ወድቆ የተገኘ ልጅ ጡቷን በማጥባት እርሀብን ያስታገሰችለት ፖሊስ

 






ረ/ሳ ቤተልሄም ምትኩ :- ልጁን ሳየው ሆዴ ተላወሰ እናትነቴ ከፖሊስነቴ በላይ አስገደደኝ እናም አይናችን እያየ በረሃብ ከሚሞት አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ አለብኝ አልኩኝ፤በረሃብ የተጎዳውን ህጻን ህይወት የታደገችው

በተለያዪ ምክንያት ህጻናት መንገድ ላይ ፤ሽንት ቤት፤ አጥር ስር ተጥለው ይገኛሉ ግንቦት 10 ቀን 2015 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ ቀበሌ 09 ገንደ-ገራዳ ድልድይ ስር የሆነው ይሄው ነው፡፡

ገና አንድ ወር የሆነው ህጻን ተጥሎ እሪታውን ቢያሰማም ሰሚ ያገኘው ግን ሰአቱ ገፍቶ ምሽት ላይ ነበር፡፡ በአካባቢው የህጻን ድምጽ የሰማችው የአካባቢው ነዋሪ ወ/ሮ ፋጡማ ድምጹን ወደ ሰማችበት ድልድይ ስር ስትሄድ ያገኘችው ነገር እጅግ እንዳስደነገጣት ትናገራለች፡፡

አንድ ወር ገደማ የሚሆነው ህጻን በጨርቅ ተጠቅልሎ ድረሱልኝ እያለ እሪታውን ያሰማ ነበር ፡፡ የተጣለውን ህጻን እንዳየችው በእናትነት ፍቅር ከወደቀበት አንስታው ወደ ቤት ይዛው ትሄዳለች ነገር ግን ይዛው የሄደችው እናት የምትሰጠው ነገር አልነበራትም እናም ለሊቱን ያለምንም ጡት በቤቷ ያሳልፋል፡፡

አርብ እለት ጸሀይ በድሬዳዋ ከተማ ላይ ብቅ ስትል ነጋ አልነጋ ስትል ያደረችው ግለሰብ ወድቆ ያገኘችውን ህጻን ለፖሊስ ለመስጠት ፖሊስ መሬት ፖሊስ ጣቢያ በማለዳ ነበር የደረሰችው፡፡
ረ/ሳ ቤተልሄም ምትኩ የፖሊስ መሬት ፖሊስ ጣቢያ መርማሪ በመሆኗ በስራ ገበታዋ ላይ እለቱን ነበረች ፡፡

ወድቆ የተገኘ ልጅ ነው ብለው ልጁን ሳየው ውስጤ ተረበሸ የምትለው ቤተልሄም በወቅቱ ህጻኑ ምንም ምግብ ባለመመገቡ ተዳክሞ ነበር እናም የሆነ ነገር እንዲሰጠው ብጠይቅም ይዛው የመጣችው ግለሰብ ምንም ነገር እንደሌላት ለሊትም ምንም ጡት እንዳልጠባ ነገረችኝ ይሄ ልጅ አይናችን እያየ ህይወቱ ማለፍ የለበትም ያለቸው ቤተልሄም እናትነቴ ገፍቶኝ ለህጻኑ ጡት ማጥባት እንዳለበኝ አሰብኩኝ እናም አጠባሁት

ወዲያው ልጁ ብርታት አግኝቶ እንደነቃ ገልጻለች፡፡
የሁለት ዓመት ሴት ልጅ እንዳላት የምትናገረው ረ/ሳ ቤተልሄም ምትኩ ልጄን ጡት እያጠባሃት በመሆኑ ይሄ አጋጣሚ ሲከሰት ለህጻኑ ጡቷን ልታጠባው እንደቻለች ተናግራለች፡፡

ፖሊስነት ፤እናትነት፤ ቅንነትን ደርባ የያዘችው ረ/ሳ ቤተልሄም ምትኩ በመጨረሻ የምለው አለኝ ትላለች ‹‹ፖሊስ በመሆኔ ሁሌም ኩራት ይሰማኛል››፡፡

በአሁኑ ወቅት ወድቆ የተገኘው ህጻን በሙሉ ጤንነት ላይ የሚገኝ ሲሆን ፖሊስ ጉዳዩን እያጣራ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ምንጭ:ድሬ ፖሊስ




Post a Comment

0 Comments