አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የጋራ ግብረ ሃይሉ አስታወቀ






 የዓድዋ ድል መታሠቢያ በዓልን ለማክበር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የጋራ ግብረ ሃይሉ አስታወቀ

128ኛው የዓድዋ ድል መታሠቢያ በዓልን ለማክበር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ፍፁም ሠላማዊ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሃይል አስታወቀ።
የፀጥታና ደህነት የጋራ ግብረ ሃይሉ የካቲት 23 ቀን 2016 ዓ.ም የሚከበረው 128ኛው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር ለማስቻል በወጣው የማስፈፀሚያ እቅድ ላይ በአዲስ አበባ ፖሊስ ውይይት አድርጓል።
በመከላከያ ዘመቻ ዋና መምሪያ የሀይል ሥምሪትና ክትትል መምሪያ ሃላፊ ሜጄር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው እንደገለፁት÷ የመላው ኢትዮጵያውያን በዓል የሆነው የዓድዋ ድል በዓል ሲከበር ምንም አይነት ስጋት እንዳያጋጥም የፀጥታ ሃይሉ ዝግጁ ሆኗል።
“የበዓሉ ተሳታፊዎች ፀብን ከሚያነሳሱ እና በዓሉን የማይገልፁ ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎችን ከመፈፀም ሊታቀቡ ይገባል” ብለዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው÷ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ታሪኩን በሚመጥን መልኩ ተገንብቶ በተጠናቀቀበት ወቅት መከበሩ የዘንድሮውን የዓድዋ ድል በዓልን ልዩ እንደሚያደርገው አንስተዋል፡፡
በዓሉ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተከብሮ እንዲውል አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁንም ነው የተናገሩት፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ÷ የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓልን ሊያውኩ የሚችሉ ሁኔታዎች እንዳያጋጥሙ ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን በማጥናትና በመለየት ችግሩን ለማስወገድና ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል ።
በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ የኦፕሬሽን ዋና መምሪያ ሃላፊ ምክትል ኮሚሽነር አበራ ሁንዴ÷ የዓድዋ ድል በዓል መከበርን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም ሁከት ለመፍጠርና የግል ፍላጎታቸውን ለማንፀባረቅ የሚሞክሩ አካላት በሚያጋጥሙበት ወቅት ለፀጥታ ሃይሉ በመጠቆም ህብረተሰቡና የበዓሉ ተሳታፊዎች የተለመደ ትብብራቸውን እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

Post a Comment

0 Comments