ሰሞኑን በክልላችን በአንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው በፅንፈኛና በዘራፊ የስልጣን ጥመኛ ቡድኖች በትጥቅ የታገዘ ሁከትና ብጥብጥ በሁሉም የክልሉ አከባቢዎች ወደ አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት እየተመለሰ ይገኛል።
ከብዙ ትዕግስትና የሰላም አማራጮች በኃላ አሻፈረኝ ብሎ ክልሉን የእልቂትና የትርምስ ማዕከል ለማድረግ በተደራጀ ሁኔታ ከውስጥና ከውጭ ጠላቶቻችን ጋር በማበር በፋይናንስና በፅንፈኛ ሚዲያዎች ታግዞ ጦርነት አውጆ በተለይም ከተሞችን ማዕከል አድርጎ መንግሥትን በመገዳደር ነፍጥ የመዘዘው ኃይል ላይ መንግሥት ህግ የማስከበር ግዴታውን ተጠቅሞ ህግ ወደ ማስከበር ሥራ መገባቱ የሚታወቅ ነው።
በዚህም መሰረት የምንግዜም የሰላም ዘብ የሆነው የሃገር መከላከያ ሰራዊት በእነዚህ ዘራፊና መረን የለቀቁ ፅንፈኛ ቡድኖች ላይ በወሰደው ተመጣጣኝ እርምጃ ሁከት ተከስቶባቸው የነበሩ የክልላችን አብዛኞቹ ከተሞችን ወደ አንፃራዊ ሰላም እየተመለሱ ይገኛል።
በክልላችን ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ፣ ዋግ ኽምራ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ደብረ ብርሃን፣ ሰሜንና ደቡብ ጎንደር አካባቢዎች በንፅፅር ሰላማዊ የሆነ እንቅስቃሴ ያለባቸውና ሕዝባችን በተረጋጋ መንፈስ የዘወትር ህይወቱን እያከናወነ የሚገኝባቸው ናቸው።
በአንፃሩ በክልላችን ርዕሰ መዲና ባሕር ዳር እና ጎንደር ከተሞች መሽጎ ሕዝባችን እንዲታወክ ሲያደርግ የነበረው ዘራፊ ቡድን ከትላንት ምሽት ጀምሮ በተወሰደ እርምጃ ከእነዚህ ፅንፈኛ ቡድኖች ነፃ የማድረግ ሥራ የተሠራ ሲሆን በቀጣይ በሁሉም የክልላችን አካባቢዎች የማያዳግም የህግ የማስከበር ሥራውን አጠናክሮ በመቀጠል ሕዝባችን ያለስጋት የእለት ከለት ሥራውን በተሟላ ሁኔታ እንዲከውን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን እየገለፅን መላው የክልላችን ሕዝብ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን ተሰልፎ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግና ለህግ ማስከበር ተልዕኮው የበኩሉን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ እናስተላልፋለን።
በመጨረሻም ሕዝባችን በፅንፈኛና የጠላት ተላላኪ ሚዲያዎች አሉቧልታ ሳይደናገር ተረጋግቶ ወደ መደበኛ ህይወቱ እንዲመለስ እያሳሰብን ዝርዝር የህግ ማስከበር አፈፃፀሙንና ክልላዊ የሰላም ሁኔታችንን በተከታታይ የምናሳውቅ መሆኑን እንገልፃለን ።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት
ነሃሴ 2/12/2015
0 Comments