" የባጃጅ አሽከርካሪዎች በቅርቡ ወደ ሥራቸው ይመለሳሉ " -ትራንስፖርት ቢሮ




ፊንፊኔ #Ethiopia መጋቢት 02,2015(YMN) የባጃጅ አሽከርካሪዎች በቅርቡ ወደ ሥራቸው እንደሚመለሱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ አስታውቋል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ምትኩ አስማረ በቅርቡ እየተነሣ ካለው የባጃጅ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ መግለጫ  ሰጥተዋል

የከተማ አስተዳደሩ የባጃጅ አገልግሎትን የተሻለ ለማድረግ የአሠራር ማስተካከያ እያደረገ ነው ያሉት ኃላፊው ይህ ተግባራዊ እስከሚሆን ድረስ የባጃጅ አሽከርካሪዎች እና ተጠቃሚዎች በትዕግሥት እንዲጠብቁ አሳስበዋል።

የባጃጅ ትራንስፓርት መንግሥት የትራንስፖርት አገልግሎትን ማድረስ በማይችልበት የከተማ ዳርቻዎች፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ አገልግሎት መሰጠት እንደተጀመረ አስታውሰው፣ አሁን ላይ አገልግሎቱ እየተስፋፋ ሄዶ በከተማይቱ ውስጥ ከሚገኙ 11 ክፍለ ከተሞች መካከል በስምንቱ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። 

ከተማ አስተዳደሩ አገልግሎቱን ወደ አሠራር ለማስገባት ባደረገው ጥረት 9 ሺህ 950 የባጃጅ አገልግሎት ሰጪዎች በ123 ማኅበራት ተደራጅተው በስምንቱ ክፍለ ከተሞች ላይ እንደሚሠሩ የገለፁት ኃላፊው ብዛት ያላቸው ግን እንዳልተመዘገቡ ጠቁመዋል። 

የከተማ አስተዳደሩ መሠራት ያለባቸውን ሥራዎች እንዳጠናቀቀ በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚመለሱ ተናግረዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ትራንስፖርት ቢሮ የባጃጅ ትራንስፖርት የአገልግሎት አስፈላጊነት በዝርዝር ተጠንቶ ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ ከየካቲት 30/2015 ጀምሮ በከተማዋ በየትኛውም አከባቢ ላልተወሰነ ጊዜ የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት የታገደ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።

ምንጨ:ኢፕድ

Post a Comment

0 Comments