የዳያስፖራ ወገኖቻችንና ማህበራት ለዉጡን በማቀጣጠል፣ የተጋረጡ ችግሮችን በመጋፈጥ ለዉጡ ቀጣይነቱን እንዲያረጋግጥ በማድረግ በኩል በእዉነቱ መልካም ስራ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በቅርቡ በተለያዩ አካባቢዎች ያጋጠመንን ጦርነትና ግጭት መነሻ በማድረግ የሀገራችንን ሉዓላዊነት በሚዳፈር መልኩ በዉስጥ ጉዳዮቻችን ጣልቃ ለመግባት በሞክሩ፣ ልዩ ልዩ ማዕቀቦችን ኢትዮጵያ ላይ በመጫን ሊያንበረክኩን በተንቀሰቀሱ ጊዜ በተለያዩ መንገዶች ሲያጋልጡ፣ ሲታገሉና የኢትዮጵያን ጥቅሞች በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲከበር የበኩላቸዉን ድርሻ ሲወጡ መጥተዋል፡፡ በሀገራቸዉ የተጀመረዉን ሪፎሪም የሚያጠናክሩ ልዩ ልዩ ድጋፎችን ሲያደርጉም ቆይተዋል፡፡ አዎንታዊ ትችቶችንም በማቅረብ መንግስት አሰራሩንና አካሄዱን እንዲያቃና ጥረት አድርገዋል፡፡ ይህ ጥረታቸዉ ከነጉድለቱም ቢሆን አሁንም እንደቀጠለ ነዉ፡፡እነዚህ ጥረቶች የየትኛዉም ዜጋ ግዴታ ቢሆኑም መንግስት ላበረከቱት አስተዋፅኦ እዉቅና ሲሰጥ መጥቷል፡፡
የለዉጥና የሪፎርም ስራና እንቅስቃሴ በባህሪዉና በተፈጥሮዉ በልዩ ልዩ ተግዳሮቶች የተሞላ ነዉ፡፡ አልጋ በአልጋ የሆነ የለዉጥና የሪፎረም እንቅስቃሴ የለም፡፡ በተለይም ደግሞ ከጦርነትና ግጭቶች ወደ አንጻራዊ የሰላም ድባብና በዚህ ላይ የሚመሰረት ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ለዉጦች ለሚሸጋገር ሀገር እጅግ የከበዱ ይሆናሉ፡፡ እንደኛ ባሉ በበርካታ መሰረታዊ ጉዳዮች ያልተግባባ፣ የዜጎች መብትና ብሄራዊ ማንነት ሚዛኑን ጠብቆ ሳይገነባ በቆየበት፣ ተደራራቢና ለዘመናት ሳይፈቱ ቆይተዉ ዛሬ ላይ ዉስብስብ ገፅታ በያዙበት፣ ህገወጥነትና ሌብነት ጎልቶ በሚታይበት፣ አክራሪነትና ፅንፈኝነት በገነገነበት ሀገር በርካታ ችግሮች ማጋጠማቸዉ አይቀሬ ነዉ፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ጉዳት ማድረስና ሀገራዊ ገፅታን ማጠልሸቱም አይቀሬ ነዉ፡፡ ለሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጋሬጣ እንደሆነም ግልጽ ነዉ፡፡ እየሆነ ያለዉም ይኸዉ ነዉ፡፡
ከእነዚህ ችግሮች ተነስተን አንዱን አካባቢ ቅዱስ ሌላዉን ደግሞ እርኩስ፣ አንዱን ማህበረሰብ የችግሩ ገፈት ቀመሽ ሌላዉን ደግሞ በተድላ የሚኖር፣ አንዱን ችግር ፈጣሪ ሌላዉን የዚህ ችግር ተጎጂ ወዘተ… አድርገን መዉሰድ አንችልም፡፡ እይታዉም ወደ ትክክለኛ የመፍትሄ አቅጣጫ አያደርስም፡፡ የችግሮቹ ፈጣሪዎችም፤ የችግሮቹ ገፈት ቀማሽም ሁሉም ናቸዉ፡፡ በተፈጠሩትም ሆነ እየተፈጠሩ ባሉ ጉዳዮች ተዋናይ ያልሆነ የለም፡፡ ስለሆነም ችግሩን መፍታት የሚቻለዉ በመካባበርና በመቻቻል ላይ የተመሰረተ፣ የሁሉንም ተሳትፎና ይሁንታን ያረጋገጠ፤ ስክነት የተሞለበት የጋራ የመፍትሄ አቅጣጫ መያዝና ይህንን በጥብቅ ዲስፕሊን በቁርጠኝት በመተግበር ነዉ፡፡
የኢትዮጵያ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ሪፎርሞች በእነዚህ እዉነታዎች ተጽዕኖና አዉድ ዉስጥ እየተካሄዱ የሚገኙ ናቸዉ፡፡ በሪፎሪሙ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶችም በእነዚህ ዉስብስብ ችግሮችና አውድ ዉስጥ እያለፉ የተመዘገቡ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ ትልቅ የአመራር ጥበብ፣ ትዕግስት፣ የሰከነ ዉይይትና መግባባትን ይጠይቃል፡፡ አንዳንዴ ነገሮችን ለጊዜውም ቢሆን እያዩ እንዳለዩ ማለፍንም ይጠይቃል፤ እጅግ አንገብጋቢ ለሆኑት የቤት ስራዎቻችን ቅድሚያ መስጠት ግዴታችን በመሆኑ። ከሚካሄደዉ የሪፎርም እንቅስቃሴ ጎን ለጎን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚደረገዉም ጥረት በእነዚሁ ዉስብስብ ችግሮች ዉስጥ በማለፍ ነዉ፡፡ በመሆኑም የሁሉም ዜጎች ስክነት የተሞላበት ተሳትፎና ጥረት በእጅጉ አስፈላጊ ነዉ፡፡ የጋራ ሀገር ችግርን በጋራ እንጂ በተናጠል መፍታት አይቻልም፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ጊዜ የሚጠይቁ መሆኑንም መረዳት ያስፈልጋል፡፡
በዚህ ረገድ ከሰሞኑ ከአንዳንድ የዳያስፖራ ወገኖቻችንና ማህበራት የሚደመጠዉ ጉዳይ እነዚህን ነባራዊ እዉነታዎች ግምት ዉስጥ ያስገቡ አይደሉም፡፡ እየተነሱ ያሉ ጉዳዮችን በጥቅሉ ሲናያቸዉ፡-
1) አብዛኛዉ በተሳሳተ መረጃ፣ ከሁከትና ግጭት
ማትረፍ የሚፈልጉ ሃይሎች በፈበረኩዋቸ የተዛቡ
መረጃዎች ላይ ተመሰረተ ነዉ፡፡
2) በኤርትራ በረሃ ሲኳትኑ የነበሩ እንዲሁም በምዕራቡ
ዓለም የተንደላቀቀ ኑሮ እየኖሩ የነበሩና በለዉጡ ወደ
ሀገር ቤት እንዲገቡ ከተደረጉ በኋላ የለመዱት
ኑሮ ስላልተመቻቸዉ ወደዚያዉ የተመለሱ ከሰሞኑ
ደግሞ ህብረተሰቡን ወደ ሌላ ግጭት ለማስገባት
ከከፈቱት የክተት ዘመቻ ጋር በቀጥታ የተቆራኘ
ይመስላል፡፡
3) እየተነሱ ያሉ ጉዳዮች መሬት ላይ ካለዉ ተጨባጭ
እዉነታ ጋር የማይሄዱ፣ በዘላቂነት የኢትዮጵያን
ችግር የሚፈቱ ሳይሆን የሆኑ ቡድኖችን ፍላጎት
ለማሳካት ያለሙ ይመስላል፡፡
4) ሀገሪቱ እያለፈችበት ያለዉን ጦርነትና ረዘም ያለ
ግጭት፣ በድህረ- ጦርነትና ግጭት ሊፈጠሩ
የሚችሉ የማህበራዊ ፖለቲካዊና
ኢኮኖሚያዊ ችግሮችንና እነዚህ ጉዳዮች
በህብረተሰቡም ሆነ በሀገሪቷ
ላይ እየፈጠሩ ያለዉን ጫና በትክክል ያጤኑ
አይደለም፡፡
አሁን ባለንበት ነባራዊ ሁኔታ ለኢትዮጵያና ዜጎቿ የሚያስፈልገዉ በተለያዩ ጠርዞች የቆሙና መላ ህዝባችንን ለግጭት የሚደርጉ ስሁት አመላካካቶችና ድርጊቶችን በጋራ መታገልና ማረቅ፣ በስክነትና ስርዓት ባለዉ መንገድ የተጀመረዉን ሪፎርም ማጠናከር፣ በህዝባችን ላይ ጫና የሚፈጥሩ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን መቀነስ፣ ዳርና ደር ቆሞ ጣት ከመቀሳሳር ይልቅ የየራስን ዉስጣዊ ችግር መፍታትና ከተቻለ ሌሎችን ማገዝ፤ ካልተቻለም እንቅፋት አለመሆን፣ መደማመጥና ለጋራ ዓላማ በአንድነት መቆም ነዉ፡፡ በሚነፍሰዉ ንፋስ ከመወሰድና በሚነሳው አቧራ ከመጋረድ ይልቅ በመርህ ላይ በመቆም ለጋራ ዓላማችን ስኬት በፅናት መታገል ያስፈልጋል፡፡ አገር የሚቀናዉ ከደመናዉ በላይ ሆነው ማየት በሚችሉና በመርህ በሚመሩ ዜጎች ነዉ፡፡
0 Comments