የመንግስት ግልበጣ ስትራቴጂ ቁጥር ሁለት(2)






ፊንፊኔ #Ethiopia መጋቢት 10,2015(YMN) ከውስጥና ከውጭ ቅንጅት የፈጠሩ ጽንፈኞች በብልጽግና ፓርቲ እየተመራ ያለውን የኢትዮጵያ መንግስት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመገልበጥ ያስችለናል ብለው ያመኑባቸውን ስልቶች አዘጋጅተው በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል

በቁጥር 1 ስትራቴጂ የሃይማኖት ግጭትን በማቀጣጠል የክርስትና እና የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ግጭት ውስጥ ለማስገባት ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፤ነገር ግን እስከ አሁን ሊሳካላቸው ባይችልም የመጀመሪያውን ስትራቴጂ በቀጣይነት ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ በክፍል አንድ ጽሑፌ ለመጠቃቀስ ሞክሬያለሁ፤በቀጣዩ ጽሑፍ ጽንፈኞች በተለያዩ ምክንያቶች ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ጉዳይ ለመንግስት ግልበጣ ያግዘናል በማለት እየተጠቀሙበት መሆናቸውን ተጨባጭ የሆኑ ማሳያዎችን በማንሳት የማቅርብላችሁ ይሆናል

ስትራቴጂ 2: የተፈናቀሉ ዜጎችን ጉዳይ ለፖለቲካ ንግድ መጠቀም

በአንዳንድ አካባቢዎች ታጠቂዎች በፈፀሟቸው ጥቃቶች ምክንያት ዜጎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው ለመፈናቀል ተገደዋል፤በዋናነት በምዕራብ ኦሮሚያ በተለያዩ የወለጋ ዞኖች ውስጥ በተለያዩ ወቅቶች የተከሰተውን የዜጎቻችን መፈናቀልና እንግልት ማንሳት ይቻላል

ዜጎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው መፈናቀላቸው ለኦሮሞና አማራ ጽንፈኞች ሰርግና ምላሽ ሆኖላቸው ተመልክተናል፤ጽንፈኞቹ ዜጎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው እንዲፈናቀሉ በመናበብ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጭምር በማረጋገጥ ለሕዝብ ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል

በዚህ ረገድ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የኦሮሞና የአማራ ጽንፈኛ ቡድኖች በመቀናጀት የሚሰሩ መሆናቸውን ይፋ አድርገዋል፤ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የኦሮሞና የአማራ ጽንፈኞች የሚቃረኑ ለማስመሰል ይሞክራሉ እንጂ በመቀናጀት የሚሰሩ መሆናቸውን ደርሰንበታል ሲሉ በቅርቡ በተካሄደው የጨፌ ኦሮሚያ ጉባኤ ላይ ለሕዝብ ይፋ ያደረጉ ስለሆነ ይህ እውነት አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው

ስለዚህ የዜጎች መፈናቀል የጽንፈኞች የፖለቲካ ገበያ እንዲደራ ያደረገ ጉዳይ መሆኑ ግልፅ ሆኗል፤ራሳቸው ተቀናጅተው ሰላም በማደፍረስ ዜጎች እንዲፈናቀሉ ካደረጉ በኋላ “መንግስት ዜጎቹን መከላከል አልቻለም” የሚለውን መልዕክት ለማስተላለፍ ከውስጥም ከውጭም ጩኸት እንዲሰማ በማድረግ በመንግስት ላይ ጫና እንዲፈጠር ተደጋጋሚ ጥረት አድርገዋል

ይህ ስትራቴጂያቸው የሚፈልጉትን ስኬት እንዲያስመዘግብላቸው ያደረጉት መፍጨርጨር በሁሉም ነዋሪዎች ላይ ጉዳት ያደረሰ ነው ኦሮሞም ተጎድቷል አማራም ተጎድቷል ሁለቱም ከሞቀ ቀዬአቸው ለመፈናቀል ተገደዋል፤የሰዎች ሕይወት ጠፍቷል ዜጎች በአመታት ልፋት ማፍራት የቻሉት ንብረት ወድማል

የመፈናቀሉ አደጋ የአማራ ተወላጆችን ብቻ ለጉዳት የዳረገ ነው የሚለው የአማራ ጽንፈኛ ክስ አሁንም ቀጥሏል፤ በተለይም ሁሉም ኦሮሞ ሰውን እንደሚገድል እንደሚያፈናቅልና ንብረት እንደሚዘርፍ በአጠቃላይ ጭራቅ አድርገው በመሳል የጥላቻ መርዛቸውን በመርጨት ላይ ይገኛሉ፤ እነዚህ ኃይሎች ሁሉም ኦሮሞዎች ላይ ፀያፍ ስድቦችን ሲያዘንቡ በመዋል የአማራን ሕዝብ መጥቀም የሚችሉበት ሁኔታ የለም

ሌላው፤የሸገር ከተማ አስተዳደር ሕገ ወጥ ግንባታዎች ለመከላከል በቅርቡ የወሰደው እርምጃ የአማራ ተወላጆችን ለማፈናቀል የተወሰደ እንደሆነ በማስመሰል የአማራ ጽንፈኞች የፖለቲካ ገበያቸውን እስከ አሁንም ደረስ አድርተዋል፤ሆኖም የሕገ ወጥ ግንባታዎች ላይ አስተዳደሩ የወሰደው እርምጃ ብሔርን ለይቶ የተፈፀመ እንዳልሆነ የሸገር ከተማ አስተዳደር ባለስልጣናት በቅርቡ በሰጡት መረጃ አረጋግጠዋል

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአማራ ጽንፈኛ ኃይል የሸገር ከተማ አስተዳደር የተመሰረተው አማራን ከፊንፊኔ/አዲስ አበባ ለማፈናቀል የተዘጋጀ ሴራ ነው በማለት በመቃወም ላይ ይገኛል፤በሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ ስም በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ አንዳንድ ፓርቲዎች የጽንፈኛውን ኃይል አቋም በመደገፍ በሸገር ከተማ አስተዳደር መመስረት ላይ በተለያዩ ወቅቶች የተቃውሞ መግለጫዎችን አውጥተዋል፤ይህም ከጽንፈኛ ኃይሎች ጋር በመናበብ እየተሰራ መሆኑ የተረጋገጠበት ሆኗል

ጽንፈኛ ኃይሎች በኢትዮጵያ ሕግ መሰረት ሃሳባቸውን ለሕዝብ በማቅረብ በምርጫ ወደ ስልጣን መምጣት የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ እያለ በሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ በምርጫ ስልጣን የያዘን መንግስት በኃይል በመገልበጥ የቋመጡለትን ስልጣን ለመያዝ የጥፋት ስትራቴጂ አዘጋጅቶ መንቀሳቀስ በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት የለውም

ኢትዮጵያ ዜጎች በመቻቻል በመከባበርና በፍቅር በጋራ የሚኖሩባት አገር በመሆኗ ጽንፈኞች የስልጣን ጥማታቸውን ለማርካት ከታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ተቀናጅተው በሚያገኙት ድጋፍ በሕዝብ የተመረጠን መንግስት በኃይል ከስልጣን ማውረድ የሚችሉበት ሁኔታ ባይኖርም እነዚህ ኃይሎች ለሕዝብ ያላቸውን ንቀት በተግባር በማሳየት ላይ የሚገኙ በመሆናቸው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እረፉ ሊሏቸው ይገባል! ቀጣዩን የጽንፈኞች ስትራቴጂ ይዤ እመለሳለሁ ሰላም ይብዛልን!

Post a Comment

0 Comments