ፊንፊኔ #Ethiopia ጥቅምት 07/2016(YMN) መፍትሔው የሰለጠነች ኢትዮጵያን መፍጠር እንጂ ለኢትዮጵያ ደምን አፍሶ አጥንት መከስከስ ብቻ አይደለም።”ለእናት ሀገራችን ይፈሳል ደማችን! አባቶቻችን በደምና በአጥንት ያቆዩትን አገር እኛም በደምና በአጥንታችን እንጠብቃለን።”
እነዚህ አባባሎች በኢትዮጵያ የተለመዱና ማንኛውም አገር ወዳድ ዜጋ የሚቀባባለቸው የአገር ወዳድነት ንግግሮች ናቸው።ይሁንና አንድ ጥያቄ አነሳሁና የግል ምልከታዬን ላካፍላችሁ ወደድኩ።አገራችንስ ብትሆን ለምን ሁልጊዜ የኛን ደም ትፈልጋለች?እኛስ ልጆቿ አይደለንም እንዴ? አናሳዝናትም?በቀጣይስ የሚያዋጣን ለኢትዮጵያችን ደምና አጥንት መከስከስ ወይስ ኢትዮጵያችንን ማሰልጠን?
ኢትዮጵያ ዛሬ ባለችበት ሁኔታ ማለትም የዓለም ጭራ የሆንበትና መረጋጋት ያልቻለችበትን ምክንያት ለአንድ ዶክመንት ማሟያ ትንሽ ጥናት አድርጌ ነበር።በውጤቱም አስራ ሶስት የሚሆኑ ትላልቅ ነጥቦች የለየሁ ሲሆን ከነዚህም አንዱ በአገሪቱ በተለያዩ ዘመናት የሚካሄዱ ጦርነቶች መሆናቸውን በመለየት የደም ምድር የመሆን አባዜ ብዬ ነበር።
ከጣሊያን ወረራ ጀምሮ በሀገራችን ስድስት(6) ትላልቅ ጦርነቶች ተካሂደዋል።ሶስቱ ከውጭ ወራሪዎች (ጣሊያን፤ሶማሊያ፤ኤርትራ)ጋር የተካሄዱ ሲሆን የተቀሩት የእርስ በርስ ጦርነቶች ነበሩ ።
ጦርነት በየትኛውም ዓለም የነበረና ያለ ሲሆን በርካታ አገሮች በአስከፊ ጦርነትና እልቂት ውስጥ አልፈው የተረጋጋች አገር መፍጠር ችለዋል።ጦርነት በባህሪያቸው ማስቀረት የሚቻሉና የማይቻሉም ጭምር ናቸው ለምሳሌ የውጪ ወራሪ ከመጣ ያለው አማራጭ ተዋግተህ ሉዓላዊነትህን ማስከበር ነው።ሌሎች ደግሞ የተለያዩ አማራጮችን ተጠቅሞ ማስቀረት የሚቻሉ ጦርነቶችም አሉ።የኛን አገር ችግር ከወሰድን የመጣው የጦርነት ወጀብ ሁሉ በተኩስና በዕልቂት መታጀቡ ነው።
የኔ ትዝብት ከላይ ፅሁፉን ስጀምር የተጠቀምኩባቸው የአርበኝነት መፈክሮችን ጨምሮ ባህላችን ጦርነት አድናቂና የአገር ፍቅር መገለጫ የህዝብ መብት ማስከበሪያ አድርገን የወሰድን ይመስለኛል ።
የጣሊያን ወረራን በምኒልክ ካሸነፍንና ነጮችን ያሸነፈ ህዝብ መባላችን የኢትዮጵያን ህልውና የምናስከብረው በኃይል ብቻ እንደሆነ የተማመን ይመስለኛል።ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያን የመሩ መሪዎች ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪየም ደሳለኝ በስተቀር ሁሉም መሪዎች እንደ መንግስት ጦርነት አውጀዋል ባህል እስኪመስል ድረስ፤
በሚገርም ሁኔታ ከሱማሊያ ጦርነት በስተቀር ሁሉም ጦርነቶች የተካሄዱት በሰሜኑ ክፍል ነው፤የነበሩ መሪዎች በተጨማሪ የአከባቢውን አንዳንድ ነገር እንመልከት ።
የትግራይ ክልል ተወላጆች በከፍተኛ ሃዛን ላይ ናቸው ግማሽ ሚሊዮን ልጆቻቸውን አጥተዋል።ስለጦርነቱ አጀማመር የሚወራውን ትርክት ትተን ቢያንስ ጌታቸው ረዳ ትላንት ነካ አድርጎ ያለፋትን ነጥብ በጥልቀት ቢመለከቱ ይበጃቸዋል።የትግራይ ህዝብ ከጭቆና ለመላቀቅ ልጆቹን የገበረበት ጦርነት በሀገራችን ነበር።በወቅቱ ደርግን ጥሎ ሀገር እስከመምራት ደርሰዋል ከሰላሳ ዓመታት በኃላ ሌላ ዕልቂት ለምን አስፈለገ? የትግራይ አመራሮች ጦርነት ባህላዊ ጨወታችን ነው እያሉ ኮሽ ባለ ቁጥር ተገፋን ብሎ ባሰቡ ወቅት ሸበጥና ቁምጣ ለብሰው በሽርጥ ተጀቡነው ክላሽ አንግተው መፎከር አደባባይን በሰልፍ እያደመቁ ለጦርነት መዘጋጀት ባህል ማድረጋቸው ዋጋ አስከፍሏቸው እየሄደ ነው። የትግራይ ሕዝብ ችግር ከጦርነት ውጪ አይፈታም ወይ? ጌታቸው ራሳችን እንፈትሽ ብሏል መልካም ነው።
የአማራ ክልል የቆየ ባህል ወይም ልምድ አለ ጀግንነትን ሁሌም በመገዳዳል ማስመስከር መፎከር! እያንዳንዱ አማራ “አራሽ ቀዳሽ ተኳሽ ነው” የሚል ይህ አደገኛ የውጊያ ፍላጎት መገለጫ ነው።እስክ አስቡ እስኪ ጠመንጃ ይዞ ሲዋጋ ሲገድል የዋለ ሰው ቆይቶ ክላሹን አስቀምጦ መስቀል ይዞ ሲቀድስና ሲባርክ።እስከሚገባኝ የሐይማኖት አባቶች ጦርነትን እያወገዙ ለሰላም ይሰራሉ ሲባል እዚሁ ታዋጊ እዚሁ የሐይማኖት መሪ ከተኮነ ነገሮች ተዘበራርቀዋል።
ከዚህ ሁሉ ይልቅ ሁላችንም በላብ በደምና በአጥንት ኢትዮጵያን ለማፅናት የሄድነውን ርቀት ያህል ኢትዮጵያን አሰልጥነን ጦርነት የምትጠየፍ ሁሉንም ልጆቿን እኩል የምታስተናግድ፤ችግሮችና ልዩነቶችን በውይይትና በንግግር መፍታትን ባህል ያደረገች ዲሞክራቲክ አገር ለማድረግ ሰርተን ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያ እናቶች በአራቱም አቅጣጫ ለቅሶ ባልተቀመጡ ነበር።
(በአላካ ሲንብሩ)
0 Comments