የእርስ በርስ የግጭት ምዕራፍን ለመዝጋት ሁሉም ዜጋ እንዲረባረብ ጥሪ ቀረበ

  



ፊንፊኔ #Ethiopia ሕዳር 02/2016(YMN) የእርስ በርስ የግጭት ምዕራፍን ለመዝጋት ሁሉም ዜጋ እንዲረባረብ እና ለሰላሙም በአንድነት ዘብ እንዲቆም የአማራ ክልል ጥሪ አቅርቧል፡፡

የአማራ ክልል በክልሉ ወቅታዊ የሰላም ጉዳይ ያስተላለፈው ሙሉ መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧል፡፡

ሰላም እስትንፋሳችን ነው!

ሰላም የዛሬውም ሆነ የወደፊቱ የትውልድ የኅልውና መሠረት ነው። የዛሬ አሻራ የሚኖረው በዛሬ ሰላማችን ልክ ነው። የትኛውም አካል ሰላም ከሌለ ስለዛሬ መኖሩን እንጂ ስለነገ እድገትና ልማት ሊያስብ አይችልም። የነገ መሠረትና ትርፍ የሚገኘው ከግጭትና ጦርነት ሳይሆን ከሰላም እንደሆነ በግጭትና በእርስ በርስ ጦርነት ያለፉ ሀገራት ታሪክን ማየት በቂ ነው፡፡ በዓለማችን የግጭት አውድማ ከሆኑት እንደ ሊቢያ፣ ሶርያና የመን የመሳሰሉ ሀገራት በሰላሙ ጊዜ የነበራቸው ገጽታና አሁን ያሉበትን ደረጃ ብቻ ማየት ለእኛ ከበቂ በላይ ትምህርትና ምስክር ነው፡፡

ይህም የሚያስረዳን የአገራቱ ሕዝቦች የሰላምን ዋጋ ቀድመው በውል ተገንዝበው፣ በእኩልነት፣ በመቻቻል፣ በአንድነትና በትብብር ከመኖር ይልቅ ወደ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በመግባታቸው የመጣ መዘዝ መሆኑን መናገር ለቀባሪ ማርዳት ነው።

ስለሆነም ሰላም በሌለበት ስለነገ እድገትና ልማት ይቅርና ስለዛሬ መኖርን ማሰብ አይችልም፡፡ ከመተባበር ይልቅ መነጣጠልን፣ ከመደማመጥ ይልቅ መነቃቀፍን፣ ከመነጋገር ይልቅ መቃቃርን፣ ከአብሮነት ይልቅ ልዩነትን፣ ከትብብር ይልቅ የኔ ባይነትን፣ ሰላምን ከማስፈን ይልቅ በስሜት መነዳትን መምረጥ ትርፉ ኪሳራ ጉዞውም የጉስቁል መሆኑን ያስረዳናል። ይህ መሰሉ ጉዞም የከፋና አሰቃቂ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ለዜጎች ሞት፣ ርሃብና እርዛት ይዳርጋል፡፡

በተለይም በአንድ ሕዘቦች መካከል በሚደረግ ግጭት ከቶ አሸናፊና ተሸናፊ ሊኖር አይችልም፡፡ በወንድማማች መካከል የሚደረግ መገዳደል ለትውልድ የሚተርፍ ቂምና ቁርሾ ጥሎ ከማለፉ ባሻገር ባለድል የሚሆን ወገን የለም። አይኖርም። ሠላማዊ የነበረ ሀገር ወይም ክልል ከመበጥበጥና ዜጎች ለሞትና ለእንግልት ከመዳረግ፣ የሀገርን ኢኮኖሚ ከማድቀቅና ከማውደም የዘለለ ይህ ነው የሚባል የሚያመጣው ለውጥም የለም፡፡ ሊኖርም አይችልም። በሕዝቦች መካከል የማይሽር ጠባሳ ከማሳረፍ ሌላ አሸናፊና ተሸናፊ ሊኖረው አይችልም፡፡

በእኛ ሀገር እየሆነ ያለውም እውነታም ይሔው ነው። እንደሕዝብ ከዚህ በመማር ለጋራ ጥቅምና እድገት የሚበጀውን ሰላማዊ መንገድ መምረጥ ይኖርብናል፡፡

ሰላም ከሌለ እድገትም አይኖርም፤ የወደፊት ተስፋም ፈጽሞ አይታሰብም፡፡ ወልዶ መሳም፣ ነግዶ ማትረፍ፣ ሰርቶ መየቀይ የለም። በሰላም ወጥቶ መግባትም ሊኖር አይቻልም። ዜጎች ስለነገ እድገትና ልማት ማስብ ይቅርና ስለዛሬ መኖር ሊያስቡ አይችሉም፡፡

በተጨማሪም ከሠላምና መረጋጋት ውጭ የዛሬው ትውልድ አሻራና የነገው ትውልድ መሠረት የሚሆን ልማት ብዙም ትኩረት አያገኝም፡፡ ሠርቼ እለወጣለሁ የሚል ዜጋ አይኖርም፡፡ ጦረኛና ቀማኛ ዜጋን እንጂ በጦርነትና በግጭት አምራች ዜጋን ማፍራት አይቻልም፡፡

በመሆኑም ባለፉት ዓመታት ያጋጠሙንን ውስብስብ ችግሮች ጥበብና ትግስት በተሞላበት መንገድ እየተሻገርን መጥተናል። በአሁኑ ሰዓት ከሁሉም በላይ እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር ሰላምና አንድነት ከሚያስፈልገን ወሳኝ ወቅት ላይ መሆናችንን መረዳት ያስፈልጋል፡፡

ሰላም የሰው ልጅ የኅልውና መሠረት ነው ስንል የዋጋ ተመን የሌለው በመሆኑ ነው። ሰላምን በገንዘብ አይሸጥም፤ አይለወጥም። ስለሰላም አስፈላጊነት ደግሞ ከእኛ በላይ አስረጅም ሆነ ምስክር ሊኖርም አይችልም። የእኛ ሰላምም በጃችን ነው፡፡ የሰላም ባለቤትም መላ ሕዝቡ ነው፡፡

ዘላቂ ሰላም የማስፈን ሒደት በመንግሥትና በጸጥታ መዋቅር ብቸኛ ፍላጎት የሚረጋገጥ ሳይሆን ሁሉም ሕዝብ የራሱን፣ የአካባቢውንና የቤተሰቡን ሰላም መጠበቅ ይጠይቃል፡፡ ያን ማድረግ ሲቻል ራስ ወዳድና በግጭት የሚነግዱ ጥቅመኞችን አደብ ማስያዝ ይችላል፡፡ ከዚያ ውጭ እርስ በርስ መናቆር፣ መገዳደል ለከፋ ውድቀትና ኪሳራ ከመዳረግ ውጪ የሚገኝ የሕዝብ፣ የቡድንና የግል ጥቅም፣ ትርፍና ተስፋ የለም፡፡ ሊኖርም አይችልም።

"ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ" እንዲሉ በሕዝብ ስም ሌት ተቀን ያለመታከት አጥብቀው እየማሉ፤ የሕዝብ መገልገያ ንብረት በአደባባይ የሚዘርፉ፣ ሲያሻቸው የሚያወድሙ፣ የሚያቃጥሉ፤ ንጹሃንን የሚገሉ በስማቸው መጠራት አለባቸው። የአማራን ሕዝብ የቆየ እንቁ እሴቱንና ባሕሉን እየሸረሸሩና እያጠለሹ፤ ያለስሙ ስም፤ ያለግብሩ ግብር እየሰጡ የታሪክ ተወቃሽ ከመሆን ባሻገር የሚያስገኘው ትርፍ አይኖርም። የሕዝብን ሃብትና ንብረት እየዘረፉ አትራፊ፤ እየቀሙ ጠቃሚ፣ እያቃጠሉና እያወደሙ አልሚ፣ በስሙ የሚምሉበትን ሕዝብ እየገደሉ ጠበቃ ለመምሰል የሚሞከሩ አካላት በቃችሁ መባል አለባቸው።

የአማራ ክልልና መላ ሕዝቡ በሰሜኑ ጦርነት ከፍተኛ ማህበራዊና ቁሳዊ ኪሳራ ደርሶበታል። ለኢኮኖሚ ቀውስም ዳርጎት አልፏል። በጦርነቱ በርካታ ወገኖች ለሕዝብና ለሀገር ኅልውና ሲሉ ሕይወታቸውን ገብረዋል። አብዛኞቹም የሞቀ ቤታቸውንና ቀያቸውን ትተው ተፈናቅለዋል። የተፈናቀሉ ዜጎች በተሟላ መንገድ ተመልሰው የቀድሞውን ማሕበራዊ ሕይወት አልጀመሩም። የነበረው ጦርነት ለመመጽዎት እጃቸው የማይሰስቱ የነበሩ ወገኖቻችንን ተመጽዋች አድርጓል። እጃቸው ደርቆ የሰው ፊት አይተው ማያውቁ ዜጎች የመንግሥትን እርዳታ ተመልካች አደርጓል። በዚህ መለስ የማይባል በርካታ ተቋማት፣ መሠረት ልማት አውድሞ አልፏል።

ይህ በእንዲህ እያለ "በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ" እንዲሉ ክልሉ ከሰሜኑ ጦርነት በውል ሳያገግም ለዳግም የእርስ በርስ ግጭትና ጦርነት ተዳርጓል። የተከሰተው ግጭት ክልሉን ለከፋ ጉስቁልና የዳረገ፤ የበርካቶችን ሕይወት የቀዘፈውና ቀላል የማይባል የንብረት ውድመትና የኢኮኖሚ ኪሳራ እያሳደረሰ ነው። ይህ የእርስ በርስ ግጭት እንዲቆምና ዳግመኛም እንዳይከሰት አሁንም የሁሉንም ብርቱ ትግልና ጥንቃቄ ማድረግን ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ የክልሉ ሕዝብ፣ ምሁራንና የፖለቲካ ተዋናኞች ወሳኝ ሚና መጫወት አለባቸው፡፡

ሁሉም ዜጋ ለሰው ሕይወት መጥፋት፣ ለንብረት ውድመትና ለዜጎች መፈናቀል ምክንያት ከሚሆኑ የተለያዩ ድርጊቶች ሊቆጠብ ይገባል፡፡ ዜጎችን በማንነት፣ በብሔር፣ በሃይማኖትና በፖለቲካ ልዩነት ለማጋጨት የሚደረጉ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻዎችም መወገዝ ይኖርባቸዋል፡፡ እንዲህ አይነት ድርጊቶችንም ሕዝቡ ነውር እና ሀገር አፍራሽ መሆናቸውን ማጋለጥ ይገባል።

ሕዝብን ለማቀራረብ እንጂ ለማራራቅ የሚጻፉ ጽሁፎች፣ በግለሰብም ይሁን በቡድን ደረጃ የሚነገሩ

ሐሰተኛና ኃላፊነት የጎደላቸው ንግግሮችና ሐሳቦች ከግለኝነት የመነጩ የጥፋት አጀንዳዎች መሆናቸውን ማጤን ያስፈልጋል፡፡ ለሁሉም ነገር ወሳኙ ሕዝብ በመሆኑ እንደዚህ ዓይነት ማደናገሪያ የሚዲያ ፕሮፖጋንዳዎች ወደጎን በመተው አንድነቱንና ሰላሙን ሊያጠናክር ይገባል፡፡

ልዩነትና ጥላቻን በማር በመለወስ ሌት ተቀን የሚታትሩ ጥቅመኛ የውስጥና የውጭ ጠላቶች የመጨረሻ ውጤታቸው ዜጎችን ማቅ ማልበስ፤ የሀገርንና የሕዝብን የቆየ እሴት እና መልካም ስም ማጠልሸትና የጥፋት አውድማ ማድረግ ነው። በግጭት እሳት ሕዝብን እየማገዱ፣ በዜጋ ስቃይና ሞት መቀለድ ደግሞ ታሪክ አይሽሬ በደልም ነው። ስለሆነም የእርስ በርስ የግጭት ምዕራፍን ለመዝጋት ሁሉም ዜጋ ሊረባረብ ይገባል። ለሰላሙም በአንድነት ዘብ መቆም አለበት።

በሰላም ውስጥ ሁሉም አለ። ያለን ሃብት ከበቂ በላይ ነው። ሰላም ከሰፈነም የሌለን ነገር የለም፡፡ ከሰላም እጦት ተጠቃሚ ሊሆን የሚችል አካል ስሌለ ሁሉም ዜጋ ሰላምን ሊጠብቀው እንደሚገባ አጠያያቂ ሊሆን አይችልም፡፡ ያለ ሰላም ቀባሪም ሆነ ጧሪ፤ ኑዋሪም ሆነ አኗኗሪ አይኖርም፤ መኖርም አይችልም። ሰላም ልክ እንደ እስትንፋሳችን ነው፤ በአንድነት ቁመን ልንጠብቀውና ልንከባከበው ይገባል።

ሰላማችን ለሁለንተናዊ ብልጽግናችን መሠረት ነው

Post a Comment

0 Comments