አገሩን ተውለት እስኪ ይኑርበት!



ያገሩ ባለቤት እሱ ነው ባላገር፣
የመሬቱ ጌታ በአፈር ውስጥ የሚያድር፣
ነፍሴ እምታመልከው ይሄ ነው የኔ አድባር፣
የስጋ የነፍሴ እሱ ነው የኔ ዘር፣
አገር ለማስከበር አፈር ለብሶ እሚኖር፣
መልካው ሰላም ሲያጣ ፈጥኖ እሚንደረደር፣
ለዳር ለድንበሩ ነፍሱን የሚገብር፡፡
ይሄው ባለመብት ያገሩ ባለቤት፣
አፈሯን የሚለብስ ችግር የመጣለት፣
አቧራ እሚታጠን እምቢ ባይ ለጠላት፣
አገሩን ተውለት እሱ ነው ባለቤት፣
የሰላሙን ደጃፍ በሩን አትንኩበት፣
በብሶት ትረካ ልቡን አታቁስሉት፡፡
አገሩ ሲታወክ አፈር ለብሶ እሚደርስ፣
ነፍሱን የሚገብር ሰላም ሲደፈርስ፣
አገሩን ተውለት እሱ ነው ባለቤት፣
ጥይት የሚዘራ ቀውጢ የመጣለት፣
በቆሎ እሚዘራ ሰላም የሆነለት፣
ባገሩ እሚበይን እሱ ነው ባለቤት፡፡
ከችግር ርቀህ መከራ አትጥራበት፣
ከሞት ማዶ ሆነህ ሞት አታውጅበት፡፡
ከቻልክ አይዞህ በለው፣ሰላም ዘምርለት፣
ጥላቻ እንዲጠፋ ፍቅር ስበክለት፣
ከወደድከው እርዳው አውጣው ከድህነት፣
ካልቻልክ ዝም በል ሁከት አትጥራበት፣
በሱ ደም ነግደህ ስልጣን አትሻበት፣
ሀብት ለመሰብሰብ ጥላቻ አትዝራበት፣
ሰላም ውሎ ይደር ግመሉን ይንዳበት፣
እርስቱ የሱ ነው አገሩን ተውለት፡፡

(በዓለምነው አበበ)




Post a Comment

0 Comments