ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተሰጠ መግለጫ




ከትናንት ታሪካዊ ስህተቱ መማር የተሳነው ሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሓት) የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመጣስ ለአራተኛ ዙር ሕዝባችን ላይ ወረራ ፈፅሟል፡፡
ጀንበር ጠልቃ በወጣች ቁጥር ከጦርነት ውጭ ማሰብ የማይችለው የህወሓት ቡድን ከዉጭ እና ከዉስጥ ጠላቶቻችን ጋር ተናብቦና ተቀናጅቶ በርካሽ ፖለቲካዊ ብያኔና ፍረጃ በጊዜያዊ አሥተዳደሩ ካቢኔ አማካኝነት መጋቢት 16/2016 ዓ.ም የአማራ ክልል ተማሪዎችን መማሪያ መጽሐፍ እንደ ሰበብ ተጠቅሞ በይፋ ጦርነት ማወጁና መቀስቀሱ ይታወቃል፡፡
ይሁን እንጂ ይህን የመላ ኢትዮጵያ ጠላትና የደኅንነት ስጋት የሆነውን የህወሓት ቡድን ባለፉት ሦስት ዙሮች ከተደረገው ደም አፋሳሽ ጦርነት ትምህርት ሊወስድ ይችል ይሆናል በሚል ጭላንጭል ተስፋ የፌዴራል መንግሥት እጅግ እልህ አስጨራሽ ትዕግስት ተላብሶ ውይይቶች እንዲካሄዱ ተደጋጋሚ ጥረት ሲያደረግ ቆይቷል፡፡
የአማራ ክልል መንግሥትም በተደጋጋሚ ከትግራይ ጊዜያዊ አሥተዳደር ጋር በፌዴራል መንግሥት አማካኝነት ውይይት ለማድረግ በርካታ ሙከራዎች የተደረጉ ቢሆንም ህወሓት ይህን የሰላም አማራጭ ወደ ጎን በመተው የማንነት ጥያቄ ያለባቸውን የራያ አላማጣ፣ ራያ ባላ፣ ኦፍላ፣ ኮረምና ዛታ አካባቢዎች ላይ ወረራ ፈፅሟል፡፡
ህወሓት ወረራ የፈፀመባቸው የራያ አላማጣ፣ ራያ ባላ፣ ኦፍላ፣ ኮረምና ዛታ እንዲሁም የወልቃይት ጠገዴ እና ጠለምት አካባቢዎች የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት ከመፅደቁ በፊት በነበሩ አሥተዳደራዊ መዋቅርና አደረጃጀት በኀይል ጠቅልሎ ከመውሰድ ጀምሮ የዘር ማጥፋት ወንጀል እስከመፈጸም ድረስ አሰቃቂ ጥፋት የፈጸመባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡ እነዚህ አካባቢዎች ስቃይ በተሞላበት ችግር ውስጥም ኾነው በወቅቱ ለነበረው መንግሥት የማንነትና ራስን በራስ የማሥተዳደር ጥያቄዎችን በማንሳት፣ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ሲጠይቁ የነበሩ መኾኑ በበርካታ ታሪካዊ ማስረጃዎች የተረጋገጥ ጉዳይ ነው፡፡
ተቸንካሪነት ዋና መለያ የኾነው የህወሓት የጥፋት ቡድን ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመውን አሰቃቂና ታሪክ ምንጊዜም የማይዘነጋው የባንዳነት ተግባር ተከትሎ በተቀሰቀሰው ጦርነት በመላ ኢትዮጵያዊያን እና በጀግኖች የፀጥታ ኀይሎች አማካኝነት የሽንፈት ፅዋን ከመጎንጨቱ ባሻገር የማንነትና የራስ አሥተዳደር ጥያቄ ያለባቸውን አካባቢዎች በጉልበት ተገፎባቸው የነበረውን ራሳቸውን የማሥተዳደር ነጻነት መቀዳጀት ችለዋል፡፡
ይሁን እንጂ ይህ ኹኔታ ያልተመቸው ተቸንካሪው የህወሓት ቡድን በሦስት ዙሮች ከተደረገው ጦርነት ማግሥት የፕሪቶሪያውን ስምምነት በማክበር በሀገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የድርሻውን ከመወጣት ይልቅ ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ በመጣስ የተለያዩ ጥፋቶችን ሲፈጽም ቆይቷል፡፡አሁንም እየፈጸመ ይገኛል፡፡
ስለሆነም የአማራ ክልል መንግሥት ይህን መሰሉን የህወሓትና የግብረ አበሮቹን ፖለቲካዊ ግልሙትና እና ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማድረግ ከመሞከር እንዲታቀብና የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በማክበር በአጭር ጊዜ በወረራ የያዛቸውን አካባቢዎች ለቆ እንዲወጣ እየጠየቅን ይህ የማይኾን ከኾነ የአማራ ክልል መንግሥትና ሕዝብ ከሌሎቹ ወንድምና እህት ኢትዮጵያዊያን ጋር በጋራ በመኾን ሀገርን ከማፍረስ መታደግና ሕዝባችንንም ከጥቃት ለመከላከል የምንገደድ መኾኑን ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡
የተከበራችሁ በክልላችን በየደረጃው ያላችሁ የፖለቲካና የጸጥታ መዋቅር አባላት፡- ከሰሜን ዕዝ ጥቃት በኋላ ትህነግ በቀሰቀሰው ጦርነት ሕዝባችን ቀጥተኛ ተጠቂ በመኾኑ ምክንያት ለበርካታ ችግሮች ተዳርጎ የነበረ መኾኑ ይታወቃል፡፡ ኾኖም ግን በየደረጃው የሚገኙ የመዋቅር አባላት ከጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ጥምር የጸጥታ ኃይሎችና ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በመኾን ሀገር አፍራሽ የጥፋት ኀይሉ ላይ የተቀዳጀው ድል ታሪክ አይዘነጋውም፡፡ ዛሬም እንደ ትናንቱ በፅናትና በቁርጠኝነት ሕዝቡን በማደራጀት አካባቢያችሁን በመጠበቅ ታሪካዊ ኀላፊነታችሁን እንድትወጡ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
የተከበርከው የክልላችን ሕዝብ፡- በተደጋጋሚ ጥቃት የፈጸመብህ የጥፋት ኀይል ዛሬም እንደ ትናንቱ ወረራ ፈጽሟል፡፡ በመኾኑም መላ የክልላችን ሕዝብ ከሐሰት ፕሮፓጋንዳ እና ሠርጎ ገቦች ራስህን በመጠበቅ ከክልል መንግሥትና በየአካባቢው ከሚገኙ አሥተዳደሮች ጋር የጠበቀ ቁርኝት በመፍጠር ጠላቶቻችን የከፈቱብንን ጥቃት ለመመከት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ የድርሻህን እንድትወጣ የከበረ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት፡- የፌደራል መንግሥት ህወሓት የቀሰቀሰው ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላም እንዲቋጭ ማድረጉን ሳናደንቅ አናልፍም፡፡ ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላም ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የተደረገውን ጥረት በሙሉ ልብ በመደገፍ ለውጤታማነቱ የድርሻችንን ስንወጣ ቆይተናል፡፡ ኾኖም ግን ህወሓት በተደጋጋሚ የተሰጠውን ዕድል ባለመጠቀም የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሲያፈርስ ቆይቷል፡፡ አሁንም በሙሉ አቅሙ ወደ ጦርነት ገብቷል፡፡ ይህን እኩይ ድርጊቱን የአፍሪካ ኅብረትና የዓለም አቀፍ ታዛቢዎች በቦታው ተገኝተው አረጋግጠዋል፡፡በመኾኑም ይህን እብሪተኛ ቡድን በአጭር ጊዜ ከወረራቸው አካባቢዎች ለቆ እንዲወጣ በማድረግ ሕዝባችንን ከጥፋት መታደግና የሀገራችንን ሉዓላዊነት ማስከበር ይገባል፡፡
ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ
ህወሓት ከምስረታዉ ጀምሮ ለአማራ ሕዝብ ባለው ሥር የሰደደ ጥላቻ ምክንያት በአማራ ሕዝብና በመላ ሀገሪቱ ሕዝብ ላይ የማያባራ ደም አፋሳሽ ጦርነትን ሲቀሰቅስ ኖሯል፡፡ ለዚህም ነው ህወሓት የኢትዮጵያም ኾነ የአፍሪካ ቀንድ አለመረጋጋት ምንጭ ነው የምንለው፡፡
ኾኖም በአሳሳች የፕሮፖጋንዳ ሥራዎቹ ምክንያት የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተደጋጋሚ በህወሓት ጉዳይ ላይ የተሳሳተ አቋም ሲይዝ ተስተውሏል፡፡ ዛሬ ግን ለዚህ አሳሳች ፕሮፖጋንዳው ያልተመቼ ኹኔታ ተፈጥሯል፡፡ በጠራራ ጸሐይ የአፍሪካ ሕብረትና ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች በተገኙበት ወቅት ወረራ መፈጸሙ በገሃድ ታይቷል፡፡
በመሆኑም ከዚህ ቀደም እንዳደረገው በአሁኑ ወቅት የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ማወናበድ አይችልም፡፡ የአማራ ክልል መንግሥትና ሕዝብ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ህወሓት የፈጸመብንን ወረራ በጥብቅ እንዲያወግዝና ከጎናችን እንዲቆም የከበረ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
ሚያዚያ 08 /2016 ዓ‹ም
ባሕር ዳር

Post a Comment

0 Comments