የ“አውራውን ምታ መንጋውን በትን” ስልት አልሰራም!




ፊንፊኔ #Ethiopia ጥቅምት 25/2016(YMN) የውጭና የውስጥ ጠላት ትኩረትና ቅንጅት በምንና በማን ላይ እንደሆነ ከተረዳን ሰነባብተናል፤ከውጭ ያለው ጠላት የውስጡን ጠላት ፈረሱን እንዴት እንደሚጋልብና የውስጡም ጠላት በውጭ ጠላቶች በምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚጋለብ አሳይቶናል

ታሪካዊ ጠላቶች ጋላቢዎቹና የተጋላቢዎቹ ፈረሶች ቅንጅት እስከምን ድረስ እንደሆነ የለውጡ ሃይልና በብዙ ሚሊየን የሚቆጠሩ የለውጡ ደጋፊዎችና ጠባቂው የታላቋ ኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳዩን አውቆ በአግባቡ ከተረዳ ዓመታት ተቆጥረዋል

ባይሆንማ ኖሮ ሰፊው የኦሮሞ ህዝብና ከኦሮሞ የወጡት የኢትዮጵያ መሪ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ዛሬ አይኖሩም ነበር ጥንት በሴራ ከመንገድ እንደቀሩቱ ጀግኖች ይቀሩ ነበር፤ይህ ሲታሰብ ሊሆን የሚችለው ሁሉ ለአዕምሮ ከባድ ቢሆንም ጉዳዩን በጥሞና ማየትና መመርመር ያስፈልጋል፤ዕቅዳቸው ቢሳካ ዛሬ የኦሮሞ ሕዝብ አንገቱን ቀና አድርጎ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር ጠላትን እየተከላከለ ሴራቸውን እያከሸፈ የልማትና ዕድገት ግስጋሴውን ማስቀጠል አይችልም

ገና በጠዋቱ ዐብይ አህመድ አሊ ላይ የተቃጣው የግድያ ሙከራ ቢሳካ ኖሮ ኢትዮጵያ የምንላት ውድ አገራችን ፈርሳ ብትንትኗ ይወጣ ነበር፤ልክ እንደ ሶማሊያ፤ሊቢያ፤ሶሪያና ሌሎችም አገራት ኢትዮጵያም ትፈርስ ነበር፤ምስጋና ለአገር ጀግኖች!ጠላት ያቀደው ቀርቶ ውጥኑ ሁሉ ተኮላሽቶ ኢትዮጵያ ጠንካራ አገር ሆና መቀጠል ችላለች!

በዋናነት ጥንትም ሆነ አሁን የኢትዮጵያ ምሰሶ በሆነው የኦሮሞ ሕዝብ ላይ ትኩረት በማድረግ ሁሉም ኦሮሞ እንዲሸማቀቅ፤በአገሩ አንገቱን ቀና አድርጎ መኖርና መንቀሳቀስ እንዳይችል ከወዲያና ወዲህ የተሽጎደጎደው ፀያፍ ስድብና የተሰጠው ስም ቢቆጠር ምን ያህል ይሆን?ስፍር ቁጥር የለውም!ማለት ይቻላል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ከኦሮሞ ማህበረሰብ የወጡ መሪ በመሆናቸው ምክንያት ብቻ ሁሉም ኦሮሞ “ተረኛ” ተብሎ ተዘልፏል፤”የዘመኑ ሰው” ተብሏል የጥንት ሆዳም ፊውዳሎች ኦሮሞን እንደ ብሔር ለማሳነስ ለማሸማቀቅ ሆን ብለው የፈጠሯቸው ስድቦችና አባባሎች ከተደበቁበት ወደ አደባባይ ብቅ ብቅ ብለው ሰምተናል፤ተመልክተናል

ኦሮሞ እንደ ሕዝብ በስፋቱ ልክ ሆደ ሰፊ ሆኖ ይህን ሁሉ ችሎ፤ነገ የተሻለ ጊዜ ይመጣል ብሎ የተቃጣበትን አደጋ ሁሉ ተቋቁሞ ነው ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር ኢትዮጵያን ማስቀጠል የቻለው!በኦሮሚያ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ስራ አጥ ወገኖች ተላላኪ ሆነው የጠላትን ተልዕኮ ተቀብለው መንገዶችን ዘግተው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲገደብ አድርገዋል፤ኦሮሞ በዚህ የጠላት ሴራ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር ተጎድቷል፤ከመኖሪያ ቀዬው ተፈናቅሏል፤ህይወቱን አጥቷል ንብረቱ ወድሟል

በተለይም የመከላከያ ሰራዊት ለጊዜው በአስቸኳይ ሊደርስ ባልቻለባቸው አካባቢዎች የሚገኘው ሕዝብ በአፈ ሙዝ ተገድዶ የሆነው ይታወሳል፤መከራውና እንግልቱ አሁን ቀንሷል የጠላት ተላላኪው ፈረስ ሸኔ በተለያዩ ወቅቶች በተወሰዱ እርምጃዎች ተደምስሶ ተመናምኗል፤ተስፋ የቆረጠውም ተበታትኖ በመሸፈት ጫካ ውስጥ ለመኖር በመገደድ ይኸው እንዲህ እንደምትመለከቷቸው ፍጡሮች ዓይነት ሆኗል

እነዚህ ከቄለም ወለጋ ደን ውስጥ በመከላከያ ሰራዊት ታድነው በቁጥጥር ስር የዋሉ የሸኔ አባላት ናቸው

አሁን በሚታወቀው ሁኔታ ተበታትነው የቀሩ የሸኔ አባላት አቅም ኖሯቸው በመንቀሳቀስ የጠላትን ተልኮ ከግብ ማድረስ የሚችሉ እንዳልሆኑ ተረጋግጧል፤ሕይወታቸውን ለማቆየት ሲሉ ተሽሎክሉከው ለመኖር የተገደዱ መሆናቸው ግልፅ ሆኗል የእዩኝ እዩኝ ፉከራ ወደ ደብቁኝ ተቀይሯል

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ጠላት ትኩረት ኦሮሞና አማራ ላይ ስለሆነ ወደ አማራ ክልልም በመሄድ የአማራ ሕዝብ ላይ የተሰራው ሴራ በአማራ ሕዝብ እንቢተኝነትና በጀግኖች ተጋድሎ ሙሉ በሙሉ ከሽፏል፤ተላላኪው ፈረስ ተሽመድምዷል፤ፉከራውና ቀረርቶው ወደ ለቅሶ ተለውጧል

የፋኖን ስም ተገን በማድረግ የተነሳው ወሮበላና ሽፍታ ቡድን ከሽፏል፤የተሰጠውን አገር የማፍረስ ተልዕኮ ከግብ ማድረስ አልቻለም ሰፊውን የአማራ ሕዝብ በማጭበርበር ከጅማሬው ለውጡን በማጥላላትና በማጣጣል ሲያሴር የቆየው የውስጥና የውጭ ጠላት አሁን የሚገባውን ዋጋ የእጁን አግኝቷል

ጠላት ሆይ ችሎታ ካለህ ማሰቢያህ ከሰራ አትችልም እንጂ ትንሸ የማገናዘብ ብቃት ካለህ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ምናልባት መረዳት ከቻልክ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያን ሕዝብ ማሸነፍ አትችልም!ተበልጠሃል!

የአሁኑ ትልቅ አጀንዳ የባህር በር ነው!ትኩረታችን ቀይ ባህር ላይ ሆኗል! ኢትዮጵያ ማንንም ሳትጎዳና ጫና ሳታደርግ ዓለም አቀፍ ሕግና ታሪካዊ ሁኔታዎችን በመጠቀም በሰጥቶ መቀበል መርህ የባህር በር ባለቤት ለመሆን እየሰራች ነው፤የሁሉም ዜጎች ትኩረት እዚህ ላይ ሆኗል፤ጩኸትህ ሌት ተቀን ቢሆን የሚሰማህ የለም የቁራ ጩኸት ሆኖ ይቀራል

ምክንያቱም ወገን የጠላትን የማዘናጊያና የማጭበርበሪያ ፕሮፓጋንዳ የሚሰማበት ጊዜ የለውም፤ዋነኛው ትኩረት አገሩ ላይ መሆኑን በተግባር እያሳየ ነው፤አርሶ አደሩ ከዘልማድ እርሻ በመውጣት ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ወደ ኩታ ገጠም እርሻ ስራ በመግባት ምርታማነትን በመጨመር እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል

ይህ ደግሞ የኑሮ ውድነትን ችግር ለማስወገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ተረጋግጧል፤አምራቹና ሸማቹ በቀጥታ እንዲገናኝ እየተሰራ ነው፤ለዚህ ተጨባጭ ማስረጃ መሆን የሚችለው በፊንፊኔ አምስቱም የመግቢያ በሮች የተገነቡ የግብርና ምርት ገበያ ማዕከሎች ናቸው አሁን”ደላላ ጉድህ ፈላ” ብለን መናገር የምንችልበት ሁኔታ ተፈጥሯል

ለማረጋገጫ ጥቅምት 24/2016 ዓ.ም በክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረውን የኮልፌ የግብርና ምርቶች ማቅረቢያ ገበያ ማዕከል ብቻ መመልከት በቂ ይሆናል


በፊንፊኔ አዲስ አበባ ኮልፌ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት የተጀመረ የግብርና ምርቶች ገበያ ማዕከል

ይህ ማዕከል ብታምንም ባታምንም በዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ ለአገልግሎት መድረስ ያቻለ ነው፤በ2 ነጥብ 3 ሄክታር መሬት ላይ በ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ወጪ የተገነባው የገበያ ማዕከል 24 ሰዓት አገልግሎት መስጠት የሚችል ነው፤ጠላት ይህን ሲመለከት ዓይኑ ይቀላል!ሕዝብ እፎይ የሚልበት የልማት ስራ የዘረፋ ተግባራቸውን እስከነ አካቴው እንደሚያስቀርባቸው ስለሚያውቁ ምቾት አይሰማቸውም፤እንግዲህ ምን ማድረግ ይቻላል? ምልሹ ምንም ነው!

በአጠቃላይ“የአውራውን ምታ መንጋውን በትን” ስልት እንዳልሰራ ተረጋግጧል ጠላት በዚህ ምክንያት ቁጭት ውስጥ መግባቱን የሚያመላክቱ እንቅስቃሴዎች እየታዩ ነው ምዕራባዊያን በተለይም የዓለም ገዥ ነኝ የምትለዋ አገር ለኢትዮ ኤርትራ ያሰበች ይመስል ቁንጮዎቿ አንዳንድ ጉምጉምታቸውን በማሰማት ላይ ይገኛሉ፤በመካከለኛው ምስራቅ አገራት አካባቢ የጀመሩት ብጥበጣ የማያወጣ መሆኑን የተገነዘቡ ይመስላል

ትኩረታቸው ወደ ምስራቅ አፍሪካዋ ታላቅ አገር ኢትዮጵያ ላይ እንደሚሆን ይታወቃል፤ለማንኛውም የከፋፍለህ ግዛና አውራውን ምታ መንጋውን በትን የጠላት ስልትና አካሄድ አልሰራም ወደፊትም የሚሰራ አይሆንም! 

Post a Comment

0 Comments