የርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ምስጋናና መልዕክት



የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር ሃላፊነታቸውን ለተወጡ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ እሴቱንና ስርአቱን ጠብቆ ፣በሰላማዊ መንገድና ባማረ ሁኔታ ተከብሮ ተጠናቋል።

ርእሰ መስተዳድሩ ኢሬቻ ምስጋና፣ እርቅ፣ ይቅርታ፣ ፍቅር፣ ሰላም እንዲሁም አንድነት እና ወንድማማችነት ከፍ ብሎ የሚታይበት መሆኑን አሳይቷል ብለዋል።

"በአሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ ከሀገር ውስጥና ከውጪ ሀገራት የተሳትፈበት መሆኑን ጠቅሰው በሰላም ተከብሮ መጠናቀቁ፣ ሕዝባችን ሰላም ወደድ መሆኑን፣ ባህላችን እና እሴቶቻችንም ለሰላም ትልቅ ቦታ የሚሰጡ መሆናቸውን ለዓለም ያሳየንበት ለክልላችን ብሎም ለሀገራችን ትልቅ ኩራት ነው" ብለዋል።

ለዚህም "አባ ገዳዋች፣ ሃደ ሲንቄዎች፣ ቀሬ እና ቄሮዎች፣ ፎሌዎች፣ በአጠቃላይ መላዉ የእሮሞ ህዝብ ባህላችንን ጠብቃችሁ እዚህ እንዳደረሳችሁ፣ ዛሬም ለበዓሉ ክብር በመስጠት የበአሉን ሰላም በማስጠበቅ የሆራ ፊንፊኔ በአል በሰላም እንዲጠናቀቅ ስላደረጋችሁ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ"ብለዋል።

የፊንፊኔ ከተማ አስተዳደር አመራርና መላው የከተማው ነዋሪዎች ፣ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ የበዓሉ ታዳሚ የሆኑ የውጪ ሀገር ዜጎች እንዲሁም በየደረጃዉ የሚገኙ የፌዴራል፣ የፊንፊኔ ከተማ አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልል የፀጥታ አካላት የሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል ሥርዓቱን ጠብቆ እንዲከበር እንዲሁም የበዓሉ ታዳሚዎች ያለምንም የፀጥታ ችግር በዓሉን በሰላም አክብረው እንዲመለሱ በማስቻላቸው ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በሌላ በኩል ኢሬቻ የምስጋና በዓል፣ እርቅ፣ ይቅርታ፣ ሰላምና ፍቅር የሚዘመርበት አንድነትና ወንድማማችነት የሚፀናበት መድረክ ከመሆንም አልፎ አለም ሊማርባቸዉ የሚገባ እሴቶችን ያቀፈ መሆኑን ለአለም ህዝብ ላሳዩ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር የሚዲያ ባለሙያዎችም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በሰላማዊ መንገድ ተከብሮ እንደተጠናቀቀ ሁሉ በነገው እለት በቢሾፍቱ ከተማ የሚከበረው የሆራ አርሰዴ ኢሬቻም ባህላዊ እሴቱን አጉልቶ በሚያሳይ መንገድ እንዲከበር ባለድርሻ አካላት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ  አቶ ሽመልስ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Post a Comment

0 Comments