በሕገ-ወጥ የዶላር ዝውውርና ሌሎች ወንጀሎች የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ



ፊንፊኔ #Ethiopia መጋቢት 05,2015(YMN) የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል በሕገ-ወጥ የዶላር ዝውውርና በሌሎች ወንጀሎች የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ገለፀ

የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል በሕገ-ወጥ የዶላር ዝውውርና በሌሎች ወንጀሎች የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታወቀ።
በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች መጋቢት 02/2015 ዓ.ም ባካሄደው ኦፕሬሽን በሕገ-ወጥ የዶላር ዝውውር፣ በተለያዩ ሀገራት ሐሰተኛ ገንዘቦችና በብር ህትመት እንዲሁም በሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ የተጠረጠሩ አምስት ግለሰቦችን ይዞ ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን የጋራ ግብረ-ኃይሉ አስታውቋል።
የጋራ ግብረ-ኃይሉ ባካሄደው ጠንካራ ኦፕሬሽን ለሕገ-ወጥ ዝውውር የተዘጋጀ በርካታ የአሜሪካን ዶላር እና የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች የተያዙ መሆኑን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በግለሰብ ደረጃ ከ100 ሺህ ብር በላይ ለድርጅቶች ከ200 ሺህ ብር በላይ በቤትና በድርጅት ውስጥ እንዳያስቀምጡ ያስተላለፈውን ክልከላ በመተላለፍ ለዶላር ግዥ ሊውል የነበረ 601 ሺህ 760 ብር፣ በሦስት ቼኮች ተፈርሞ ለሕገ-ወጥ የዶላር ግዥ ሊውል የነበረ 4 ሚሊዮን 900 ሺህ ብር፣ ሦስት ክላሽንኮቭና አራት ሽጉጦች ከመሰል ጥይቶች ጋር በሕገ-ወጥ መንገድ ይዘው የተገኙ ተጠርጣሪዎችን በመያዝ ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ አስታውቋል።
በሌላ በኩል አንዳንድ የውጭ ሀገር ዜጎች የቱሪስት ቪዛና ሌሎች ህጋዊ መንገዶችን በመጠቀም ወደ ሀገራችን ከገቡ በኋላ ሰወር ያሉ አካባቢዎች የሚገኙ ፔኒሲዮኖችና ሆቴሎችን ለረጅም ጊዜ በመከራየት ሐሰተኛ ዶላርና ብር በማተም የሀገራችንን ኢኮኖሚ ለማዳከም የተሰማሩ ተጠርጣሪዎች ለዶላሩና ለብሩ ማተሚያ ከሚጠቀሙባቸው ወረቀቶችና ኬሚካሎች ጋር በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ የገለፀው የጋራ ግብረ-ኃይሉ ተጠርጣሪዎቹ ይህንን ሕገ-ወጥ ተግባር የሚፈጽሙት አደንዛዥ ዕፅ በመጠቀም እንደሆነም በምርመራ ተደርሶበታል ብሏል፡፡
የተጀመረው ኦፕሬሽን በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ሳይሆን ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር በሚካሄድባቸው በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች ሁሉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለፀው የጋራ ግብረ-ኃይሉ በእነዚህ አደገኛ የወንጀል ተግባራት ላይ የተሰማሩት ተጠርጣሪዎች ከነ-ኤግዚቢቶቻቸው በቁጥጥር ሥር ሊውሉ የቻሉት በኅብረተሰቡ ጥቆማና በጋራ ግብረ-ኃይሉ ጠንካራ ኦፕሬሽን መሆኑን ገልጿል።
ኅብረተሰቡ ላደረገው ትብብር ላቅ ያለ ምስጋና አቅርቦ በየትኛውም አካባቢ በሀገራችን ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጸሙ መሰል የወንጀል ተግባራትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀትና ጥቆማ በመስጠት እያደረገ ያለውን ቀና ትብብር አጠናክሮ እንዲቀልም ጥሪውን አቅርቧል።

ምንጭ (ኢዜአ)

Post a Comment

0 Comments