ፊንፊኔ #Ethiopia ሰኔ 02/2015(YMN) በታላቁ አንዋር መስጂድ ህዝበ ሙስሊሙ እንደወትሮ ሁሉ የጁምዓ ሰላቱን ሰግዶ በሰላም ወደ መጣበት መመለሱን ኡስታዝ አቡበከር አህመድ ገልጸዋል።
" ባለፉት ሁለት ጁምዓዎች በተፈጠሩ ችግሮች በርካታ ሙስሊሞች ከህይወት መስዋትነት አንስቶ ብዙ ዋጋ ከፍለዋል " ያሉት ኡስታዝ አቡበከር " የነሱ መስዋትነት ሁልጊዜም በልባችን ውስጥ ሲታወስ የሚኖር ነው " ብለዋል።
" ህዝበ ሙስሊሙ ሁልጊዜም ሰላም ፈላጊ እና የሰላም ዘብ መሆኑን እንደወትሮ ሁሉ ዛሬም አስመስክሯል " ያሉት ኡስታዝ አቡበከር " ለህዝበ ሙስሊሙ ሰላም የእምነቱ መርህ እና መመሪያው በመሆኑ ሰላሙን ለመጠበቅ ሁሌም ዝግጁ እና ንቁ ነው " ሲሉ ገልጸዋል
በዛሬው ጁምዓ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የመንግስት የፀጥታ ኃይል በመስጂዱ ዙሪያ ለጥበቃ በመሰማራቱ በህዝበ ሙስሊሙ ዘንድ ስጋት ፈጥሮ የነበረ ሲሆን ከሚመለከተው የፀጥታ አመራሮች ጋር በመነጋገር ዙሪያውን ከቦ የነበረው የፀጥታ ኃይል ወደኃላ እንዲመለስ በማድረግ ህዝበ ሙስሊሙ ፀጥታውን በራሱ በምእመናን እና በአስተባባሪዎቹ እንደወትሮ በማስጠበቅ የጁምዓ ሰላቱ በሰላም ተሰግዶ ማጠናቀቅ መቻሉ ተገልጿል።
ኡስታዝ አቡበከር ፤ የዛሬው ጁምዓ በሰላም እንዲጠናቀቅ አስተዋፅኦ ላበረበተው ህዝበ ሙስሊም እንዲሁም የፀጥታ መዋቅሩ በድርሻው ህዝበ ሙስሊሙ በራሱ ሰላሙን ማስጠበቅ እንደሚችል እምነት በማሳደር የበኩላቸውን በመወጣታቸው ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይም የፀጥታ ኃይሉ በትብብር እና በመናበብ ከህዝበ ሙስሊሙ እና ከአመራሩ ጋር ተቀራርቦ በመስራት የጋራ ሰላማችንን ማስጠበቅ እንደሚቻል ከዛሬው ጁምዓ ትምህርት መውሰድ ይቻላል ብለዋል።
VIA:tikvahethiopia
0 Comments