"በህቡእ በመደራጀት አሰቃቂ ግድያ እየተፈጸመብን ነው " የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ

 




ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሰላምና ጸጥታ ቢሮ በወቅታዊ ጉዳዮች የተሰጠ መግለጫ

የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ከሕግ የራቁ የታጠቁ ኀይሎችን ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ እየሠራ መኾኑን አስታወቀ።

በሀገራችን የተረጋጋ ሰላም እንዲሰፍን የክልላችን የፀጥታ ተቋማት አመራሩና አባሉ ከሰላም ወዳዱ ኅብረተሰብ ጋር በመመካከር ከእርስ በርስ ግጭት የመውጣት ባህል እንዲዳበር መንግሥት ሆደ ሰፊ በመኾን ለሰላም በሩን በመክፈት በሰፊው ሥራ እየሠራ ይገኛል።

በተለይም ከመጋቢት 5 /2015 . ጀምሮ የክልል ከፍተኛ አመራሮች በሰሜን ወሎ፣ በሰሜን ሽዋ እና በሰሜን ጎንደር ዞኖች በኢ-መደበኛ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን በሰላማዊ መንገድ በአካባቢያቸው በሰላም አስከባሪና ሚሊሻ ሠራዊት እንዲደራጁ በመንግሥት ስምሪት ውስጥ መሥራት የማይፈልግ ወደ ግል ሥራው እንዲገባ ተከታታይ የውይይት መድረክ ፈጥረናል።

መንግሥት ሕግ ለማስከበር አቅም ሳያንሰው የሰላም ውይይትን በማስቀደሙ የክልሉን መንግሥት አመራር አልባ ለማድረግ በህቡእ በመደራጀት አሰቃቂ ግድያ እየተፈጸመብን ይገኛል። ሕግ ለማስከበር የገባውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ያልኾነ ስም በመስጠት ለኅብረተሰቡ የጥላቻ መንፈስ ለመፍጠር የበሬ ወለደ ታሪክ በማኅበራዊ ሚዲያ ሲቀሰቀስ ይውላል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለአማራ ክልል ሕዝብ ሕይወቱንና ደሙን የሰጠ፤ በችግር ጊዜ አብሮ መከራ ያየ፤ የአማራ ክልል ሕዝብም ለመከላከያ ሠራዊታችን ፍቅሩንና አለኝታነቱን በተግባር ያሳየ አብሮት የሞተ የደማ እውነተኛ ሠራዊቱን የሚያከብር ሕዝብ ነው። በተከፋይ አክቲቪስቶች የሐሰት ትርክት ሳንሰማ ለሕግ መከበር ሕዝባችን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ እናቀርባለን።

የክልሉ መንግሥት ከሀገር ሽማግሌዎችና ከሃይማኖት አባቶች ጋር አብሮ በመሥራት ከሕግ ርቀው የነበሩ የቅማንት ታጣቂዎችን በሰላማዊ መንገድ ወደ ቀበሌያቸው እንዲገቡ ተደርጓል። በዚህም ከጎንደር መተማ መስመር ሰላማዊ እንቅስቃሴን መፍጠር ተችሏል።

በሰሜን ወሎ ዞን የሚንቀሳቀሱ የምሥራቅ አማራ ፋኖ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ቢያደርሱም አፀፋዊ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በሀገሩ ባህል መሰረት በዘወልድ ሽማግሌዎች መንግሥት ይቅር ብሎ ለሰላም እጁን በዘረጋበት ወቅት በዚህ ኀይል የሚመራው ቡድን አመራራችን በመግደል አሁንም ሕዝቡን እያሸበረ መከላከያ ሠራዊታችን ከሕዝብ ለመነጠል እየሠራ የሚገኝ በመኾኑ አጥፊዎች ለሕግ እስኪቀርቡ የተጀመረው የሕግ ማስከበር ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል በመኾኑ መላው የፀጥታ መዋቅራችንና ሕዝባችን ለሕግ የበላይነት መከበር ዘብ እንድትቆሙ ጥሪ እናቀርባለን

የክልሉ መንግሥት የነፍስ ወከፍ ጦር መሳሪያ የማስወረድ ፍላጎት ሳይኾን ሕጋዊ የማድረግ መኾኑን በተደጋጋሚ የማሳወቅ ሥራ ሠርተናል።በጦር መሳሪያ አዋጅ መሰረት የቡድን ጦር መሳሪያ በማንኛውም መንገድ ይዞ መንቀሳቀስ የማይቻልና ለመንግሥት ገቢ የሚደረግ መኾኑን በመገንዘብ ሚያዚያ 23/2015 . በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በጃዊ ወረዳ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ቡድኖች በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን ለመንግሥት ሰጥተዋል። ዳግም በወንጀል ድርጊት ታርቀውና ካሳ ከፍለው ተሳታፊና ተባባሪ እንደማይኾኑ አምነው በግል ከበደሉት ግለሰብ ጋር ታርቀውና ካሳ ከፍለው ከሕዝብና ከአካባቢው አሥተዳደር ጋር መልካም ግንኙነት በመፍጠር ወደ ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲገቡ የሚያስችል ሥራ የምንሠራ ይሆናል።

በመጨረሻም ለሕግ መከበር መላው ሕዝባችን ከክልሉ የፀጥታ ኀይልና ከሀገር መከላከያ ሠራዊታችን ጎን በመቆም ትብብር እንድታደርጉ እየጠየቅን ሕገ ወጥ በመኾን በቡድን ታጥቆ መንቀሳቀስ በግድያና በዘረፋ የሕዝባችንን ሰላም የምትነሱ ኀይሎች በሰላማዊ መንገድ ለመንግሥት እጃችሁን ከመስጠት ውጭ አማራጭ የሌለ መኾኑን አውቃችሁ እድሉን እንድትጠቀሙበት ጥሪ እናስተላልፋለን።

የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ

ሚያዚያ 24/2015 .

ባሕር ዳር

 

Post a Comment

0 Comments