የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ውሳኔዎችን አስተላልፏል




ፊንፊኔ #Ethiopia የካቲት 20,2015(YMN) የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ሰኞ የካቲት 20/2015 ዓ.ም ባካሄደዉ 3ኛ መደበኛ 6ኛ የስራ ዘመን 2ኛ ዓመት ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል፡፡ 

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የክልሉን ህዝብ ኑሮና ተጠቃሚነት በመሰረታዊነት ለማሻሻል የሚያስችሉ ፈጣን፣ ዘላቂና ሰፊ መሰረት ያለው ልማት ለማስመዝገብ የተለያዩ የልማት ስትራጂዎችን በማመንጨት እና ስትራቴጂዎቹና እቅዶቹ ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችሉ አደረጃጀቶችንና አሰራሮችን በመዘርጋት ስሰራ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
ባለፉት አመታት ውስጥ የህዝባችንን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የከተማ ልማት ስራዎችን ለማካሄድ በከተማዎቹ የእድገት ደረጃ መሰረት በርካታ ከተሞችን በመመስረት ሰፋፊ ስራዎች የተሰሩ ቢሆንም አሁን በደረስንበት የእድገት ደረጃ ዘመናዊ እና ተወዳዳሪ በመሆን ህዝባችንና ክልላችን የሚመጥኑ ከተሞችን ለመፍጠር እንዲሁም ህገ ወጥነትን በመቆጣጠር በከተሞች ውስጥ እየታዩ ያሉ ውስብስብ ሁኔታዎችን ለማስተዳደር ያለውን አደረጃጀት እየፈተሹና እያሻሻሉ መሄድ አስፈላጊ ነው፡፡
በመሆኑም ከተሞቹ ያላቸውን መልካም እድል እና እምቅ አቅም ወደ አንድ በማምጣት አብሮ እንዲለሙና የጋራ ዓላማ እንዲኖራቸው፣ በአንድ ፕላን በመተዳር ሁለንተናዊ እድገት እንዲኖራቸው፣ ጠንካራ የኢኮኖሚ እድገት ኖሯቸው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ሙያን ለማስፋፋት፣ የብዝነስ አስተሳሰብን ለማዳበር እና የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ሁለትና ከዛ በላይ የሆኑ ከተሞችን አንድ ላይ ቀላቅሎ በአዲስ መልክ ለማደራጀት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ለአስተዳደር በሚያመች መንገድ የከተሞቹ አደረጃጀት እንደሚከተለው ተከናውኗል:-
1. ቢሾፍ ከተማ፡ ቢሾፍቱ ከተማ፣ ዱከም ከተማ እንዲሁም የመዘጋጃ ቤት ከተሞች ሂዲ፣ ኡዴ ደንካካ እና ድሬን በመቀላቀል በ3 ክ/ከተሞች እና በ10 ወረዳዎች እንዲደራጅ ሆኗል፤
2. ሻሸመኔ ከተማ፡ ሻሸመኔ ከተማ እና ብሻን ጉራቻ ከተማን በመቀላቀል በ4 ክ/ከተሞች እና በ12 ወረዳዎች እንዲደራጅ ሆኗል፤
3. አዳማ ከተማ፡ አዳማ ከተማ እና ወንጂ ከተማን በመቀላቀል በ6 ክ/ከተሞች እና በ19 ወረዳዎች እንዲደራጅ ሆኗል፤
4. ሮቤ ከተማ፡ ሮቤ ከተማ እና ጎባ ከተማን በመቀላቀል በ3 ክ/ከተሞች እና በ12 ቀበሌዎች እንዲደራጅ ሆኗል፤
5. ማያ ከተማ፡ ሀረማያ ከተማ፣ አወዳይ ከተማ እና አዴሌ ከተማን በመቀላቀል በ3 ክ/ከተሞች እና በ12 ቀበሌዎች እንዲደራጅ ሆኗል፤
6. ባቱ ከተማ፡ ባቱ ከተማ እና አዳሚ ቱሉ ከተማን በመቀላቀል በ7 ቀበሌዎች እንዲደራጅ ሆኗል።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የመልማት መልካም እድል ያላቸው ከተሞች ያላቸዉን መልካም እድል በተሟላ መንገድ በመጠቀም ሁለንተናዊ የሆነ ልማት እንዲያስመዘግቡ ለማድረግ እንዲሁም በአካባቢያቸው ያሉትን ከተሞችና ወረዳዎችን ልማት እንዲያፋጥኑ ለማስቻልና የአመራሩን ትኩረት በቅርበት እንዲያገኙ ለማስቻል የሚከተሉት ከተሞች ተጠሪነታቸው ለክልሉ መንግስት እንዲሆን ተወስኗል፡፡
1. መቱ ከተማ
2. አጋሮ ከተማ
3. ቡሌ ሆራ ከተማ
4. ነጆ ከተማ
5. ሰንዳፋ በኬ ከተማ
6. ሸኖ ከተማ
7. ሞያሌ ከተማ
8. ዶዶላ ከተማ
9. ሻክሶ ከተማ
በተመሳሳይ መልኩ የከተሞች የማስፈፀም አቅማቸው ተሻሽለው ፈጣንና ከእንግልት የፀዳ አገልግሎት በሙሉ አቅም እንዲሰጥና ሁሉአቀፍ የሆነ ልማት እንዲመዘገብ ለማድረግ እንደ አጠቃላይ እየተደረገ ያለውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣዎን የከተሞችን እድገት መሠረት በማድረግ የከተሞችን ደረጃ እንደሚከተለው እንዲሻሻል ተወስኗል።
1. አዳማ፣ ሻሻመኔና ቢሾፍቱ ከተሞች፡- የሬጂዮ-ፖሊስ ከተማ
2. የሮቤ ከተማና የማያ ከተማ፡- ዋና ከተማ
3. የመቱ፣ አጋሮ፣ ቡሌ ሆራ፣ ነጆ፣ ሰንዳፋ በኬ፣ ዶዶላመ ሸኖ፣ ሞያሌና ሻክሶ ከተማ፣- ወደ ከፍተኛ ከተማነት እንዲያድጉ ተወስኗል።
በሌላ መልኩ ለረጂም ጊዜ ስነሳ የቆየውን የልማት፣ የሰላም እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በመመለስ ፈጣን የሆነ የኢኮኖሚያና ማህበራዊ ለማስመዝገብ፣ በድንበር አካባ ያለውን ህገ ወጥነትን ለመቅረፍ፣ በድንበር አካባ ከአጎራባች ክልሎች ጋር የሚከሰተውን የሰላም ሁኔታን ለመፍታት እንዲሁም ተደራሽ የሆነ አገልግሎት ለማቅረብ ውጤታማ የሆነ አደረጃጃትና አሰራር መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የምስራቅ ቦረና ዞን አዲስ ዞን ሆኖ እንዲደራጅ ተወስኗል፡፡
በአዲስ መልክ 21ኛ ዞን ሆኖ የተደራጀው የምስራቅ ቦረና ዞን ዋና ከተማው ነጌሌ ቦረና ሆኖ፡-
• ከቦረና ዞን ሞያሌ ወረዳ፣ ሞያሌ ከተማ፣ ጉቺ ወረዳ እና ዋችሌ ወረዳ፣
• ከጉጂ ዞን ሊበን ወረዳ፣ ጉሚ ኤልደሎ ወረዳ፣ ነጌሌ ቦረና ከተማ፣
• እንዲሁም ከባሌ ዞን መደወላቡ ወረዳ፣ ኦቦርሶ ወረዳ እና ሀረና ቡሉቅ ወረዳ በመጨመር እንደ ዞን 10 ወረዳዎችን በመያዝ እንዲደራጅ ተደርጓል፡፡
በአዲሱ አደረጃጀት የምስራቅ ቦረና ዞን በአዲስ መልክ የተደራጀ ሲሆን የጉጂ ዞን ዋና ከተማ አዶላ ሬዴ ሆኖ የቦረና ዞን ዋና ከተማ ደግሞ ያቤሎ ከተማ እንዲሆን ተወስኗል
በልላ በኩል ለማህበረሰቡ ተደራሽ የሆነ አደረጃጀት ለማቅረብ፣ የመሬት ስፋት፣ የፀጥታ ችግር፣ የመልካም አስተዳደርና ፈጣን የልማት ጥያቄዎችን ለማረጋገጥ መደ ወላቡ ወረዳ የነበረዉን በሁለት ቦታ በመክፈል ማለትም የመደ ወላቡ ወረዳና ኦቦርሶ ወረዳ ሆኖ እንዲደራጅና ጭናክሰን ወረዳ የነበረዉን በሁለት ወረዳ በመክፈል ማለትም ጭናክሰን ወረዳና የመከኒሳ ኦሮሞ ወረዳ ሆኖ እንዲደራጅ ተወስኗል።

ምንጭ:የኦሮሚያ ኮሙኑኬሽን ቢሮ

Post a Comment

0 Comments