቁሟል

 

 

Post a Comment

0 Comments