ኦሮሞና መላው ሕዝብ የሚጠቀመው ክስ በመደርደር አይደለም!


ፊንፊኔ #Ethiopia ሕዳር 29/2016(YMN) ሁል ጊዜ “እኔ ብቻ ትክክል ነኝ” በሽታ ነው፤ እኔ ያልኩት ብቻ ተግባራዊ ካልሆነ የድርቅና አካሄድ መላውን ሕዝብ ሊጠቅም አይችልም፤ሕዝብ ተጠቃሚ መሆን የሚችለው በመንግስት ከፍተኛው የስልጣን እርከን ላይ በመቀመጥ የተድበሰበሰ አካሄድ በመከተልና የራስን እውነት ብቻ ለማጉላት በመሞከር አይደለም፤ያለው ሁኔታ አሳፋሪና አስተዛዛቢም ነው

የሰላም ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ታዬ ደንደአ በየጊዜው ሃሳባቸውን ነፃ ሆነው በአደባባይ ላይ በመግለፅ ይታወቃሉ ከሰሞኑም ጊዜ ጠብቀው አድርገውታል መልካም ነው፤አቶ ታዬ ግልፅ ስለሆኑ እንወድዎታለን ለእርስዎ ክብርም አለን ግን የራስን ሃሳብና አተያይ ይፋ በማድረግ ብቻ የኦሮሞና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተጠቃሚ ይሆናል ወይ? ብለን ጥያቄ ለማንሳት እንገደዳለን ይህን ጊዜ ለምን መረጡ? ብለንም እንጠይቃለን!

1ኛ ከግለሰብ ባለስልጣን ጋር የሚፈጠር ልዩነትና አለመግባባት ዘላቂ መፍትሄ ማግኘት የሚችለው አደባባይ ላይ ወጥቶ ዘባራቂ በመሆን ሳይሆን በውስጥ ሕገ ደንብና መመሪያ መሰረት ተነጋግሮ በመተማመን ብቻ ነው

ለዚህም ጥበብና አቅም ያስፈልጋል እኔ ብቻ ነኝ ባለ እውነት ማለት የትም ሊያደርስ አይችልም፤አደባባይ ላይ ወጥቶ ትክክለኛው ሰው እኔ ብቻ ነኝ እውነቴን ተቀበሉ እኔ ከደሙ ንፁህ ነኝ አካሄድ ትክክለኛ ሊያስብል አይችልም

2ኛ በመንግስት ውስጥ ሆኖ አሸባሪ ቡድንን መደገፍና ማንቆለጳጰስ በሕግ ያስጠይቃል!ሸኔ አሸባሪ ቡድን ነው የጠላት ተላላኪ ነው የኦሮሞ ሕዝብ ጠላት ነው የኦሮሞ ሕዝብ እንዲሸማቀቅ፤በሌሎች ወንድሞቹም በጥርጣሬ እንዲታይ ያደረገ ቅጥረኛ ቡድን ነው

ታዲያ ይህን ቡድን በመደገፍ መንግስትን ማጣጣል እንዴት ተቀባይነት ሊኖረው ይችላል?የሩቁን ትተን በቅርብ ያለውን ብናይ ከሰሞኑ በታንዛንያ ዳሬ ሰላም በአሸባሪው ቡድንና በመንግስት ተወካዮች መካከል የተካሄደው የሰላም ድርድር ያለ ውጤት የተበተነው መንግስት በማደናቀፉ ነው እንዴት ይባላል?ይህስ እንዴት ሊሆን ይችላል?

መንግስትስ ይህን የሚያደርገው ምን ለማግኘት ነው?መንግስት የመረጠው ሕዝብ በእንግልት ኑሮ እንዲቀጥል ይፈልጋል ማለት ነው?መራጩ ሕዝብ ሰላም አጥቶ ወጥቶ ለመግባት የሚቸገርን ሕዝብ እንግልት መመልከት የሚሻ መንግስት የለም ሊኖርም አይችልም!

3ኛ አቶ ታዬ ደንደአ ለኢትዮጵያ ጠላት ለሚሰራው ቢቢሲ አማርኛ በሰጡት ቃለ ምልልስ በትግራይ ጦርነት ብቻ 28 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ መድረሱን ነግረውናል ይህን መረጃ ከየት አመጡት? በምንና በማን አስጠኑት? በሰላም ሚኒስትር ዴኤታነታቸው ወደ ስራ ቦታቸው መረጃውን ማን አመጣላቸቸው? ይህን የተናገሩት ለቀድሞ ቀጪና አዋራጃቸው የወያኔ ቁንጮዎች አሁን ባለው ሁኔታ ድጋፍ ለማድረግ ፈልገው ነው? ወይስ ምንድነው? ግልፅ አይደለም! እስኪ እባክዎ በለመዱት ግልጽነትዎ ያብራሩልን

የእርስዎስ አያልቅም ስንቱን አንስተን እናውጋ? በዲፕሎማሲው ዘርፍም ኢትዮጵያ ውጤት አልባ ናት ብለው በዚያ በሚታወቁበት ግልፅነትዎ እውነቱን ነው የነገሩን?አይናችሁን ጨፍኑና ላሞኛችሁ ያሉን አይመስልዎትም? ከሰሞኑ በዱባይ የተካሄደውን የአየር ንብረት ጉባኤ ተከታትለውት ይሆን?ከተከታታሉ እውነታውን መረዳት አይሳኖትም ብዬ ነው፤ሌላው የዲፕሎማሲ ስኬት ይቅርና በአረንጓዴ ልማት ስኬት ብቻ የአገራት መንግስታት ተወካዮች ለኢትዮጵያ መንግስት ያጎረፉት አድናቆት የዲፕሎማሲ ስኬት አይደለምን?

ለማንኛውም የውስጥና የውጭ ጠላቶች ባደረጉት ቅንጅት በመንገድ ላይ የሚቀር ብልጽግና የለም!ብልጽግና መራሹ የኢትዮጵያ መንግስት ስፍር ቁጥር የሌለው ችግር እያለ መቀጠል የቻለው የአብዛኛው ሕዝብ ሙሉ ድጋፍ ስላለውና በቀጣይ ላለው ሂደትም መልካም ተስፋ የሰነቁ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደጋፊ ዜጎች ስላሉ ነው

ቀደም ሲል በመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ ሸኔዎች ጫካ ካለው የሸኔ ቡድን ጋር ግንኙነት አለው ፈተናው የከበደው ለዚህ ነው ሲባል ቆይቷል “እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል” እንዲሉ አሁን እወነቱ ግልፅ ሆኗል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሁሉም ገላልጦ ራሱን ይፋ እያደረገ ነው፤በተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ መቀመጫ ያላቸው አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለአማራ ጽንፈኛ `ሃይል ወግነው የመከላከያ ሰራዊት ከአማራ ክልል መውጣት አለበት በሚል ያራመዱት አቋም ተቃባይነት አጥቶ ያለው ሁኔታ ይታወቃል

አሁን ገዱ ቁጥር 2 ከጨፌ ኦሮሚያ ተነስቷል የሚያስብል ሁኔታ ተፈጥሯል እንዲሁም ቀጣዩ እስክንድር ነጋ ከኦሮሚያ ለመነሳት ይሞክር ይሆናል ለውስጥ አዋቂ ምን ይሳነዋል? ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ መንግስት ለግለሰቦች ፍላጎትና ጥቅም መሟላት ሳይሆን የመላውን ሕዝብ ጥቅምና መብት ማስከበር ግዴታው ስለሆነ አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳል ተብሎ ይጠበቃል እውነቱ ይኸው ነው “አብዮት ልጇን ትበላለች!”

Post a Comment

0 Comments