የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ባወጣው መግለጫ ፤ በመጀመሪያ ምዕራፍ ዕቅድ በትልልቆቹ የአማራ ክልል ከተሞች ፦
=> ባሕር ዳር፣
=>ደብረ ማርቆስ፣
=>ደብረ ብርሃን፣
=> ላሊበላ፣
=> ሸዋ ሮቢት ላይ አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ " የሕግ የበላይነት እንዲከበር አስደርጌያለሁ " ብሏል።
በእነዚህ ከተሞች " በዘረፋ እና በጥፋት የተሰማራ ቡድንን በመምታት በከተሞቹ ላይ የሕግ የበላይነትን ማስከበር ተችሏል " ሲል ገልጿል።
በአሁኑ ሰዓት ከተሞቹ ከስጋት ነጻ መሆናቸውን የገለፀው ዕዙ ፤ የመከላከያ ሠራዊቱ እና የክልሉ ህግ አስከባሪ አካላት የማጥራት ስራ እየሰሩ ነው ብሏል።
የመጨረሻውን የማጽዳት እና የመልቀም ተግባር በማከናወን ከተሞቹ በአጭር ጊዜ ወደ ተሟላ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለሱ ይደረጋል ሲልም አሳውቋል።
የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ ፦
-ከዛሬ ሐሙስ ነሐሴ 4 ጀምሮ ከላይ በተጠቀሱት ከተሞች መደበኛ የአውሮፕላን በረራ እንደሚጀምር፤
- ከባጃጅና ከሞተር ሳይክል በስተቀር ሁሉም ዓይነት የከተማ የትራንስፖርት አገልግሎቶች ወደ አገልግሎት እንደሚገቡ፤
- የመንግሥት ፣ የማኅበረሰብ አገልግሎት ፣ የንግድ፣ የጤና፣ የፋይናንስ፣ ወዘተ. ተቋማት አገልግሎት እንዲሰጡ እንደሚደረግ አሳውቋል።
በሌላ በኩል ፤ እስካሁን 14 ተጠርጣሪዎችን በአዲስ አበባ ከተማ በቁጥጥር ሥር ማዋሉንና ወደፊትም እንደሁኔታው በቁጥጥር ሥር የሚያውላቸውን ግለሰቦች አስመልክቶ አስፈላጊውን መረጃ ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ገልጿል።
በአማራ ክልል ከተሞች እስከ ነሃሴ 17 የሚቆይ የሰዓት እላፊ ገደብ ተጥሏል
በባሕር ዳር ፣ ጎንደር እና ደብረ ብርሃን ጨምሮ በሌሎች ከተሞች የሰዓት እላፊ ገደብ ተጣለ።
የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ትዕዛዝና ክልከላም አውጥቷል።
- የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ከሚሰጡ ተሽከርካሪዎች፣
- የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ሰጪ ባለሞያዎች
- የፀጥታ አስከባሪ ተቋማት ባልደረቦች ውጪ ለማንኛውም ሰው እና ተሽከርካሪ ከምሽቱ አንድ ሰዐት በኋላ መንቀሳቀስ በጥብቅ ተከልክሏል።
የባጃጅ እና የሞተር ሳይክል እንቅስቃሴ ከነሐሴ 4 እስከ ነሐሴ 17 2015 ድረስ ፈጽሞ መከልከሉ ተገልጿል።
ከባጃጆችና ከሞተር ሳይክሎች በስተቀር ሌሎች የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ከነሐሴ 4 ጀምሮ ወደ ሥራ የመመለስ እና አገልግሎት የመስጠት ግዴታ ተጥሎባቸዋል።
ከዚህ ባለፈ ፤ በባሕርዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ብርሃን፣ ደብረ ማርቆስ፣ ሸዋ ሮቢትና ላሊበላ የሕዝብ የአገልግሎት ሰጪ፣ የመንግሥት፣ የማኅበረሰብና የንግድ ተቋማት ከነሐሴ 4/2015 ጀምሮ ክፍት እንዲሆኑ ታዟል።
የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ ከፈቃዴ ውጪ በአማራ ብሔራዊ ክልል ከተሞች የአደባባይ ስብሰባ፣ ሰልፍና መሰል እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ፈጽሞ የተከለከለ ነው ብሏል።
በማንኛውም መልኩ የህዝብ እንቅስቃሴን የሚያስተጓጉል እና የትራንስፖርት አገልግሎትን የሚያሰናክል ድርጊትም በጥብቅ የተከለከለ ነው ሲል አስጠንቅቋል።
በተጨማሪ ፤ በክልሉ ለጸጥታ ሥራ ከሚንቀሳቀሱ የህግ አስከባሪ አካላት እና ከነዚህ አካላት ፈቃድ ውጭ የጦር መሣሪያ ይዞ መዘዋወር ፈጽሞ ተከልክሏል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሽፋን ከአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ትእዛዝ ውጭ ወቅታዊ ሁኔታን ሰበብ በማድረግ ግለሰቦችን ከመደበኛው ህግ አግባብ ውጪ ማሰር እና ማቆየት፣ የንግድ ቤቶችን ማሸግ እና መሰል እርምጃዎችን መውሰድ በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን አሳውቋል።
0 Comments