" ለመውጫ ፈተና ራሳችሁን አዘጋጁ " - ትምህርት ሚኒስቴር




ፊንፊኔ #Ethiopia የካቲት 02 2015(YMN) ትምህርት ሚኒስቴር ፤ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ለዩኒቨርስቲ መውጫ ፈተና ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ አሳሰበ።

የዩኒቨርስቲ መውጫ  ፈተና በመጪው ሀምሌ ወር በሁሉም የትምህርት መስኮች እና መርሀግብሮች በግልና በመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ይሰጣል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በመውጫ ፈተና ዙሪያ ከተማሪዎች ህብረት ተወካዮች  ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱም የመውጫ ፈተና በመጪው ሀምሌ ወር በኦንላይን ለሁሉም የመንግስትና የግል ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንደሚሰጥ ገልፀዋል።

ለሚሰጠው የመውጫ ፈተና ብቁ ለመሆንም ተማሪዎች በየዩኒቨርስቲዎቹ የሚሰጠውን የመጨረሻውን ሰሚስተር ፈተና መውሰድና ኮርሶችን ማጠናቀቅ እንደሚገባም ሚኒስትር ዴኤታው አስገንዝበዋል፡፡

ለፈተናው በሁሉም የትምህርት መስኮች ላይ የተመረጡ ኮርሶች የብቃት ልየታ ተደርጎላቸው ዩኒቨርስቲዎች እንዲያውቁት መደረጉን የጠቆሙት ዶክተር ሳሙኤል በአሁኑ ወቅትም የፈተና ንድፈ ማሳያና / Blueprint / የፈተና ዝግጅት ስራ በመከናወን ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በመሆኑም ተማሪዎች በቀሪዎቹ አምስት ወራት ተገቢውን ዝግጅት በማድረግ ራሳቸውን ለፈተናው ብቁ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በመድረኩ የተገኙ የተማሪዎች ህብረት ተወካዮችም ወደ ዩኒቨርስቲዎቻቸው ሲመለሱ ተማሪዎች ለፈተናው በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው  ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡

በውይይቱም ከሁሉም ዩኒቨርስቲዎች የተውጣጡ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንቶች ተገኝተዋል፡፡

ምንጭ፦ ትምህርት ሚኒስቴር 



Post a Comment

0 Comments