ግዙፍ ሕዝብ!የባህር በር አልባ አገር ኢትዮጵያ!




ፊንፊኔ #Ethiopia ጥቅምት 03/2016(YMN) ወደ ኋላ መሄድ የለም ጉዞ ወደፊት ብቻ!እኛ ኢትዮጵያዊያን የባህር በር አልባ የሆንበት ታሪካዊ ሁኔታ ይታወቃል አሁን ቁስል ማከክ አይጠቅመንም ቁጭት ምን ያደርጋል?

የኢትዮጵያ አንድ አካል የነበረችው ኤርትራ ከሰላሳ ዓመታት በፊት ሉአላዊ አገር መሆን የቻለች ናት፤የኤርትራ ሉአላዊነት ከኢትዮጵያ አያንስም አይበልጥም እኩል ነው!እዚህ ላይ የአስተሳሰብ ችግር ያለባቸው ዜጎች ስህተታቸውን ማረም አለባቸው!

ወይም ደግሞ እንደተለመደው ይህን እውነታ በመካድ የሚንቀሳቀሱቱ በክህደት የሚታወቁ ባንዳዎች ናቸውና ስለ እነርሱ ምንም ማድረግ አይቻልም፤ጊዜ ምላሽ ይሰጣቸዋል አዲሷ ኢትዮጵያ ከየትኛውም ከቅርብም ከሩቁም አገራት ጋር ጦርነት ውስጥ መግባት አትሻም  ኢትዮጵያኮ ሄዳ ማንንም አትነካም ተፈጥሮዋም አይደለም፤ይህ ማለት በሉአላዊነትና ብሔራዊ ጥቅሟ ላይ ለመጣው ዝም ትላለች ማለት አይደለም! ስንነካ ምን እንደምንሆን ሁላችንም እናውቃለን ቀፎው የተነካ ንብ መሆናችን ይታወቃል

የቀድሞዎቹ መሪዎች ከኤርትራ  ጋር ለአመታት የቆየ ጦርነት ውስጥ አስገብተውን በሚሊየን የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ደመ ከልብ ሆነው የቀሩት በወቅቱ በነበሩ አመራሮች የዕውቀት ማነስና የስህተት አካሄድ ምክንያት ነው ያለፉ አባቶችን ለመውቀስ አይደለም!

በተለይም በኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም ጊዜ በደርግ ስርዓት ከየቤቱ በግዳጅ ተወስዶ በኤርትራ በረሃ ውስጥ የቀረው ወጣት ስንት ነው?በዘመነ ኢህአዴግ ወቅትስ ለቁራሽ መሬት ሲባል ስንት ሺህ ወጣት ትውልድ አለቀብን? የወደመው ኢኮኖሚስ ምን ያህል ነው?በወያኔ ቁንጮዎች እብጠት ምክንያት አሁን በቅርብ በአውዳሚው ጦርነት ያለቀው ወገንስ ምን ያህል ይሆናል?ያጋጠመው ክስረትና ውድመት አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያንን ሁሉ የሚያስቆጭና የሚያንገበግብ ነው

ኢትዮጵያ አሁን ይህን እውነት በቅጡ መረዳት የሚችል አመራር አላት በእብሪት ተወጥሮ በማን አለብኝነት ሕዝቡን ወደ ጦርነት የሚከት መንግስት የለንም፤ለዚህ የሚገፋፉ ኃይሎች ግን እዚህም እዚያም እንዳሉ ይታወቃል ግልጽ ነው

አሁን በዚህ ሰሞን ምን እየተባለ ነው?አጭበርባሪ የፖለቲካ ነጋዴዎች በየስረቻው ተወሽቀው የሚዶልቱትን ማወቅ ይገባል!መንግስት የባህር በር ይገባናል ባህር አልባ አገር ሆነን መቀጠል አንችልም ብሎ  እውነታውን ሲያቀርብ ከቅርብም ከሩቅም እየተወራና እየተነዛ ያለው ፕሮፓጋንዳ  ምንድነው?እያንዳንዱ ለውድ አገሩ ኢትዮጵያ የሚያስብ ዜጋ ይህን መመርመርና መረዳት ይጠበቅበታል!

አለበለዚያ ጮሌ ጩሉሌ የፖለቲካ ነጋዴዎች በሚሉት ብቻ እንደ እንስሳ መነዳት ይመጣል፤የከሰሩ የፖለቲካ ነጋዴዎች ካጋጠማቸው ክስረት ለመውጣት ለማገገም ይህን አጋጣሚ መጠቀማቸው የማይቀር ነው

ቀድመውም ጀምረውታልኮ “ብልጽግና መራሹ የኢትዮጵያ መንግስት በአሁኑ ወቅት የባህር በር ጉዳይን ያመጣው የወቅቱን አጀንዳ ለማስቀየር ነው” ተብሏል፤ኤርትራን መበቀል የሚሻው ኃይልም “ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ልትዋጋ ነው” ብሎ ልቡን ቅቤ ያጠጣ መስሏል፤እርሱ ከጦርነት ያተርፋላ!የፖለቲካ ገበያው ደርቷል ሸማቹ ማን ይሆን? በሂደት የሚታይ ይሆናል

ለማንኛውም መንግስታችን የባህር በር ጥያቄያችን ምላሽ የሚያገኘው በሰላማዊ መንገድ ብቻ ነው ብሏል ተገቢ አቋም ነው ሊደገፍ ይገባል! አብዛኛው ዜጋ ይህን እውነት ይረዳል ይገባዋል፤ ምን እየተባለ እንደሆነ ያውቃል በጥባጩ፤እይታን የሚያዛበው በጣም ጥቂቱ ነው ከዚህ ጥቂት በወሬው ጤፍን ከሚቆላው ራስን መጠበቅ ይገባል!

ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የመደራደሪያ አቅም አለኝ ብላ ከተነሳች አትችይም ብሎ ከፊቷ የሚቆመው ማነው?መጪው ጊዜ አስቸጋሪ እንዳይሆን አዲሱ ትውልድ የሰቀቀን ኑሮ እንዳያጋጥመው ከአሁኑ መስራት አለብን የሚለውን አቋም አብዛኛው ሕዝብ ይደግፋል ለተግብራዊነቱም ይንቀሳቀሳል አስደሳቹ እውነት ይህ ነው

አለም አቀፍ ሕጎችን በመመርመር፤የስነ ሕዝብ አወቃቀርና አሰፋፈርን መሰረት በማድረግ፤እንዲሁም የወንዝ ሃብቶቻችንን በመጠቀምና አሁን የደረስንበትን የኢኮኖሚ ደረጃ ተጠቅመን የባህር በር ባለቤት የምንሆንበት ጊዜ ሩቅ አይሁን!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር ባደረጉት ቆይታ የሰጡት ገለፃ ጠቀሚ ነው፤ ሃሳቡ ብዙሃኑ ዘንድ ደርሷል በቅጡ መረዳት ያስፈልጋል

አማራጩ ብዙ ነው፤አንዱን ይዘን ሙጭጭ የምንለበት ሁኔታ የለም በዚህ የኢትዮጵያ መንግስ አዲስ ሃሳብ ጎረቤት አገራት በመጓጓት መሽቀዳድም ውስጥ የሚገቡ ይመስለኛል ውሳኔው የኢትዮጵያ ነው የቱ ያዋጣኛል? ዘላቂውስ የቱ ነው? የትውልድ እፎይታ በየትኛው ይገኛል? የሚለው ውሳኔ በኢትዮጵያ እጅ ውሰጥ ይገኛል ይኸው ነው!

እሳቸው ባቀረቡት የእንወያይ ሃሳብ መሰረት ከአሁን በኋላ ውይይቱ ይጦፋል ተብሎ ይጠበቃል፤ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ ይንቀሳቀሳሉ ምሁሩ ይናገራል ከታሪክ አዋቂዎች አንደበት ብዙ የምንሰማ ይሆናል፤አማራጮቹ ሁሉ ይቀርባሉ፤የሊህቃን ውይይት መግባባትን ይፈጥራል፤ፖለቲካዊ ንቃትና አቅም የሚፈጠር ይሆናል፤ታሪክና ትርክት ይታያል፤ከቀይ ባህር የነጠለን ትርክትም ይከለሳል!እንደ አገር የባህር በር ባለቤት የምንሆንበት ጊዜ ሩቅ አይሁንብን! መልካም ቆይታ!

Post a Comment

0 Comments