ፊንፊኔ #Ethiopia መጋቢት 29,2015(YMN) በሌላው ዓለም አንድ ቋንቋ ፣አንድ ገዢ ትርክት፣ አንድ ባህልና አንድ ሃይማኖት መሠረት በማስያዝና በዚያ መስመር ላይ ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች እንዲመላለሱ ፤ እንዲያ እንዲኖሩ በመወሰን አንዳንዴም በማስገደድ ሀገር ለመመስረት እና ለመገንባት የተደረገው ሙከራ ለግዜው ፍሬ ያፈራባቸው ሀገራት ቢኖሩም እየቆየ የሚፈነዳ የሰዓት ቦምብ እንደመቅበር ያለ ችግር እንደሚያስከትል በታሪክ መስመር ላይ ከተለያዩ ሀገራት ልምዶችና ተሞክሮዎች በቀላሉ መረዳት እንችላለን፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የቋንቋ ብዝሃነት፣ የባህል ብዝሃነት፣ የእምነት ብዝሃነት ፣ የታሪክ ብዝሃነት፣ የአመለካከት እና የአስተሳሰብ ብዝሃነት በእጅጉ በሚስተዋልባቸው እና መገለጫቸውም በሆኑ ሀገራት እና ህዝቦች በመደመር መስመር ላይ የጸደለ ሕብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነት ብልጫ ያለው ምርጫ ሳይሆን የውዴታ ግዴታ ነው፡፡
ሕብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነት ከወገንተኝነት በላይ ሀሳቡ ድንበር አልባ ነው፡፡ ፈረንሳዮቹ Liberté, égalité, fraternité ብለው የአብርሆትን ዘመን አቀጣጥለውበታል-ተጠቅመውበታል -ሀገራቸውን አበልጽገውበታል፡፡ ትርጉሙም ነፃነት እኩልነት እና ወንድማማችነት/እህትማማችነት ማለት ነው፡፡
በመደመር መስመር ላይ የጸደለ ሕብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነት መዳረሻው ‹‹የራሴን እምነት እመን! - የአንተን ተው!››፣ ‹‹የእኔን ባህል ኑር -የአንተን ባህል ተው!›› ፣ ‹‹ የእኔን ቋንቋ ተናር! -የአንተን ተው!›› ፣ ‹‹የእኔን ሐይማኖት ተቀበል! - የአንተን ተው!›› ወዘተ ... ሳይባባሉ ከሀገር አልፎ ድንበር አልባ ወንድማማችነትን መመስረት ነው፡፡
ከወገንተኝነት ርቆ ፣ ከስጋ ዝምድና በላይ በሰብአዊነት ተዛምዶ፣ ከአካባቢያዊ ስሜቶች ተሻግሮ ፣ ከሐይማኖታዊ ማንነትም በልጦ ወንድማማችነትን በማጎልበት በሰብአዊነት ላይ የተመሰረተ ግለሰባዊ እና ማህበረሰባዊ ግንኙነቶችን ማሳደግ ነው፡፡
ሕብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነት ‹‹የማንም ነፃነት፣ ባህል፣ቋንቋ፣ ታሪክ ወዘተ ... ከማንም አይበልጥም! - አያንስም!›› በሚል ጽኑ እምነት የጠቅላይነትን እና የገዢነትን ጥማትና አባዜ በእኩልነት መንፈስ ይሞግታል፡፡ የልዩነት ሽኩቻዎችን እና ‹‹የእኔ ይበልጥ!-ያንተ ያንስ!›› አባዜዎችን እኩልነትን ፣ መከባበርን እና መደማመጥን መሠረት ባደረገ የጋራ ዓላማ ለመግራት ይሞክራል-ይጥራል፡፡
‹‹የእኔ ይበልጥ!-ያንተ ያንስ!›› ድርቅት የጋራ ቋንቋችንን ለቅሶ ከማድረግ የዘለለ አንድም ሀገራዊም ሆነ ህዝባዊ ፋይዳ እንደሌለው በማመን ፍቅርን ፣ መተሳሰብን ፣ መደጋገፍን ይሰብካል፡፡
በጠቅላነት፣ በገዢነት እና በአግላይነት መስመር ወደ ቀደመ ክብሯ እና ስሟ የምትመለስ ኢትዮጵያ ፤ ከተንደረደረበት ቁልቀለት ወደ ከፍታ ማማ የሚወጣ ህዝብ አይኖርም፡፡
ከተንደረደርንበት ቁልቀለት ወደ ነበርንበት ከፍታ ለመውጣት መመለሻዉ ዳገት ነው! የምንሄድበት መንገድ ስንመለስ ይረዝምብናል!
ይህን ረዥም እና አድካሚ ዳገት ሕብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነት እና በመደመር መንፈስ መንገዱን ማሳጠር -ድካሙንም መቀነስ አማራጭ ሳሆን ግዴታ ነው!
ወንድማማችነት ለኢትዮጵያውያንተፈጥሮአቸው እንደሆነ እልፍ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ከሰማንያ በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ተከባብረው ተዋደው የሚኖሩባት ኢትዮጵያ ሲባል እንደው ለማለት ብቻ ያህል የሚባል ሳይሆን ሁሉም የአገሪቱ አቅጣጫዎች ብንቀሳቀስም ባህሉ ቋንቋ እሴቱ ማህበራዊ መሠረቱና መልኩ ሁሉ የጋራ እንደሆነ የሚያሳይ በርካታ ውብ መልኮችን እናገኛለን ፡፡
በመሆኑም ተጋምደው -ተዋልደው የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከማለት ይልቅ ተዋህደው አንድ ሆነው የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የሚለው አገላለጽ በእጅጉ የሚሰምር ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ተከባብረው ተፈቃቅደው መኖር እንዲችሉ ከዚህ የተሻለ ማለትም ከሕብረ-ብሄራዊ ወንድማማችነት የሚመረጥ ወይም ደግሞ የሚበልጥ ሌላ መንገድ አለ ብሎ መውሰድ እጅጉን ያዳግታል። ምክንያቱም እኛ ለህብረብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለአብሮነትና በጋራ ለሚደረግ እድገትና የብልጽግና ጉዞ እጅጉን የምንመች ህዝቦች መሆናችን ነው፡፡
ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ለማለት በሚያስችል መልኩ በደም የተዋሃድን፣ በታሪክ የተጋመድን፣ በባህል የተዛመደ እና አንዱን ከአንደኛው ለመለየት፤ የአንደኛውን በሌላኛው ላይ ለመጫን የሚያስቸግር የታሪክ ስሪት እና ዳራ ያለን ህዝቦች ነን፡፡ በመሆኑም የአግላይ- ጠቅላይ ትርክቱም ሆነ ትርክቱ ያመጣውን መዘዝና ጦስ በሌላ ስህተትና በማግለል ፣ በመገለል ወይም ደግሞ በሌላው መገለልን ተቀብሎ የተገልሎ እና አግልሎ ኑሮን መፍቀድ በፍጹም የሚያዛልቅ ጎዳና እና ምርጫ አይደለም፡፡ ከአፍሪካ ሰማይ ስር፤ ከሰው ልጅ መገኛ ከኢትዮጵያ የፈለቀው መደመር ይሉት ትልቅ መስመር የሚያቀነቅነው እና ኢትዮጵያዊያን ብንኖርበት፣ ብንለው ፣ብንሰብከው እና ብናጸናው የተሻለ ነገን ይፈጥርልናል ብለን የምናምንበት እና ለስኬቱም ጠንክረን የምንሰራለት መስመር በብዙ ልምድ፣ በብዙ ንባብና በብዙ ጥናት ዳብሮና በልጸጎ ለኢትዮጵያውያን ከብልጽግና መስራችና ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተሰጠ የሚያሻግረን -የሚያዛልቀን መስመራችን ነው፡፡
መንገዳችን መደመር ፤መድረሻችንም ብልጽግናና መሻገር እንደሆኑ በአንድም በሌላ መንገድ - በአንድም በሌላ መድረክ ተደጋግሞ የተባለ ጉዳይ ነው:: በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያ የምትባለውን ሁላችንም የምንወዳት፤ እሷም ሁላችንንም የምትወደንና የምትፈቅደን ሀገር በአፍሪካ ምድር ላይ ህልው ሆና ለመላው የጥቁር ህዝቦች እና ለአፍሪካ እንደልማዷ የነፃነት ቀንዲል እያበራችን እንድትዘልቅ የሚያወጣን መንገድ መደመር እና ሕብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነት ብቻ እንደሆነ ብልጽግና ያምናል፡፡ አምኖም ይሰራል፡፡
የፖለቲካ አካሄድና ርዕዮት እንደ ፓርቲዎች እንደ ፖለቲካ ልሂቃንና ተመራማሪዎች እንደየ ጊዜው እና የግለሰቦችን አረዳድ፣ ፍላጎትና እምነት የሚወሰን ቢሆንም የትኛውም ቅኝትና የትኛውም የፖለቲካ ርዕዮት ሀገርን እና ህዝብን ህብረብሄራዊ ወንድማማችነትን ደፍቆ በማግለል እና በመጠቅልል የአይ-አዎ ቅኝትን ለማስኬድ መሞከር ትርፉ ወድቆ መሰባበር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ከህብረብሄራዊ ወንድማማችነት፣ ከመደመር፣ ከአብሮነት፣ ከመተቃቀፍ፣ ከመደጋገፍ እና ታላቅ ኢትዮጵያን ለማቆም እና ለማጽናት በጋራ ከመሰለፍ የተለየ አካሄድ ያለው የፖለቲካ አስተምህሮትም ሆነ አይዶሎጂካዊ ርዕዮት ለኢትዮጵያ የሚበጅ እንዳይደለ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ የያዝነው ዓላማ ሕብረ-ብሔራዊ እና የበለጸገች ኢትዮጵያን መገንባት ነውና!!
ይህን ዓላማ ለማሳካት አጭር እና አድካሚ ያልሆነው መንገድ መርጠናል!
እሱም በመደመር መስመር ላይ የጸደለ ሕብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነት ነው!
የዛሬንው ጽሁፌን ‹‹ሳይቸግር ጤፍ ብድር›› ከተሰኘው የተፈሪ ዓለሙ ግጥም ውስጥ በመዘዝኳቸው ሁለት ስንኞች እቋጫለሁ፡፡
ዥንጉርጉር እኮ ነው ሰማይ እና ምድሩ፤
ልዩነት ቢበዛም አይጠብም ሀገሩ፡፡
(በአዲሱ አረጋ)
0 Comments