የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አገልጋይነት በአንድ ቀን ተለኩሶ የሚጠፋ ሻማ አይደለም አለ



ፊንፊኔ #Ethiopia ጳጉሜ 01/2015(YMN) አገልጋይነት በአንድ ቀን ተለኩሶ እንደሚጠፋ ሻማ ሳይሆን፤ በሕይወት እስካለን ድረስ ልናከናውነው የሚገባ የህይወት መርሕ ነው ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ‘ጳጉሜን 1’ የአገልጋይነት ቀንን አስመልክቶ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለ ቀርቧል፡

መላዉ ኢትዮጵያዊያን በዛሬው ዕለት ጳጉሜን 1/2015 ዓ/ም ለሚከበረው የአገልጋይነት ቀን እንኳን አደረሳችሁ!!
ሀገርና ሕዝብን ማገልገል የህይወት ዘመናችን ታላቁ ዕድልና ኃላፊነት ነው፡፡ ሁሉም ሰው ተወልዶ በህይወት ምድር ላይ በሚኖርበት ዘመን ሀገሩንና ማህበረሰቡን የማገልገል ሰብአዊ ኃላፊነት አለበት፡፡
ሆኖም ግን ሁሉም ሰው እኩል የማገልገል ዕድል ላያገኝ ይችላል፡፡ በህይወት ዘመናቸው ሙሉ ጊዜያቸውን ሕዝብና ሀገርን ለማገልገል ዕድሉን የሚጎናፀፉት ከብዙዎች ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው፡፡
በመሆኑም አገልጋይነት ዕድልና ፀጋ ነው፡፡ ስለሆነም አገልጋይነት ዕድልና ፀጋ መሆኑን ተገንዝበን በተሰማራንበት መስክ ሀገርና ሕዝብን በሚገባ በማገልገል ትርጉም ያለው ህይወት ከመኖርም ባሻገር የአንድ ሀገር የታሪክ አካል የመሆን ውሳኔን መወሰን ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡
ዛሬ የአገልጋይነት ቀንን ስናስብ በተሰለፍንበት የሥራ መስክ የሚጠበቅብንን ኃላፊነት እና ድርሻ በትክክለኛ የአገልጋይነት ስሜት በመወጣት ኢትዮጵያን የማገልገል መንፈሳችንን የምናድስበት ዕለት ነው፡፡
በመሆኑም ዕለቱ “ኢትዮጵያን እናገልግል” በሚል መሪ ቃል ተሰይሟል፡፡
አገልጋይነት በአንድ ቀን ተለኩሶ እንደሚጠፋ ሻማ ሳይሆን፤ በሕይወት እስካለን ድረስ ልናከናውነው የሚገባ የህይወት መርሆዎ ነው፡፡
አገልጋይነት የተወሰኑ ቀናት ክንዋኔ ሳይሆን አንድ ሰው በዘመኑ ሊያከናውን የሚገባው ማህበረሰባዊና ሀገራዊ ኃላፊነት በመሆኑ ዕለቱ ዳግም ለበለጠ አገልግሎት ቃላችንን የምናድስበት ቀን ነው፡፡ ዕለቱ “ሀገሬ ለእኔ ምን አደረገችልኝ ሳይኾን፤ እኔ ለሀገሬ ምን አደረግሁ” ብለን ራሳችንን የምንጠይቅበት ቀን ነው፡፡
ስለሆነም አንድ አገልግሎት ስንሰጥ እይታችን መሆን የሚገባው ከጥቅም ባሻገር ትውልድና ሀገርን ለመገንባት የዜግነትና ሰብአዊ ኃላፊነታችንን ለመወጣት መሆን ይኖርበታል፡፡
እያንዳንዱ ዜጋ ያስተማረውን ሕብረሰተብ ያሉበትን የመልከም አስተዳደር ችግሮች በመፍታት ረገድ ሀቀኛ አገልጋይ ኾኖ ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት የዜግነት ግዴታውን መወጣት ይኖርበታል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

Post a Comment

0 Comments