“ሌባ ለአመሉ ዳቦ ይልሳል”

 

 


ፊንፊኔ #Ethiopia ግንቦት ግንቦት 30/2015(YMN) ለአርሶ አደሩ እንዲከፋፈል በውጭ ምንዛሪ ወደ አገር የገባውን ማዳበሪያ የሚሸጥ ማንኛውም ሰው እጁ መቆረጥ አለበት!

በአንድ ወቅት እነ አቶ መለስ ዜናዊ ሌብነትም ስራ ነው ብለው ተናግረው መንገዱን ወለል አድርገው ከፈቱና ኢትዮጵያ እንደ አሸን በፈሉ ሌቦች ተቸገረች በጣም ያሳዝናል!ማዳበሪያም ተሰርቆ ይሸጣል

“ሌባ ለአመሉ ዳቦ ይልሳል”ሆነና ነገሩ ሌብነቱ ተስፋፍቶ መንግስት በከፍተኛ ወጪ ወደ አገር ያስገባው ማዳበሪያ በተለመደው የሌብነት ኔት ወርክ አማካይነት ከመጋዘን ወጥቶ ወይም ደግሞ በአላማ ቢስ ታጣቂዎች ተዘርፎ ገበያ ላይ ይቸበቸባል

ማዳበሪያውን ከገበያ የሚገዛውም አይጠይቅም፤ዝም ብሎ ገዝቶ ይጠቀማል ግለኝነቱ በርትቶበት፤ ደግሞ እኮ የማዳበሪያ ዋጋ ንሯል ብሎ መንግስትን ያማርራል ከዚህ ይልቅ ሻጩን ከየት አመጣህ? በማለት ጠይቆ አሳማኝ ምላሽ ሲያጣ ሽመሉን መምዘዝ ነው ያለበት!

መንግስት ለአርሶ አደሮች ድጎማ በማድረግ ያስገባው የትኛውም ማዳበሪያ ዩሪያም ሆነ ዳፕ ገበያ ላይ ወጥቶ ሲቸበቸብ ወይም በድብቅ ሲሸጥ ዝም ብሎ መመልከት አይገባም!

ይህ ማደባሪያ በመንግስት ተገዝቶ ወደ አገር እንዲገባ ቢደረግም ገንዘቡ የእኔ፤የአንተ የአንቺ ነው በግብር ከሁላችን የሚሰበሰብ ገንዘብ ነው መንግስት ከየትም ሊያመጣ አይችልም

ከእኛው ተሰብስቦ ለአርሶ አደሩ ወገናችን ምርትና ምርታማነት መጨመር የሚገባው ማዳበሪያ በአይነ ደረቅ ደፋሮች ተሰርቆ ሲሸጥ ዝም ማለት አይገባም መሸማቀቅ ያለባቸው ሌቦች ናቸው ሌቦች ላይ በመዝመት እንዲሸማቀቁ ማድረግ የሚያስችል አቅም አለን እንጠቀምበት!

ከሰሞኑ ከወደ አማራ ክልል አርሶ አደሮች መንግስት ማዳበሪያ ያቅርብልን ብለው ሰልፍ ወጥተዋል አሉ ምናልባት ነገርየው በአካባቢው ከሰነበተው መጥፎ የፖለቲካ ትኩሳት ጋር ተያያዥነት ከሌለው ደግ ነው ያደረጉት

ከሰልፉ መካሄድ በላ በመጋዘን የተከማቸው ማዳበሪያ ወጪ ተደርጎ ለአርሶ አደሮች ይከፋፈል የሚል ውሳኔ መተላለፉን ሰምቻለው ለአርሶ አደሮቹ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ሲባል የተወሰደ እርምጃ እንደሆነ መገመት ይቻላል

“ወደብ ላይ ደርሷል” የተባለው ማዳበሪያ አገር ውስጥ ገብቶ ወደየአካባቢው እስኪከፋፈል ድረስ አርሶ አደሮች በተገኘው ማዳበሪያ መጠቀም ከቻሉ መልካም ነው፤ለነገሩ ይመጣል የተባለው ማዳበሪያ የእርሻ ወቅት ካለፈ በላ ቢደርስም ለቀጣይ አመት ካልሆነ ጥቅም ሊኖረው አይችልም

በቅርብ ጊዜ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ በክልሎች ግብርና ቢሮ የስራ መሪዎች ላይ ቅሬታ እንዳላቸው በሚዲያ ሲናገሩ ሰምቻለሁ፤ሚኒስትር ዲኤታዋ በምሬት ሲናገሩ እንደሰማሁት የክልል ግብርና ቢሮ የስራ ኃላፊዎች በመጋዘን ተከማችቶ የቆየውን ማዳበሪያ ለማከፋፈል ያልፈቀዱት “ከውጭ የሚመጣው ይድረስና አንድ ላይ እናከፋፍላለን” የሚል ነው

እንዲህ አይነቱ መዛነፍና ዳተኝነት ነው ለአይነ ደረቅ ሞሽላቃ ሌቦች የሌብነት በሩን ወለል አድርጎ የሚከፍተው የሌቦች መግቢያ በር ተከርችሞ እንዲዘጋ በመናበብ መስራት ይገባል!

አርሶ አደሩም አገኘሁ ብሎ ማዳበሪያን ከገበያና በድብቅም ከየስርቻው በውድ ዋጋ መግዛትን ትቶ በሕጋዊ መንገድ በተወካዮቹ አማካይነት መብቱን ይጠይቅ!

የክልል ግብርና ቢሮ የስራ ኃላፊዎችም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ይከላከሉ!በየዘርፉ የተሰማራው የግብርና ባለሙያዎች ለአርሶ አደር ወገኖቻችን በመቆርቆር ይስሩ!አርሶ አደር ከድህነት ህይወት ከወጣ የእነርሱም ኑሮ መሻሻሉ አይቀርም ጊዜው ሲደርስ ሁሉም ይሆናል

እስከዚያው ድረስ በመታገስ መስራት ያስፈልጋል ለጊዜያዊ ጥቅም መልከስከስ በደላሎች እጅ መግባት በኔትወርክ መጠለፍ ዘላቂ ጥቅምን የሚያሳጣ ስለሆነ በጥንቃቄ መስራት ይገባል!

መንግስት ደግሞ እጅ ከፍንጅ የሚያዙ የማዳበሪያ ሻጮችን ጨከን ብሎ እጃቸውን መቁረጥ ይጠበቀበታል!መንግስት ሆይ የገጠሩ ችግር እንደከተማው ችግር ጊዜያዊና በሆይ ሆይታ የሚያልፍ እንዳልሆነ ታውቀዋለህ ከሰማንያ በመቶ በላይ ደጋፊና መራጭህ የሚገኘው  በገጠሪቱ ኢትዮጵያ መሆኑንም ከአንተ በላይ ማን ያውቃል? ይህ ለአንተ አይነገርም መንግስትዬ!

Post a Comment

0 Comments