ፊንፊኔ #ሚያዝያ 28/2015(YMN) በህወኃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ዘመን ተደጋጋሚ "የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር"ችግር የሚፈጠረው በ"ኦህዴድ"ውስጥ ነበር (በብአዴንም ውስጥ ተመሳሳይ ችግር እንደነበር ልብ ይባል)።በዚህ ምክንያትም በተደጋጋሚ "ጠንካራ ግምገማ"የሚካሄደው በኦህዴድ ውስጥ እንደነበር አይዘነጋም።ለዚህ የሚቀርበው ምክንያት "ኦህዴድ ውስጥ ኦነግ የሆኑና አስተሳሰቡን የተሸከሙ ጠባቦች ሰርገው ገብተዋል"የሚል ነበር።በአንድ የኦህዴድ ግምገማ ላይ ራሳቸው አቶ መለስ ዜናዊ ተገኙና የማበጠር ስራቸውን ጀመሩ(ግምገማ የተለየ አስተሳሰብ ያለውንና በስጋት የሚጠረጠርን ሰው መምቻ መድረክ ነው)።በዚህ ወቅትም አቶ መለስ አንድ "ታሪካዊ"ዘለፋ መናገራቸው አደባባይ ወጣ-"ኦህዴድ ሲፋቅ ኦነግ ነው"የሚል።የአቶ መለስን "ግምገማ"ለታሪክ ፍርድ እንተወውና ወደ አሁናዊዉ የሀገራችን ሁኔታ እንመለስ።
በዶ/ር አብይ አህመድ የሚመራው የለውጥ መንግስት ስልጣን እንደጨበጠ ከወሰዳቸው አስገራሚ እርምጃዎች አንዱ ለሚዲያ ነፃነት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነበር።በዚህም ስርጭታቸው በኢትዮጵያ አየር ውስጥ ዝር እንዳይል በር ተቆልፎባቸው የነበሩ መደበኛና ዲጂታል ሚዲያዎች እንደፈለጉ አየሩን ናኙበት።በርካታ አዳዲሶችም እንደአሸን ፈሉ።አንዳንዶቹ ምቹ ሁኔታውን ተጠቅመው አገር ለማፍረስና ህዝብን ከህዝብ ለማፋጀት ዓላማቸው ሲጠቀሙበት በቁጥር በርከት ያሉት ግን "የለውጡ መንግስት ደጋፊ"መስለው ቀረቡ።እንደውም አንዳንዶቹ ራሳቸውን "የለውጥ አርበኛ"አድርገው በመሾም አጉራሽና ፈትፋች ሆነው ለተወሰነ ጊዜ ታዩ።አበው "እንደሰራ አይገድል"እንደሚሉት ለውጡ በትጥቅና ግድያ የታጀበ የተለያየ ሴራና ሸፍ ጥ ፈተና ሲያጋጥመውና የፅንፈኛ ብሔረተኛው ጎራ እየበረታ÷የዘር ጥላቻውና የጭካኔ ግድያው ምድሪቱን እያስጨነቃት ሲመጣ ፈተናው ራሱ "ሲፍቃቸው የከፉ ፅንፈኞችና የዘር ጥላቻ አቀንቃኞች"ሆነው ተገኙ።ውስጣዊ ማንነታቸውም በአደባባይ ተሰጣ።ይህ በአንድ ጀንበር የ360 ዲግሪ ለውጥም ከነባሩ ፅንፈኛና ሁከት ጠማቂ ጎራ የእንኳን ደህና መጣችሁ ጭብጨባ አስተጋባላቸው።"የጀግና ጀግና"ሙገሳና ውዳሴም አጎረፈላቸው።የደም ንግድ ትርፋቸውም ኪሳቸውን አሳበጠው።
አሁን በግንባር ቀደምትነት በዲጂታል ሚዲያው የዘር ጥላቻንና እልቂትን የሚደግሱት እነዚህ የደም ነጋዴዎች ናቸው።የዘር ጥላቻና የሁከት ፈጠራ መዋያና ማደሪያ ያደረጉት ደግሞ የአማራ ክልልን ነው።አንዳንዱ የጥላቻና የሁከት ፈጠራ ቅስቀሳቸው በቪዲዮና ኦዲዮ ቅንብር የታጀበ ነው።አንዳንዱ የቪዲዮና ኦዲዮ ቅጥልጥል ፈጠራቸው የዝቅጠት ወርድና ቁመታቸውን የሚያሳይ ተራ ፈጠራ ሲሆን አንዳንዱ ግን የጭካኔንና የአረመኔነትን ደረጃ የሚለካ ነው።መቼም ቢሆን ሰው ሲገደል የቪዲዮና ኦዲዮ ካሜራ ተዘጋጅቶና ተጠምዶ ሊሆን እንደማይችል የውጊያን ባህሪ ለሚረዳ ሰው ግልፅ ነው።"በለው÷ግደለው÷ጨርሰው..."እየተባለ የሚፈፀም ግድያ ለምን ዓላማ እንደሚቀረፅና በማን እንደሚቀረፅ ማወቅ ቀላል ነው።በወለጋም ሆነ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ወይም በሌሎች ቦታዎች ስናይ የቆየነው ይህን የጭካኔ ድርጊት ነው።ገዳዮቹ እየገደሉ የሚቀርፁበት ዓላማም መንግስትንና ህዝብን በተለይም መንግስትንና የአማራን ህዝብ ለማቆራረጥና በክልሉ ትርምስና አለመረጋጋት እንዲፈጠር መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው።ይህ አረመኔያዊ "ልምድ"ወደአማራ ክልል ገብቶ የጭካኔ እርምጃውን እየጀማመረ ይመስላል።ከሸዋ ምድር የተገኘውና የአማራ ጀግና አመራር የነበረው ግርማ የሽጥላ እንዲገደል መወሰን ብቻ ሳይሆን የመገደሉን መርዶም ግድያው በተፈፀመ በደቂቃዎች ውስጥ በደስታ ሲቃ ተሞልተው ቀድሞ በሰበር ዜና የነገሩን እነዚሁ ፅንፈኛ የሞት ነጋዴዎች ናቸው።ግርማ ከመገደሉ ቀናት በፊትም "half-cast የኦሮሞ ክልስ ስለሆነ የአማራ ጠላት ነው ይገደል"ብለው የወሰኑትም እነዚ የጊዜአችን ዘረኛ ናዚዎች ናቸው።በአሁኑ ወቅት ስሩ አሜሪካና አውሮፓ በሚመዘዝ ፅንፈኛ ኃይል ምክንያት በተወሰኑ የአማራ አካባቢዎች አለመረጋጋት እየታዬ መሆኑ አይካድም።ይህ የጥቂት የአማራ አካባቢዎች አለመረጋጋትም በነዚህ "ሲፋቁ ፅንፈኛና ዘረኛ "ሆነው በተገኙ የዘር ጥላቻ ጠማቂዎችና አክቲቪስቶች ሀሰተኛ ወሬ በግልፅ እየተደገፈ ነው።እጅግ የሚያስቆጨውና የማይሽር ጠባሳ ሆኖ የሚኖረው የመከላከያ ሠራዊታችንን ስምና ክብር ለማዋረድ የሄዱበት እርቀት ነው።ይህን የኢትዮጵያ ህዝብ መመኪያ ሰራዊት÷ይህን በደሙና በአጥንቱ የኢትዮጵያን ህልውና እያስከበረ የሚገኝ ጀግና ሠራዊት በአንድ ብሔር ሠራዊትነት÷ያውም "በኦነግ ሸኔ"ሰራዊትነት ለማዋረድ መድፈር መቼም የማይረሳ ደባ ነው።
በኔ እምነት ይህ በአማራ ህዝብ ስም ከውጭ እስከ ውስጥ ተደራጅቶ ክልሉን የእልቂትና የትርምስ ማሳ ለማድረግ ሲደክም የኖረው ፅንፈኛ ኃይል ዕድገቱን ጨርሷል።በዚህ ጥላቻ ጠማቂ የብሶት ኃይል ድጋፍ ወሮበላ ታጣቂዎች መከራ የጫኑበት ህዝብም በይፋ ማውገዝ ጀምሯል።ይህ ፅንፈኛና ዘረኛ ኃይል ቀለብ በሚሰፍርለት ታጣቂው በኩል ማድረግ የሚችለውን ሸዋሮቢትና አካባቢውን÷ጎንደር ከተማንና አካባቢውን መረጋጋት በመንሳት ዕድገቱን ጨርሷል።በ"ጠላት ተከበሀል"ቅስቀሳ አማራን ወዳጅና ደጋፊ ለማሳጣት ሲሰራ ስለኖረ ከዚህ በላይ የትም መሄድ አይችልም።የዚህ ዘረኛና ፅንፈኛ ኃይል የፖለቲካ ድኩምነት እራቁቱን የቀረውም በዚህ የጠላት ሸመታ ጅልነቱ ነው።ከዚህ በላይ ወደላይም ሆነ ወደጎን ማደግ አይችልም።መንግስት የአማራን ህዝብና ክልል ከዚህ የከፋ ፅንፈኛ ኃይል ትርምስ ለዘለቄታው ነፃ ለማውጣት ህዝቡን ያሳተፈ እንቅስቃሴ ማድረግ አለበት።በተለይ እንደ ሸለምጥማጥ ምርጥ አመራሮቹ እየተበሉበት ያለው የክልሉ መንግስት የተጠናና ዘላቂ የሆነ እርምጃ እንደሚወስድ ይጠበቃል።የዚህ ፅንፈኛ ኃይል ቀዳሚ ዓላማ የክልሉን አመራር ማጥፋትና እንደልቡ ክልሉን ማጎሳቆል እንደመሆኑ ወሳኝ እርምጃ ይጠበቃል።"ሲፋቁ ፅንፈኛ"የሆኑት የደም ነጋዴዎች በአማራ ህዝብ ስም እየነገዱ ሊቀጥሉ አይገባም።
(በዓለምነው አበበ)
0 Comments