በንግግር እና በድርድር ላይ የተመሰረተ የሰለጠነ የፖለቲካ አካሄድ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያዊያን ያስፈልገናል -ይገባናልም! ብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያን ህዝቦች ለማስተዳደር ኮንትራቱን ከወሰደ ግዜ ጀምሮ በሀገራችን ሰማይ ላይ የሰላም ፀሐይ እንድትወጣ ፤ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ - ከሰሜን እስከ ደቡብ የሰላም ንፋስ እንዲነፍስ ፤ ኢትዮጵያ አገራችን ሰማይዋም ፣ ምድሯም ፤ ሁሉም ነገሯ ሰላም- ሰላም እንዲሸትና በሰላም እንዲታወድ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል::
ይህንኑ ጥረቱን አጠናክሮ በመቀጠልም በቀጣይ በመላ ሀገራችን ሰላም እንዲሰፍንና ተማሪው በሰላም የሚማርባት ፣ ነጋዴው በሰላም የሚነግድባት ፣ ገበሬው በሰላም የሚያርስባት ፣ ዜጎች በሰላም የሚወጡባት ፣ በሰላም የሚገቡባት ፣ ልጆች በሰላም ቦርቀው ውለው በሰላም የሚያድሩባት ፣ ሙሽሮች በሰላም የሚሞሸሩባት ፣ የተዘራ የሚታጨድባት ፤ የታጨደው የሚወቃባት ፤ የተወቃው በሪቅ በጎተራ የሚሰበሰብባት ፣ የሰላም አድባር ያደረባት ሀገር እንዲኖረን ብልጽግና ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ለወደፊቱም ለሰላም ያለውን ቁርጠኛ አቋም እና ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
በተለይም ከባለፈው የፓርቲያችን መስራች ጉባኤ ማግስት ጀምሮ ለሰላም ያለንን ቁርጠኝነት በተግባር ለማሳየት ባደረግነው ያላሰለሰ ጥረት ስለ ሰላም የሰራናቸው ስራዎች ፍሬ አፍርተው አንጻራዊ የሆነ ሰላም በሀገራችን ሁሉም አቅጣጫዎች እየታየ መምጣቱን የቅርብ የሩቅም - ወዳጅም ጠላትም የሚገነዘበው ሀቅ ነው፡፡
በተለያየ ግዚያት ሰላማችን ሲታወክ ፣ ህዝባችን ሲረበሽ ፣ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ሲጎዳና ኢኮኖሚያችንም እንዲያድግ በምንፈልገው ልክ እና መጠን ሳያድግ - አንዴ ወደፊት አንዴ ደግሞ ወደ ኋላ ሲል የነበረበት ዋነኛ ምክንያት የሰላም እጦት ነው፡፡በሰሜን ኢትዮጵያ ከህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ጋር የተደረሰው የሰላም ስምምነትና የሰላም ስምምነቱ ያስከተላቸው የሰላም ትሩፋቶች ለሀገራችን የሰላም ግንባታ ሂደት ተስፋ የፈነጠቀ እንደሆነም እሙን ነው፡፡
የቤንሻንጉል-ጉምዝ ታጣቂዎችን ወደ ሰላማዊ መድረክና ድርድር እንዲመጡ ፓርቲያችንና መንግስታችን ለመወያየትና ችግሮችን በሰላም ለመፍታት ያደረጉት ዕልህ አስጨራሽ ጥረት ፣ ያላሰለሰ ጥረት እና ትዕግስት ፍሬ አፍርቶ ዛሬ ላይ በክልሉ እና አካባቢው የሰላም ንፋስ ይነፍስ ጀምሯል፡፡
በጋምቤላ ክልልም የጋምቤላ ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ (ጋሕነን) የመንግስታችንን እና የፓርቲያችን የሰላም ጥሪ ተቀብሎ ፤ያነሳውን ነፍጥ መሬት አስቀምጦ፣ መደራደርና መነጋገንር መርጦ ለሰላም ባደረገው ቁርጠኛ ውሳኔና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ፍሬ አፍርቶ በጋምቤላ ክልልና በአካባቢው የሰላም አየር መንፈስ ከጀመረ ዋል አደር ብሏል፡፡
በሀገረ ታንዛኒያ ከኦነግ ታጣቂ ሀይሎች ጋር ሲደረግ የነበረው የሰላም ውይይት እና ድርድር የመጀመሪያው ምዕራፍ ዛሬ እንደተጠናቀቀ መገለጹ ይታወቃል፡፡ ፓርቲያችን ንግግሩ እና ድርድሩ መጀመሩን በራሱ እንደ አንድ አዎንታዊ እርምጃ የሚመለከተው ሲሆን ይህ እርምጃ ወደፊት ገፍቶና ተጉዞ በቀጣይ ፍሬ እንደሚያፈራ ፣ ውጤት እንደሚይዝና እንደሚሰምርም ጽኑ እምነት አለው ፡፡
ድርድር በአንድ ጊዜ ተጀምሮ በአንድ ግዜ ያለመቋጨቱ ፤ ውይይትም በአንድ ጊዜ ተጀምሮ በአንድ ጊዜ ፍሬ ያለማፍራቱና ውጤት ያለማምጣቱ እውነት የውይይትና የንግግር - የክርክርና የድርድር ባህሪ … ጠንከር ሲልም ተፈጥሮ እንደሆነ ዕሙን ነው ፡፡
በሚያስማሙ ነገሮች ላይ እየተስማሙ ፤ በማያስማሙ ነገሮች ላይ ደግሞ እያንሰላሰሉ ፣ እየተነጋገሩ ፣ እየዋሉ ፣ እያደሩ ለሌላ ውጤትና ድርድር ለሚያመጣው የሰላም ስኬት መንደርደር ዘመናዊው አለም የሚጠይቀው የፖለቲካ ቀለም ነው፡፡ ፓርቲያችን እና መንግስታችን በዚህ በጽኑ ያምናሉ፡፡ ዛሬ የተሳኩትን የድርድር አንኳር ነጥቦች ይዘው እሱን እያጠናከሩ በሌላ ድርድር ሌላ ውጤት ለማምጣት ተግተው እየሰሩ በመላ ኢትዮጵያ ሰላም እንዲመጣ እና እንዲሰፍን ከመላ ህዝባችን እና ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ድርጅቶች እንዲሁም ከሌሎች ወዳጅ አጋር ሀገሮች እና ድርጅቶች ጋር በመሆን በቀጣይም ይሰራሉ::
እስካሁን ከሄድንባቸው ችግሮችን በውይይት የመፍታት ተሞክሮአችን የምንማረው ነገር በመነጋገር እና በመደራደር ብቻ እንጂ በመጨቃጨቅና በመነታረክ ለሀገራችን እና ለህዝባችን የምናመጣው ውጤት አለመኖሩን ነው፡፡
በቀጣይም ሌሎች አለመግባባቶች በድርድር እና በውይይት ለመፍታት እንደወትሮው ሁሉ ፓርቲያችን ዝግጁ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ መግለጽ እንወዳለን፡፡
ከዚህም ባሻገር ፓርቲያችን ብልጽግና ለሀገር ሰላም እና እድገት የመጀመሪያና የመጨረሻ አማራጭ መነጋገር መደማመጥ እንጂ መገፋፋት እና ነፍጥ አለመሆናቸውን በጽኑ ያምናል:: በሁሉም የሀገራችን አቅጣጫዎች ስለ ሠላም የሚደረጉ ንግሮችና ድርድሮች በቀጣይም ተጠናክረው የሚቀጥሉ ሲሆን መንግስት በፖሊሲው - ፓርቲያችን ደግሞ በማኒፌስቶው ስለ ሰላም ከገለጹት በላይ ተራምደው እና ሠርተው በሀገራችን ሰላም እንዲመጣ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ እናረጋግጣለን!
(በአዲሱ አረጋ)
0 Comments