‘’ዶ/ር እመቤት ከፍተኛ የጥርስ ህክምና ማዕከል ‘’በተደጋጋሚ ማስታወቂያም ሆነ በየካ -ኮተቤ ዋና መንገድ ስመላለስ አውቀዋለሁ፡፡እውነት ለመናገር ባለቤቱ ዶ/ር እመቤት የጥርስ ህክምና ማዕከሏ ስፖንሰር ባደረገው የአንድ የእግር ኳስ ቀጥታ ስርጭት በስልክ ተጠይቃ ስትናገር ከመስማቴ በስተቀር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህዝብ ተወካይ መሆኗን አላውቅም ነበር፡፡በቃለ መጠይቁ ወቅት በሰጠችው አስተየያየት ደስተኛ እንደነበርኩ አስታውሳለሁ፡፡አባቷ በምስራቅ ጦር ግንባር ለሀገራቸው መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግና ልጅ ናት።በአባቷ በጦር መውደቅ ምክንያት ወደ ኩባ ተልካ የተማረች የጀግና ልጅ ናት።
ሆኖም ይህችን የህክምና ባለሙያና ስራ ፈጣሪ (Entrepreneur) የተከበረች ሴት ማፈሪያው የማህበራዊ ሚዲያ መንጋ በነውር ጅራፉ ሲገርፋት ታዘብኩና የዶክተሯን ንግግር ደጋግሜ አዳመጥኩ፡፡በእውነት ለራሴ አዘንኩ፣ለሀገሬም አዘንኩላት፡፡ይህ የአሉቧልታ መንጋ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ተጥዶ በጠላው ላይ እየዘመተ እንደምን በዚች አገር የዲሞክራሲ ባህል ሊፈጠርና ሊዳብር ይችላል?
ዶክተሯ አጽንኦት ሰጥታ የተናገረችው የአዲስ አበባ ህዝብ በኑሮ ውድነት መሰቃየቱንና በደህንነት ስጋት መከራ ማየቱን ነው፡፡ወደ አዲስ አበባ የሚፈልሰው ህዝብ የከተማውን የኑሮ ወድነት እንዳናረውና ወደ አዲስ አበባ እህል እንዳይገባ በኬላ መታጠሩ ትክክል አለመሆኑን ነው ያስረዳችው፡፡የአዲስ አበባ ህዝብ በከፍተኛ የደህንነት ስጋት ውስጥ መሆኑን በመጥቀስ በተለይ የአደባባይ በዓላት በመጡ ቁጥር ህዝብ ሽብር ውስጥ እንደሚገባና ‘’ በዓሉ በሰላም ይጠናቀቅ ይሆን ወይ‘’የሚለው የእናቶች ስጋትና ጸሎት እንደሚጨምር ነበር ስሜትን በሚፈትን ቁጭት የተናገረችው፡፡የአደባባይ በዓላት የአዲስ አበባን ህዝብ ለሽብር የሚዳርጉ ከሆነ ህዝብ ከሚሸበር በዓላቱ ቢከለከሉ ይሻላል በሚል አውድ ነበር ስሜቷን የገለጸችው፡፡
ሀሳብን ከአውድ ውጭ መተርጎምና ቃላት ቦጭቆ በማውጣት ማጥላላትን ስራ ያደረገው የሶሻል ሚዲያ መንጋ በዶክተሯ ላይ የእርግማን ዶፉን ማውረድ ጀመረ፡፡ማሽሟጠጡና ማላገጡ አልበቃ ብሎም በሙያዋ ላይ ሊሳለቅባት ከጀለ፡፡ይህ ለዕውቀትና ለስራ ፈጣሪነት ዋጋ የማይሰጥ የፊደል ሽፍታ ይህችን ስራ ፈጣሪ ሐኪም ‘’ ዶክተር መባል የለባትም፣የጥርስ ሐኪም እንደሌላው የህክምና ዘርፍ ከባድ ስላልሆነ ዶክተር መባል የለባትም፣ እንደ አዋቂም አትቆጠርም‘’እስከማለት የደረሰ የማይምነት ልኩን አሳዬ፡፡
ጭራሽም ህዝብ በህክምና ማዕከሏ እንዳይገለገል(Boycot) እስከማሳደም ድረስ ጥሪ አቀረበ፡፡የአደባባይ በዓላት ህዝብን ለደህንነት ስጋትና ለሽብር ድርጊት የሚዳርግ ከሆነ በዓሉ እንዳይከበር ቢከለከል ይሻላል ማለት በዓሉ አይከበር ማለት እንዳልሆነ የሚያሰላስልና ሀሳብን በቀናነት የሚረዳ ህሊናውን ያጣው ይህ ሁከት ናፋቂ መንጋ በምን ትርጉምና አግባብ ነው ‘’የአደባባይ በዓላት እንዳይከበሩ ጠየቀች ‘’ብሎ በጸያፍ ስድብ የሚሰድባት? የአደባባይ በዓል ማክበር አስፈላጊ አይደለም ብላ እንኳ ቢሆን ስህተቷን በጨዋነት ማስረዳት እንጂ እንዴት የነውረኛ ስድብ አተላ ይደፋባታል?
የሚገርም ሌላም ትዝብት አለ፡፡በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የአደባባይ በዓላት የሚያከብረው የአንድ ኃይማኖት ተከታይ ወይም የአንድ አካባቢ ህዝብ ብቻ አይደለም፡፡ ሙስሊሙም፣ ካቶሊኩም፣ ፕሮቴስታተንቱም፣ኢሬቻውም….የየራሱ የአደባባይ በዓል አለው፡፡በዶክተሯ ላይ የዘመተው መንጋ ግን የአንድ ኃይማኖት ተከታይ የሚመስል የፖለካ ነጋዴ መሆኑን መገመት ቀላል ነው፡፡ይህ ብጥብጥ አላሚ መንጋ ሳይጠራ አቤት ማለትን አመሉ አድርጎታል፡፡በቅርቡ በአንድ አካባቢ ‘’ቁሞ ቀር ‘’የሚል ቃል ሲነገር ‘’አቤት ‘’አለ፡፡አቤት ብሎ ግን ቃሉ የሚመለለከተው እኔን ነው አላለም፡፡’’….እከሌ የሚባል ህዝብ ለመስደብ ነው ‘’በሚል የአቤት ባይነት ትርጉም የራሱን ጥላቻ ወደህዝብ ለማሸጋገር ሞከረ፡፡እጅግ አንገት የሚያስደፋው ግን ትናንት የብልጽግና ‘’ ውታፍ ነቃዮች‘’እየተባሉ በዚህ መንጋ ይዘመትባቸው የነበሩ እንደ EMS ያሉ ሚዲያዎች በዶክተሯ ላይ አብሮ ዘማች መሆናቸው ነው፡፡ይህ መንጋ ንግግርን ከአውድ ውጭ እየተረጎመና ቃላትን ለብቻ እየመዘዘ በማብጠልጠልና የሀሰት ዘመቻ በመክፈት ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ አገርና ህዝብ ጠቃሚ ዜጎችን ህሊና እንደጎዳ ግልጽ ነው፡፡አሁንም በዶ/ር እመቤት ላይ የተከፈተው የማጥላላት ዘመቻ ከድሮው የተለየ አይደለም፡፡
የአዲስ አበባ ህዝብ የአደባባይ በዓላት እንዲከበሩ የሚፈልገው ኃይማኖቱና ባህሉ ስለሆነ ነው፡፡የማህበረራዊ ሚዲያ ዘማቹ ግን ለሁከትና ለጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ግብአት ሊያደርገው ነው፡፡ይህ የሁከት ህልመኛ ኃይል በህዝብ ስም መነገዱን ያቆም ዘንድ ዝም ሊባል አይገባም፡፡አገርና ህዝብ የሚያገለግሉ ዜጎቻችን የማፈሪዎች ዘመቻ ሰለባ እየሆኑ አንገታቸውን ሊደፉ አይገባም፡፡
(በዓለምነው አበበ)
0 Comments