አሜሪካ ስለ ኢትዮጵያ ምን አለች?

 



ፊንፊኔ #Ethiopia ሚያዝያ 25/2015(YMN) አሜሪካ የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ለማብቃት በተደረሰው ስምምነት መሠረት ውጤታማ ትጥቅ የማስፈታት እና ተያያዥ ተግባራትን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ተቆጣጣሪዎች እንዲሰማሩ ጠይቃለች።


ይህንን የጠየቀችው በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተደረሰው ስምምነትን ስድስተኛ ወር ምክንያት በማድረግ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤቷ በኩል ባወጣችው መግለጫ ነው።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምን አለ ?

- የሰላማዊ ሰዎችን ጥበቃ እና ውጤታማ ትጥቅ የማስፈታት፣ ታጣቂዎችን የማሰናበት እና ከኅብረተሰቡ ጋር መልሰው የሚቀላቀሉበትን ሂደት የሚከታተሉ ተቆጣጣሪዎች በማሰማራት በስምምነቱ ላይ የተቀመጡ ሃሳቦች መቋጫ ሊያገኙ ይገባል።

- የኤርትራ ጦር እና ከፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ውጪ ያሉ ኃይሎች ሙሉ ለሙሉ ከትግራይ እንዲወጡ መደረግ እንዲሁም የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የፈጸሙ እና ተሳታፊዎችን ተጠያቂ ማድረግን ጨምሮ ተአማኒ የሽግግር ፍትሕ ሂደት በሰሜን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው።

- ባለፉት ስድስት ወራት በስምምነቱ ትግበራ በርካታ አውንታዊ እርምጃዎች ተወስደዋል።

• በትግራይ ተቋርጠው የቆዩ መሠረታዊ አገልግሎቶች መልሰው ሥራ መጀመራቸው፣

• የሰብአዊ እርዳታ ያለገደብ መቅረቡ፣

• ህወሓት ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ማስረከቡ፣

• እስረኞች መፈታታቸው፣

• ሁሉን አካታች የሽግግር ፍትህ ሂደት መጀመር እና በትግራይ ጊዜያዊ መስተዳደር መቋቋሙ የተወሰዱ አውንታዊ እምርጃዎች ናቸው።

በሌላ በኩል ፥ አሜሪካ በሰሜን ኢትዮጵያ የተከናወነው ስኬታማ የሰላም ሂደት በኦሮሚያ ክልል ሰላም ለማምጣት ዕድል መፍጠሩን አሳውቃለች።

ሀገሪቱ በመንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል የተጀመረውን ንግግር አድንቃለች።

ሁለቱም ወገኖች ለሁሉም ተቀባይነት ያለው ስምምነት ላይ ለመድረስ በቅን ልቦና እንዲደራደሩ አበረታታለሁ ብላለች።

Post a Comment

0 Comments