የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መግለጫ

  




ፊንፊኔ #Ethiopia ሕዳር 02/2016(YMN) መሪን ከህዝብ በመነጠል እና ህዝብን መሪ አልባ በማድረግ የሚጸና ማንነት የሚለወጥ ፖለቲካ የለም! የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት

ጽንፈኝነት ሁሉንም በአንድ ጣሪያ ሊያሰባስብ የሚችል ትርክት ከመገንባት ይልቅ ልዩነትን በመስበክ በከረረ ጥላቻ በሚናዉዙ ግለሰቦች እና ቡድኖች የሚዘወር አሁን ላለንበት ዘመን የማይመጥን እኩይ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ነዉ። የዚህ እኩይ አላማ ባለቤት የሆኑ ቡድኖች እና ግለሰቦች ሀገርን ለማፍረስ መሪን ከመግደል፣ ከማሳደድ እና ከማሸማቀቅ ትርፋቸዉን የሚያገኙ ናቸዉ።

በዚህ መዳረሻ የሌለዉ የፖለቲካ አካሄድ ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግስት እንዳይኖር እና የተበታተነ ህዝብ እንዲኖረን የሚያደርግ ነዉ። ዉጤቱም እርስበርስ መከፋፈል ልዩነቶችንም ከማቻቻል ይልቅ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት መግባት እንደህዝብ የማይተካ ዋጋ መክፈል ነዉ።

እነዚህ ሀይሎች ኢትዮጵያን ሊፈትኗት እንጅ ከቶዉንም ሊጥሏት እንደማይችሉ የመጣንበት መንገድ ምስክር ነዉ። ለዚህም ሰላምና ፍቅርን የያዘ ሁሉ አሸናፊነትን እንደሚቀዳጅ የሚያምነዉ መንግስት ለሚገጥሙት ፈተናዎች ሁሉ ከህዝብ ጋር አብሮ በትዕግስት እና በጽናት መሻገር የሚችል አመራር አደራጅቶ ወደ ስራ ከገባ ሰነባብቷል። በዚህ ጊዜም ፈተናን ተቋቁሞ ለህዝብ ሲል ራሱን አሳልፎ ለመስዋዕትነት ያዘጋጀ መሪ መፍጠር ተችሏል።

ይህ በጊዜያዊ ስሜት የሚነዳ የህቡዕ አደረጃጀት ሊያዉቀዉ የሚገባ ነገር ቢኖር የኢትዮጵያ አይቀሬ ብልጽግና ቅርብ መሆኑን እና በገዳይ አስገዳይ ፕሮፓጋንዳ ሸብረክ የሚል አንድም የብልጽግና መሪ አለመኖሩን ነዉ።

እንደህዝብ መሪዎቻችን በማሳደድ ብርታታችን እና መልካም ገጽታችንን የሚያበላሹ፤ ጸጋዎቻችንን በአግባቡ እንዳንጠቀም የሚያባክኑ፤ አንሰዉ የሚያሳንሱን እና ትውልድ የሚያመክኑ የተቃርኖ አሰላለፎችን መመርመር እና ማረቅ የምንጊዜዉም ስራችን መሆን አለበት።

በመሆኑም ጽንፈኝነት ከስነ_ፍጥረቱ መሪን ከህዝብ በመነጠል ህዝብን መሪ አልባ በማድረግ ላልተገባ የፖለቲካ ግቡ መጠቀም ዋነኛ መገለጫዉ መሆኑን በመረዳት ህዝባችን ወደነበረ ሰላሙ በመመለስ ልዩነቶቻችንን በማጥበብ ዛሬም ህዝባችን እንደትናንቱ በሀገር ግንባታ ሂደት ዉስጥ ያለዉን ጉልህ ድርሻ እንዲያበረክት መስራት ይገባል።

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሰት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ

ህዳር 01/2016 .

ባሕርዳር

Post a Comment

0 Comments