ውጥረቱን ማን ወጠረው?




የሀሰት ወሬ ጅረት አልደርቅ ሲልና"ረብሻ ተቀሰቀሰ"ድራማ ሲበዛ መስማት-ማየትም ሆነ ማስተባበል ይሰለቻል።በአሁኑ ወቅት ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተጣደው አብዛኛው "ዋሽቶ አዳሪ"በሆነበት÷ሳር ቅጠሉ በጥላቻ ቀበርቾ በታጠነበትና የማህበራዊ ሚዲያው ቀዳሚ ንግድ የሀሰት ወሬ መቸብቸብ በሆነበት በዚህ ዘመን የትኛውን ቅጥፈት ከየትኛው ሀሰት ለይቶ"በህግ አምላክ"ለማለት መሞከር ከንቱ ድካም ነው።
ሆኖም የትናንት ጠዋቱን የሀሰት ድራማ ተመልክቸ ዝም ማለትን አልወደድኩም።ትናንት ማለዳ ከገላን የጋራ መኖሪያ ሰፈሬ ተነስቸ ስራ ቦታየ የደረስኩት ከመደበኛው የስራ መግቢያ ሰዓት ቀድሜ ነው።በሌሊት ተነስቶ ወደ ስራ ቦታ መሄድ የገላን የጋራ ነዋሪዎች"ባህል"ሲሆን እኔም የድሮ ሰፈሬን ሰንጋ ተራን በእንባ ተለይቸ ከተቀላቀልኳቸው ሰባት መስከረሞች ጠብተዋል።ዋነኛ መመላለሻ መስመሬ ደግሞ ከገላን የጋራ መኖሪያ ቤቶች እስከ ሜክሲኮ የተዘረጋው ዋና መንገድ ነው።ሰፈራ÷ኃይሌ ጋርመንት÷ለቡ መብራት÷ጀርመን አደባባይ÷መካኒሳ÷ሳር ቤትና ሜክሲኮ ሰባት ዓመታት ሙሉ ጧት ማታ የምመላለስባቸውና የእጀን መዳፍ ያህል የማውቃቸው ናቸው።
ትናንት ጠዋት ቢሮዬ እንደደረስኩ እንደልማዴ "የማህበራዊ ሚዲያው ዓለም እንዴት እንዳደረ"ለማወቅ በር ሳላንኳኳ ዘው ብዬ ገባሁ።"በጋርመንት አካባቢ ውጥረት ነግሷል÷ረብሻ ተቀስቅሷል÷በሰው ህይወት ላይ አደጋ ደርሷል...."የሚል ወሬ ይዘዋወራል።ከደቂቃዎች በፊት በተለመደው ሰላማዊ ሁኔታ ያለፍኩበት መንገድ/አካባቢ እንደምን "ውጥረት ነገሰበት"ወሬ ፋብሪካ ሆነ?
በተለምዶ ኃይሌ ጋርመንት የሚባለው አካባቢ በሰውና በተሽከርካሪ ፍሰት የሚጨናነቅ ነው።ብዙ ህዝብ የሚኖርበት የጋራ መኖሪያ ቤቶችና አዲሱን የአፍሪካ "CDC""ህንፃና የነፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ጨምሮ በርካታ የተለያዪ የንግድ ተቋማትና መኖሪያ ህንፃዎች ይገ ኙበታል።"የጨረቃ ቤቶችና ነዋሪዎች ይገኙበታል"የሚባለው "ሰፈራ"እና የወ/ሮ አዳነች አቤቤ ፕሮጀክት የሆነው የከተማው ሰፊ የአትክልት ተራም ከጋርመንት ጋር ዓይንና አፍንጫ ናቸው።በሰፈራና በጋርመንት መካከል የሚርመሰመሰው ባጃጅ ብዛት አስገራሚ ነው።የጋርመንት ሰፈር ልብ የሆነው "ላፍቶ አደባባይም በአራት አቅጣጫ መንገዶችን ያከፋፍላል።ወደ ቃሊቲ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ-መገናኛ÷ወደ ጀርመን አደባባይሜክሲኮ÷ወደ ሰፈራ -ገላን ኮንዶሚኒየም÷ወደ ጀሞ-ሰበታ መስመሮች ላፍቶ አደባባይ የፈቀደላቸው ናቸው።
ይህ አካባቢ ነው እንግዲህ "በረብሻ ተናወጠ"የሚል በፈጠራ ቪዲዮ የታገዘ ድራማ የተሰራበት።በነገራችን ላይ በተለይ የአትክል ተራው ከተከፈተ ወዲህ በአትክልትና ፍራፍሬ ሻጭና ከመርካቶ ሳይቀር በሚመጡ ሸማቾች አንዲሁም ከገጠር በብዛት ፈልሰው በመጡ የጉልበት ሰራተኞች ትርምስ አቅልን ያስታል።"ጋርመንት አካባቢ በረብሻ ተናወጠ"የሚለውን ሀሰተኛ የፈጠራ ወሬ በምስል እንዲያጅብ ታስቦ የተለቀቀው "ቪዲዮ"እጅግ አስቂኝና ቀሽም ትወና መሆኑን ለመረዳት "video editor"መሆንን አይጠይቅም።ከጋርመንት አካባቢ ጋር የማይመሳሰል የሰዎች እንቅስቃሴና የሰዎች ጫጫታ ጋር ተቀነባብሮ ለዕይታ የቀረበልን ነው።ከሁሉም የሚያሳዝነውና የጥላቻን ለከትየለሽነት የሚያረጋግጠው በአንድ ባጃጅ ውስጥ የተቸወነው ድራማ ነው።አንድ የአዲስ አበባ ፖሊስን የደንብ ልብስ የለበሰ"ፖሊስ"ባለባጃጁን "ለምን ኦሮሚያ ድንበር ውስጥ ገባህ"በሚል አሳፋሪውን ድራማ ይተውናል።ለማስመሰል ሲባል የኦሮሚያን ፖሊስ ወይም ልዩ ኃይል የደንብ ልብስ ቢጠቀሙ ምናለበት
😂
"ጋሽ ፖሊሱ"ይህን ድራማ ሲሰራ አቀራረፁ የወረደ ሰው ካሜራ/ሙባይል ካሜራ ደግኖ ይቀርፃል-"ፖሊሱ"ፈቅዶለት ማለት ነው!!!
ይህ ቀሽም ድራማ የበለጠ ያናደደኝና ያሳሰበኝ በአንድ በጣም በማከብረውና በጋዜጠኝነት ሙያ ብቃትና ልምዱ በማደንቀው የድሮ ወዳጀ ታዋቂ የዩቲዪብ ቻናል መተላለፉ ነው።በእርግጠኝነት ይህ ወዳጀ በአመፅ ቀስቃሽ ድራማ ሰሪዎች ቀሽም ተንኮል ተሸውዷል።ህዝብን ከህዝብ በተለይ ኦሮሞና አማራን ለማጋጨት እረፍት ያጡ ሁከት ናፋቂዎች እንዲህ ዓይነት "ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ"ድራማ እየከወኑ ለሚያከፋፍሉላቸው ድረ ገፆች ማሰራጨት የተለመደ ነው።የሚገርመው እነሱ ሁከት ይቀሰቅስልናል÷ህዝብን ማህበራዊ እረፍት በመንሳት ከመንግስት ጋር ያጋጭልናል የሚሉትን የፈጠራ ድራማ በመስራት አለመድከማቸው ሳይሆን ህዝብ ግምት የማይሰጠውን መናኛ የሀሰት ድራማ የሚያሰራጭላቸው ድረ ገፅ አለማጣተቸውና የሀሰት ወሬውንም የሚያናፍሱላቸው የክፋት ደብተራዎች አለማጣታቸው ነው።
መቼ ይሆን ሀሰትንና ክፋትን ተፀይፈን የምንተወው?
እኔ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሀገራችን የምትገኝበት ፖለቲካዊ÷ኢኮኖሚያዊ÷ማህበራዊና የደህንነት ስጋት ውጥንቅጥ በእጅጉ ያሳስበኛል።በተለይ ዘረኝነትና ጥላቻ የፈጠረው ስጋት ያስጨንቀኛል።ከአንዳንዶች ጋር የማልስማማ ውስብስብ ችግሩን ከፈጠሩትና ከአባባሱት ኃይሎች ማንነትና በመፍትሄ ፍለጋው መንገድ ነው።ህዝብን ማህበራዊ እረፍት ለመንሳትና አገርን ወደከፋ አለመረጋጋትና የእርስ በእርስ ግጭት ለማስገባት የሚመረትን ማናቸውንም የሀሰት ወሬና የሚከወን የጥላቻ ድራማ አጥብቄ መቃወሜን እቀጥላለሁ-የጋርመንቱን ድራማ ጭምር።ጋርመት ሆይ! የአትክልትና ፍራፍሬውን ነገር አደራ!!

በዓለምነው አበበ

Post a Comment

0 Comments