የጎንደር ከተማ ፀጥታ ሁኔታ

  



ፊንፊኔ #Ethiopia መስከረም 16/2016(YMN) በጎንደር ከተማ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ አስመልክቶ በማህበራዊ ሚዲያ የሚናፈሰው መረጃ ፈጽሞ ከእውነት የራቀ መሆኑን የጎንደር ከተማ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ብርጋዴር ጄኔራል ማርዬ በየነ ገለጹ፡፡

ኮማንድ ፖስቱ ጽንፈኛ ቡድኑ ላይ እየወሰደ ካለው እርምጃ ባሻገር የከተማዋን ነዋሪዎች በማወያየት ባከናወነው ስራ የከተማዋ የሰላም ሁኔታ መሻሻሉን ተናግረዋል።

ጽንፈኛ ቡድኑ የኢትዮጵያን ህልውናና ሰላም ከማይፈልጉ አካላት የሚላክለትን ፍርፋሪ በመጠቀም ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት የሚፈጽም የህዝብ ጠላት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ኮማንድ ፖስቱ ከህዝብ ጋር ባደረገው ውይይትም ህብረተሰቡ የጽንፈኛ ቡድኑን እኩይ ድርጊት በግልጽ ማንሳቱን ጠቅሰዋል፡፡

ነገር ግን ከጽንፈኛ ቡድኑ ጎን የተሰለፉ አንዳንድ አካላት በማህበራዊ ሚዲያ የሃሰት መረጃዎችን በማሰራጨት ህዝብ ለማደናገር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም ባለፉት ቀናት "ብርጋዴር ጄኔራል ማርዬ ተገድለዋል" በሚል በማህበራዊ ሚዲያ የሃሰት መረጃ ሲያሰራጩ መቆየታቸውን አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም "ክፍለ ጦር ደመሰስን፤ ታንክ ማረክን፤ አውሮፕላን ጣልን" የሚሉ የበሬ ወለደ መረጃዎችን ሲያሰራጩ መቆየታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም ህብረተሰቡ ሆነ ብለው የሃሰት መረጃ በሚያሰራጩ የጽንፈኛው ቡድን አባላት መደናገር እንደሌለበት አስገንዝበዋል።

ኮማንድ ፖስቱ በጽንፈኛ ቡድኑ ላይ ከሚወስደው እርምጃ ባሻገር ህዝብን በማወያየት ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እየሰራ መሆኑንም የተናገሩት ብርጋዴር ጄኔራል ማርዬ፤ በዚህም የመከላከያ ሰራዊቱ የተሰጠውን ግዳጅ በብቃት እየተወጣ ነው ብለዋል፡፡

በቅርቡ በጎንደር ከተማ በአንድ ፖሊስ ጣቢያ ላይ ተኩስ በመክፈት ለማምለጥ በሞከሩ የጽንፈኛው ኃይል አባላት ላይ እርምጃ በመውሰድ የከተማዋን ሰላም ማስጠበቅ መቻሉንም ገልጸዋል፡፡

ሰራዊቱ ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ውጤታማ ስራ እያከናወነ ነው፤ ለዚህ ደግሞ ደጀኑ ህዝባችን ምስክር ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

Post a Comment

0 Comments