ፊንፊኔ #Ethiopia ሚያዝያ 05.2015(YMN) ፍላጎታቸውን መሠረት በማድረግ መንግስት በመደባቸው ተቋማት ለመሥራት ደስተኛ እና ዝግጁ መሆናቸውን በደቡብ ወሎ ዞን የተመደቡ የአማራ ልዩ ኃይል አባላት ተናገሩ።
በየወረዳው በተለያዩ የጸጥታ ተቋማት የተመደቡ የልዩ ኃይል አባላት በዛሬው ዕለት የደቡብ ወሎ ዞን አመራሮች በተገኙበት በደሴ ከተማ ሽኝት ተደርጎላቸዋል።
መንግስት ለላቀ ተልዕኮ የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ማደራጀቱ ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንንም በደስታ እንደተቀበሉና በሚሰጣቸው ሥምሪት ለመስራት ፈቃደኛና ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በማኅበራዊ ሚዲያ ልዩ ኃይሉ እንዲፈርስና ትጥቅ እንዲፈታ ተደርጓል የሚለው አሉባልታ ነው ያሉት አባላቱ፤ እውነታው ተነግሯቸው በሚፈልጉበት ዘርፍ ከነትጥቃቸው ምደባ ተሰጥቷቸው መሠማራታቸውን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ መንግስት በሚያሠማራቸው ግዳጆች ሁሉ ለመሠማራት ቁርጠኛ መሆናቸውንም ነው የገለጹት።
የደቡብ ወሎ ዞን ሠላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ አህመድ መሐመድ በበኩላቸው፤ልዩ ኃይሉን መልሶ የማደራጀት ሥራ እንደ ሀገር አንድ ጠንካራ የሆነ የጸጥታ መዋቅር ለመገንባት ዓላማ ያለውና በሁሉም ክልሎች እየተተገበረ የሚገኝ ነው ብለዋል።
ይህም በክልል ደረጃ የሚመለከታቸው አካላት ውይይት ያደረጉበትና የጋራ መግባባት የተደረሰበት መሆኑንም ገልፀዋል
ምንጭ:-ደቡብ ወሎ ዞን ኮሙኒኬሽን መምሪያ
0 Comments