ፊንፊኔ ታህሳስ 19/2016(YMN) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የሲቪል ሰርቫንት ተቋማትን መገንባት አካል ነው፤ የተገልጋዩን እርካታ ለማሻሻል ወሳኝ ነው ያለውን የመንግስት ሰራተኞች የብቃት ምዘና ፈተና የፊታችን ቅዳሜ እንደሚሰጥ ገለጸ
ፈተናው የስነ ምግባርና የክህሎት ክፍተቶችን ለመለየት የሚካሄድ የምዘና አካል እንደሆነ የከተማው አስተዳደር አስታውቋል
የምዘናው ፈተና ከዳይሬክተር እስከ ፈጻሚ ሰራተኞች ያሉትን የሚያካትት ሲሆን፤ በተሰማሩባቸው ስራዎች ተገቢውን እውቀት፣ ክህሎትና ስነምግባር አሟልተው የተገኙ ሰራተኞች በተወዳደሩበት ቦታ ይመደባሉ ተብሏል
በምዘናው በክህሎትና ስነ ምግባር አንጻር ክፍተት የተገኘባቸው ሰራተኞች በሚመጥኗቸው ቦታዎች በመመደብ ተገቢው የክህሎትና ስነ ምግባር አቅም ግንባታ ማሻሻያ ስልጠና እንደሚሰጣቸው ታውቋል
ማንኛውም ሰራተኛ አሁን ፈተናውን ቢወድቅ የአቅም ግንባታ ማሻሻያ ስልጠና ከተሰጠው በኋላ ድጋሚ የመፈተን እድል የሚያገኝ ሲሆን፤ የድጋሚ ፈተናውን ማለፍ ሳይችል ቢቀር "ጥቅሙ ተከብሮለት ይሰናበታል" ተብሏል
"በተለያየ መልኩ ውዥንብር በመፍጠር ሪፎርሙ እንዳይሳካ የሚፈልጉ ኃይሎች አሉ" ያለው የከተማ አስተዳደሩ፤ ”የሪፎርሙ አላማ ዘመናዊ በቴክኖሎጂ የታገዘ፣ የተገልጋዩን እርካታ ከፍ የሚያደርግ፣ የከተማዋን ቀጣይ እድገት ታሳቢ ያደረገ፣ ሲቪል ሰርቫንትና ተቋማትን መገንባት ብቻ ነው“ ብሏል
0 Comments