ፊንፊኔ #Ethiopia ነሃሴ 01/2015(YMN) በአማራ ክልል የተወሰነውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚያስፈጽመው ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ሕግ የማስከበር ሥራውን በማከናወን ክልሉን ወደ መደበኛ እንቅስቃሴው በአጭር ጊዜ እንዲመለስ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
ለወራት የቆየው እና ባለፈው ሳምንት ተባብሶ ከክልሉ አቅም ውጪ በመሆኑ የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ ገብነት የተጠየቀበት የፀጥታ መደፍረስ፤ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ያለ ግጭት መሆኑ ይታወቃል።
በዚህም ሳቢያ በክልሉ አብዛኛው ክፍሎች ውስጥ እየተካሄደ ባለው ግጭት እና ፍጥጫ የየብስ እና የአየር ትራንስፖርት ተስተጓጉሏል፣ የኢንትርኔት አገለግሎት ተቋርጧል፣ አንዳንድ አካባቢዎችም በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መግባታቸው ተገልጿል።
በዚህም ሳቢያ የአማራ ክልል መንግሥት ጥያቄን ተከትሎ የፌደራሉ መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው አርብ በአማራ ክልል ላይ ለስድስር ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጎ፣ አዋጁን የሚያስፈጽመው ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ አቋቁሟል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ዋና ሰብሳቢ እና የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አግልግሎት ዳይሬክትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በአማራ ክልል የተከሰተውን ችግር ለመፍታት ክልሉን በአራት ኮማንድ ፖስቶች በማዋቀር ሕግን የማስከበር ሥራ እንደሚከናወን ትናንት ምሽት በሰጡት ማብራሪያ ላይ ተናግረዋል።
በዚህ ማብራሪያ ላይ አቶ ተመስገን፣ በአማራ ክልል የተከሰተው በትጥቅ የታገዘው እንቅስቃሴ “የክልሉን መንግሥት በማፍረስ ወደ ፌደራል መንግሥቱ የሚዞር ግብ ያለው” መሆኑን በመጥቀስ በክልሉ የተለያዩ ክፍሎች ሕገወጥነት ተከስቷል ብለዋል።
አቶ ተመስገን “የተደራጁ ዘራፊ ቡድኖች” ያሏቸው በክልሉ ውስጥ የዞን እና የወረዳ ከተሞችን ተቆጣጥረው የፍትሕ እና የሕዝብ ተቋማት አገልግሎት እንዳይሰጡ ከማስተጓጎል ባሻገር “በአንዳንድ አካባቢዎች ማረሚያ ቤቶችን ሰብረው ወንጀለኞችን እንዲያመልጡ እስከማድረግ የደረሰ ውንብድና ፈጽመዋል” ብለዋል።
በአማራ ክልል ሕግ እና ሥርዓትን ለማስከበር እንዲሁም የመንግሥት እና የፓርቲ መዋቅርን የማጠናከር ሥራዎችን ለማከናወን በሚል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ ክልሉን በአራት ኮማንድ ፖስቶች ማዋቀሩን አስታውቋል።
በዚህም መሠረት ጠቅላይ መምሪያው ክልሉን በአራት ኮማንድ ፖስቶች የከፈለ ሲሆን፣ የመጀመሪያው የምዕራብ አማራ ኮማንድ ፖስት የተባለው ምሥራቅ እና ምዕራብ ጎጃምን፣ የደብረ ማርቆስ ከተማን፣ የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን እና ባሕር ዳር ከተማ ያሉበት ነው።
ሁለተኛው ደግሞ የሰሜን ምዕራብ አማራ ኮማንድ ፖስት ሲሆን ሰሜን፣ ምዕራብ፣ ማዕከላዊ እና ደቡብ ጎንደር እንዲሁም የጎንደር ከተማ እና ደብረታቦር የሚገኙበት ነው።
ሦስተኛው ኮማንድ ፖስት ደግሞ ማዕከላዊ ሸዋ የሚባል ሲሆን በውስጡ ሰሜን ሸዋ፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን እና ደብረ ብርሃን ከተማን ያካተተ ሲሆን፣ አራተኛ ደግሞ የምሥራቅ አማራ ኮማንድ ፖስት የሚባለው ኮምቦልቻ እና ወልዲያ ከተሞች የተካተቱበት ሰሜን እና ደቡብ ወሎ እንዲሁም ዋግ ኽምራን ያካተተ መሆኑን የዕዙ ሰብሳቢ ገልጸዋል።
የአስቸኳይ ጊዜውን ለማስፈጸም የተዋቀረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ከአማራ ክልል፣ ከመላከያ ሠራዊት፣ ከብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አግልግሎት፣ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከብልጽግና ፓርቲ እና ከኮምዩኒኬሽን አግልግሎት የተወጣጡ አባላት ያሉት መሆኑ ተጠቅሷል።
አቶ ተመስገን ጥሩነህ በክልሉ ውስጥ የተፈጠረውን ችግር እና የሚነሳ የትኛውንም ጥያቄ መንግሥት በሰላም ምላሽ ማግኘት አለበት ብሎ በጽኑ እንደሚያምን በመግለጽ፣ ሕግ እና ሥርዓት የማስከበሩ ሥራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
0 Comments