የኦሮሞ አርቲስቶች በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች ርዳታ የማሰባሰብ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ገለጹ

 


በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች ርዳታ የማሰባሰብ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን የኦሮሞ አርቲስቶች ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አስታወቀ። ኮሚቴውዜጋ ለዜጋው ጋሻ ነውበሚል መሪ ቃል ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል

በድርቅ ለተጎዱ ዜጎችን ለመርዳት በአርቲስቶች የተቋቋመው ኮሚቴ ሰብሳቢ አርቲስት ቀመር የሱፍ ሰሞኑን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤የክልሉ አርቲስቶች አንድ ላይ በመሆን በድርቅ ለተጎዱ የቦረና ጉጂ እና ባሌ ቆላማ አካባቢዎች ለሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን እርዳታ የማሰባሰብ ሥራ ጀምሯል። ኮሚቴው በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ እንዲደረግ የማነሳሳት ሥራ ይሠራል፣ ርዳታ በመሰብሰብ ኅብረተሰቡ ከችግሩ እስከሚላቀቅ የድረስ ድጋፍ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አርቲስት ቀመር ገልጿል።

ኮሚቴው የተጀመረውን ሥራ ከግቡ ለማድረስ የአጭር እና ረጅም ጊዜ እቅድ ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል ያሉት ሰብሳቢው ከኅብረተሰቡ የተገኘውን ድጋፍ በማሰባሰብ በፍጥነት በድርቅ ለተጎዳው ኅብረተሰብ ማድረስ ቀዳሚ ሥራ ይሆናል። በተመሳሳይ 15 ቀናት ውስጥ ኮንሰርት የማዘጋጀት እቅድ አለ፣ በሰፊው ኅብረተሰቡ እጁን እንዲዘረጋ ለማድረግ በክልሉ የሚገኙ አርቲስቶች ከሌሎች ክልሎች እንዲሁም በሀገር ውስጥና በውጪ ከሚኖሩ አካላት ጋር ለመሥራት ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ሥራውን የበለጠ ተደራሽና ስኬታማ ለማድረግ ኮሚቴው ከኦሮሚያ ክልል ቡሳ ጎኖፋ ጋር እንደሚሠራ ገልጸው እስከ አሁን በተሠራው ሥራ ለምግብነት የሚውሉ እህሎች በቆሎ ዱቄት፣ ዘይትና በገንዘብ ለመርዳት ኅብረተሰቡ ቃል እየገባ ሲሆን የተሰበሰበው ርዳታ መጠን ሙሉ በሙሉ ኮሚቴው እጅ ሲገባ ይፋ ይደረጋል። በአርቲስቶች የተጀመረው ዜጎችን የመርዳት ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አርቲስት ቀመር ጥሪ አቅርበዋል።

የኦሮሚያ ፋይን አርት ፕሬዚዳንት አርቲስት ዑመር ጎቤ በበኩላቸው በአሁኑ ሰዓት በድርቅ የተጎዳውን የቦረና ማኅበረሰብ በመጎብኘት ላይ እንደሚገኙ ገልጸው በጉብኝታቸው ወቅት በድርቁ ምክንያት ሕዝቡ ላይ እየደረሰ ያለው ችግር አስከፊ መሆኑን መረዳታቸውን ገልጸዋል። አያይዘውም በድርቁ ምክንያት እስከ አሁን ድረስ ሦስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን እንስሳት መሞታቸውንና ከስምንት መቶ ሺህ በላይ ሰዎች ለተረጅነት መጋለጣቸውን ለተረጅነት ከተጋለጡ ውስጥም 200 ሺህ በላይ አስቸኳይ ርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው መረዳታቸውን ተናግረዋል። በተመሳሳይ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት እና እድሜያቸው 65 ዓመት በላይ የሆኑ አዛውንቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው አይቻለሁ ብለዋል።

አርቲስት አቡሽ ዘለቀ በተመሳሳይ በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳት ከአርቲስቶች ጋር በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል። ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ጋር በመሆን ኅብረተሰቡን ከችግሩ ለመታደግ ጥረት እየተደረገ ነው። እስከ አሁን ድረስ በተደረገው እንቅስቃሴ ለምግብነት የሚውሉ እህሎች መሰብሰቡን ገልጾ በገንዘብ ለመርዳት ለሚፈልጉ ወገኖች የባንክ አካውንት እየተዘጋጀ ነው ብሏል። አርቲስቶች ባሉበት ቦታ ሆነው በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን የመታደግ ሥራ እንዲያፋጥኑ አርቲስት አቡሽ ጥሪ አቅርቧል

 

 

Post a Comment

0 Comments