ሕግና ስርዓት ያላት አገር ውስጥ እንገኛለን፤የአገር ሕግና ስርዓት መከበር አለበት የአገር ሕግና ስርዓት ካልተከበረ ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም መግባት አይችሉም
ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም መግባት የማይችሉበት ሁኔታ ከተፈጠረ ምንም ነገር ሊኖር አይችልም ሕግና ስርዓት ከተጣሰ ሰርቶ መብላት፤በነፃነት መንቀሳቀስ፤ወልዶ መሳም፤የሰላም እንቅልፍ መተኛት ማህበራዊ ሚዲያዎችን መጠቀም የሚናፍቅ ይሆናል
አሁን የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር ሕግና ስርዓት እንዲጣስ ግፊት በማድረግ ላይ የሚገኙ ኃይሎች ነገር ከተበላሸ በኋላ የሉም ይደበቃሉ ፈርጥጠው ይጠፋሉ ተጎጂውና ለከፍተኛ እንግልት የሚጋለጠው እየተገፋፋ ያለው ወገን ብቻ ይሆናል
አንዳንድ ኃይሎች በቀጣይም መንግስትን በምርጫ ማሸነፍ እንደማይችሉ ስለተረዱ በየትኛውም የተገኘ አጋጣሚ በመጠቀም ወደ ስልጣን ለመውጣት ይፈልጋሉ፤ይህን ፍላጎታቸውን በተለያዩ ወቅቶች አንፀባርቀዋል፤ከመስከረም 30 በኋላ መንግስት የለም ብለው የፎከሩበትን ሁኔታ መዘንጋት አይገባም
በአሁኑ ወቅትም በምክክርና በውይይት ዘላቂ መፍትሄ ሊያገኝ የሚችለውን ጉዳይ ተገን በማድረግ ምናልባት ከተሳካልን ዓይነት ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል
ይህ ጥረታቸው በስልጣን ላይ የሚገኘውን መንግስት የሰላም ጥረት በማንቋሸሽና በማጣጣል እየተገለፀ ይገኛል፤አካሄዳቸው ማንንም የሚጠቅም እንዳልሆነ ቢያውቁም እኔ ያልኩት ካልሆነ ልሙት ዓይነት አካሄድ ላይ ይገኛሉ
በተለይም በውጭ የሚገኙና አገር ውስጥም ተደብቀው ያሉ ኃይሎች በለው! ፍለጠው! ቁረጠው! የሚል ግፊት በማድረግ ላይ ናቸው፤ እነርሱ በሰው እጅ እሳት መያዝን ያውቁበታልና ወገን ጠንቀቅ እንበል!
ይህ ጫጫታና ርብርባቸው በከፍተኛ ተስፋ እየተጠበቀ ያለው የአገራዊ መግባባትና ምክክር ፕሮግራም እንዲጨናገፍ ማድረግም ስለሆነ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በማድረግ ላይ ያሉት ጥበቃና ጥንቃቄ እንዳለ ሆኖ ሁሉም ዜጋ የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ የመጠበቅና የመከታተል ኃላፊነትና ግዴታ እንዳለው መዘንጋት የለበትም
0 Comments