አመለኛዋ ባልቴት



ፊንፊኔ ሚያዝያ 11/2016(YMN) የባልቴትዋ ንቀት ከምድረ ገጽ እንዳያጠፋት ያሰጋል

የኖረችበት ክፉ አመልዋ ስለሚያስቸግራት አርፋ መቀመጥ አይህንላትም አትችልም፤”ጭር ሲል አልወድም” ለእርሷ ይሆናታል፤ይገልፃታል የባህል ጨዋታዬ ነው ያለችውን ጦርነት የሙጥኝ ብላዋለች

ለነገሩ ጦርነት ውስጥ ተወልዳ ያደገችና በጦርነት ኖራ ጎልምሳ፤አርጅታና ባልቴት ሆናም  የባህል ጨዋታ የምትለው ነገር ሁል ጊዜ ያምራታል፤ብትጎዳበትም ካሳለፈችው መከራ ተምራ ልምድ ወስዳ እርግፍ አድርጋ መተው አልቻለችም እንዴት ትተወው?በፍፁም አትችልም ጦርነት ከሌለ መኖር እንደማትችል ለተደጋጋሚ ጊዜ በተግባር አሳይታለች ባልቴትዋ!

አሁን በዚህ ሰሞን ለአራተኛ ጊዜ መቼም እንቅልፍ የሚያሳጣትን አካባቢ በመውረር አምስት ቦታዎችን በጉልበቷ ይዛለች አሉ፤የሰማሁትን ነው የምነግራችሁ፤የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ከትናንት በስትያ በይፋ ባወጣው አንድ መግለጫ እንደነገረን ከሆነ ባልቴትዋ እንደለመደችው በጉልበት የያዘቻቸው አካባቢዎች ራያ አላማጣ፤ራያ ባላ፤ኦፍላ ኮረምና ዛታ በመባል ይታወቃሉ፤ምናልባት የቀድሞ ስልቷን በመጠቀም እዚህ ደርሻለሁ እዚያ ገብቻለሁ ትለን ይሆን እንዴ?አቅም የላትም! እንዴት ትሁን?

ባልቴትዋ ክረምት በመጣ ቁጥር ጠላቴ ነው በምትለው ላይ ጦርነት ካላካሄደች ባህላዊ ጨዋታዋን ካላሳየች በፍፁም ደስ አይላትም፤እጅግ ይከፋታል፤ምን ቦጣትና ይክፋት?ለማን ብላ?ምቹ ጊዜ መኖሩን ስትገምት ወይም ወዳጆችዋ አለንልሽ ብለው ሹክ ሲሏት ያንን የምትመፃደቅበትን ባህላዊ ጨዋታ ትጫወት እንጂ!

የባልቴትዋ ነገር እኮ ተነግሮ አያልቅም ራስዋ ቆስቁሳ ባስነሳችው ጦርነት ያለቁ የትግራይ ወጣቶች ደም በእርሷ ዘንድ  ከምንም አይቆጠርም ምኗም አይደለም፤ምክንይቱም እርሷ እንደምትለው ለሀገረ ትግራይ ሲሉ ነው የተሰውት በቃ!ባልቴትዬ እንዲህ ነው የምታስበው

ደግሞ እኮ ለሌሎች ያላት ንቀት ገደብ አልባ ነው፤ንቀቷ ብርቱ ነው ቀደም ሲል ሌሎችን በመናቅ ያደረገችው እንቅስቃሴ ሁሉ ጎዳት እንጂ አልጠቀማትም፤የባልቴትዋ ትዕቢት ከግማሽ ሚሊየን በላይ የትግራይ ክልል ወጣቶች እንዲያልቁ ምክንያት ሆኗል፤እንዲያውም አንዳንዶች እንዴትና በምን ዘዴ እንደቆጠሩት ፈጣሪ ይወቀው እንጂ በጦርነቱ ምክንያት ያለቀው ሰው ቁጥር ከአንድ ሚሊየን ይልቃል

አሁን በሕገ መንግስቱ መሰረት የእኔ ነው የምትለውን መሬት በጉልበት ለመያዝ መዘጋጀትዋን ባልቴትዋ ቀደም ብላ ምልክቶችን አሳይታለች፤ማስጠንቀቂያዎችንም ሰጥታለች የአማራ ክልል ለአካባቢው ልጆች በአማርኛ ትምህርት መስጠቱን ያቁም! ካላቆመ ወዮለት ስትል ዝታለች፤ትክክለኛውን ቁጥር ራሷ የምታውቀው ቢሆንም ከ270 ሺህ በላይ ታጣቂዎች አሉኝ ብላ በአደባባይ አስታውቃለች፤የፌዴራል መንግስት ካልረዳ እገዛ ካላደረገ ይህን ጦር ምን ላድርገው ስትልም ተሰምታለች

ባልቴትዋ ይህን ሁሉ ስትል ጦርነቱ ይብቃ ብላ ወደ ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በመሄድ የፈረመችው የሰላም ስምምነት ዝርዝር ጉዳይ መኖሩን ከነአካቴው የዘነጋችው መስላለች የባልቴት ነገር እንዲህ ነው እኮ፤ አልዘሚር በመርሳት በሽታ ተጠቃች እንዴ?

የአስተዳደር ወሰን አለመግባባት በህጋዊ አካሄድ ተገቢው ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ በህዝብ ውሳኔ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ የፌዴራል መንግስት ቀደም ሲል የሰጠው አቅጣጫ የተዋጠላት እንዳልሆነ በተግባርዋ ደጋግማ አሳይታለች፤በቅርቡ ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ ሆና ቅጣቱን ውጣ ዝም ብትልም በራያ በኩል ለፈፀመችው ትንኮሳ ጀግናው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ክንዱን አሳይቷታል አሉ ወሬ አይደበቅም እኮ!

ደግሞ እኮ ብልጥ እኔ ብቻ ነኝ ብላ ታስባለች አይ የባልቴት ነገር!የፌዴራል መንግስት በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ ነበሩበት የመኖሪያ አካባቢ ይመለሱ ሲል የሰጠውን አቀጣጫ ገልብጣ ነው የሰማችው፤የፌዴራል መንግስት ታጣቂዎችሽ  ወደ አካባቢው ይግቡ  ያላት መሰላት እንዴ?

የባልቴትዋ ንቀት ለከት የለውም የፌዴራል መንግስት ምንም አያመጣም የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሰች ትመስላለች ምናልባት የንቀቷ ደረጃ ከፍ ሊል የቻለው የፌዴራል መንግስት ደክሟል በሚል ግምት ሊሆን ይችላል፤ወይም ደግሞ እነዚያ የውጭ አጋሮችዋ በጦርነቱ ጊዜ ሳታላይት ሳይቀር እገዛ ያደረጉላት እነ እንቶኔ ሞራል ሰጥተዋትም ሊሆን ይችላል እንጠርጥር እንጂ! “ጠርጥር ከገንፎ አይጠፋም ስንጥር” ይባል የለም እንዴ?አዎ መጠርጠር መልካም ነው

 

 

 

 

 

Post a Comment

0 Comments