ስለ መምህራን ጥያቄ ምን ተባለ ?





የዩኒቨርሲቲ መምህራንን የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ለመመለስ " በጥሩ ሁኔታ እየተሠራ " መሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ሥራ አስፈጻሚዎች መግለጻቸውን የማኅበሩ አመራሮች ተናገሩ፡፡

አመራሮቹ ይህን ያሳወቁት ትላንትና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በመምህራን እና በሀገር ጉዳይ ከተወያዩ በኃላ ለሪፖርተር ጋዜጣ በሰጡት ቃል ነው።

የማህበሩ ፕሬዜዳንት ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዮሐንስ በንቲ ፤ እንደተለመደው አሠራር የአጠቃላይ ትምህርት መምህራን በሚሠሩበት አካባቢ የመኖሪያ ቦታ የማግኘት አሠራሩ የሚቀጥል ሆኖ የዩኒቨርሲቲ መምህራንን መኖሪያ ቤት በሚመለከት ግን ውይይት እየተደረገበትና ጥሩ ምላሽ ሊገኝ እንደሚችል እንደተረዱ ተናግረዋል፡፡

" የዩኒቨርሲቲ መምህራን የቤት ጥያቄን በሚመለከት ከዚህ በፊት የተነሳ ጉዳይ አለ፡፡ ውይይት እየተደረገበት ሲሆን ዕልባት እንዲያገኝ እየተሠራበት እንደሆነ ነው የተገለጸልን " ሲሉ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ስላገኙት ምላሽ አስረድተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲ መምህራን ከዚህ በፊት ሲያነሱት ስለነበረው #የደመወዝ ጥያቄን በሚመለከት ማኅበሩ አንደኛው ይዞት የሄደው ጉዳይና የተወያየበት ሲሆን ጠ/ሚኒስትሩ ለደመወዝና መሰል ጥያቄዎች በየደረጃው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እንዳደረጉባቸው እንደነገሯቸው ገልጸዋል፡፡

የደመወዝ ጭማሪውን በሚመለከት፣ የኑሮ ውድነትን በአጠቃላይ የማቅለል ሥራ እንደሚሠራ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹላቸው፣ ይህንንም ለማስተካከል ጥረት እንደሚያደርጉ በውይይታቸው ላይ እንደተነሳ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡ 

የማኅበሩ አመራሮችም ስለ ደመወዝ ጭማሪ ጥያቄ ቁርጥ ያለ ምላሽ ለማግኘት ጠብቀው እንዳልሄዱም ተናግረዋል፡፡


" ማናችንም ደመወዝን በሚመለከት ‹ከዛሬ ጀምሮ ይህን ያህል ጨምረናል› የሚል መልስ አንጠብቅም፡፡ ችግሩ እንዳለና ትኩረት ተሰጥቶ መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ እንዲፈጽም ነው ያነሳነው " ሲሉ የማህበሩ ፕሬዜዳንት ገልጸዋል።

የማኅበሩ አመራሮች ከመምህራን ጥያቄዎች በተጨማሪ ፦

- የሙያ ጥያቄና የመምህርነት ሙያ ምንነትን በሚመለከት፣ 

- የት/ቤቶች አቅምና ግብዓት ፣

- ለመምህራን ምቹ የሥራ ከባቢ መፍጠርን በሚመለከት 

- ማህበሩ ለመገንባት ስላቀደው ህንፃና ሌሎች ጉዳዮችን አንስተው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር መወያየታቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።

Post a Comment

0 Comments